በኤአይ የወጡ ፎቶዎች
የምስሉ መግለጫ,በኤአይ የተዘጋጁ ፎቶዎች

ከ 9 ሰአት በፊት

በየዕለቱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ውስብስብ እየሆኑ በመጡበት ባለንበት ዓለም እንዲህ ዓይነት ምሥሎችን በዐይን አይቶ የቴክኖሎጂ ፈጠራ መሆናቸውን መለየት ቀላል አይደለም።

ከምሥሎች ባሻገር ሥነ ጽሑፎች፣ ሙዚቃ እና ግጥም እንዲያው በአጠቃላይ የሥነ ጥበብ ውጤቶች በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) አማካይነት እየተመረቱ ነው።

እነዚህ በኤአይ አማካይነት የሚዘጋጁት ሥራዎች ለእውነታ እጅግ የቀረቡ በመሆናቸው ምክንያት የሰው ልጅ የአእምሮ እና የእጅ ውጤት ከሆኑት ጋር መለየት እጅጉን አዳጋች እየሆኑ መጥተዋል።

ታዲያ አንዳንዶች ይህን የቴክኖሎጂ ውጤት ላልተገባ ዓላማ በመጠቀም እውነት የሚመስሉ ይዘቶችን በማሰራጨት በርካቶችን እያሳሳቱ ይገኛሉ።

በኤአይ የወጡ ፎቶግራፎች
የምስሉ መግለጫ,ከሁለቱ ፎቶዎች ትክክለኛው የሰው ፎቶ የቱ ነው?

ለምሳሌ ከላይ ካሉት የሁለት ታዳጊዎች ፎቶዎች መካከል በካሜራ የተነሳ ትክክለኛ የሰው ፎቶ የቱ ነው? የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤት የሆነውስ የትኛው ነው?

እንደሚታዩት የሁለቱ ታዳጊዎች ምሥሎች ፊታቸው ላይ ፈገግታ የሞላ በሻሽ ፀጉራቸውን የሸፈኑ፣ ገጽታቸው ቀርቦ የሚታይ ጉርድ የሚባለው ዓይነት ፎቶዎች ናቸው። ምን ተመለከቱ? የትኛው እውነተኛ፣ የትኛውስ ፈጠራ ነው?

የሁለት ታዳጊ ሴቶች ምሥሎች የእውነተኛ ሰው ፎቶግራፎች አይደሉም፤ የኮምፒዩተር ውጤት እንጂ።

በቅርቡም በኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች መልዕክቶቻቸውን ለማስተላለፍ ወይም ደግሞ ሐሰተኛ ዜናዎችን ሆነ ብሎ ለማሰራጨት በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተዘጋጁ ምሥሎችን በማዘጋጀት ሲያጋሩ በስፋት እየታዩ ነው።

ብዙዎች በኢትዮጵያ ያለውን የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት፣ የመብት ጥሰቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ይገልጻሉ የሚሏቸውን ምሥሎች በኤአይ እያመረቱ ያጋራሉ። ታዲያ እነዚህን ለእውነት የቀረቡ ምሥሎችን ለበርካታ ሰዎች ሲያጋሩ ምሥሎቹ እውነተኛ ሳይሆኑ በኤአይ የተመረቱ እንደሆኑ አይገልጹም።

በኤአይ ምስል እንዴት ይሠራል?

እንዲህ አይነቶቹ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተዘጋጁትን እውነተኛ የሚመስሉ ምሥሎች የሚዘጋጁት ልፋትን በማይጠይቅ በቀላል ሁኔታ ነው። ይህም የሚሠራው ለሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የምንፈልገውን ምሥል መረጃ በጽሁፍ በመስጠት ትዕዛዝ በመስጠት ነው።

ስለዚህ ሂደቱን በቀላሉ ለማስረዳት ቴክኖሎጂው ጽሑፍን ወደ ምሥል በመቀየር ነው እውነት መሳይ ፎቶዎችን የሚሰጠው።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤት የሆነ ምሥል ለማግኘት ምሥሎቹን ወደሚሠሩ ጄኔሬቲቭ ኤአይ (generative AI) ወደሚባሉ ድረ-ገጾች በመሄድ በጽሑፍ ትዕዛዝ በመሰጠት የፈለግነውን ዓይነት ምሥል ማግኘት እንችላለን።

እንደ ምሳሌ ከዚህ በታች ያለውን ምሥል እንመልከት።

ኤአይ ፎቶ

እንደሚታየው ምሥሉን ለማግኘት የተሰጠው መግለጫ “black woman with colored hair, in a white dress drinking coffee; sitting by the window” (ፀጉሯን ቀለም የተቀባች፣ ነጭ ቀሚስ የለበሰች፣ ከመስኮት ጎን ተቀምጣ ቡና የምትጠጣ ጥቁር ሴት) የሚል ነው።

ድረ-ገጹም የተሰጠውን መግለጫ ተቀብሎ ይህን ምሥል አውጥቷል።

በስፋት ከሚታወቁ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤቶች የሆኑ ምሥሎችን መሥራት የሚቻሉባቸው በርካታ ድረ ገጾች ያሉ ሲሆን፣ ቁጥራቸው እየጨመረ ከመጡት ተመሳሳይ ድረ ገጾች መካከል Midjourney, Dall.E, Adobe Firefly, NightCafe, Stable Diffusion ተጠቃሽ ናቸው።

ከላይ እንደምሳሌ የተጠቀምነውን ምሥል ያወጣው አዶቤ ፋየርፍላይ ድረ-ገጽ ነው።

እነዚህን ምሥሎች እንዴት መለየት ይቻላል?

ምንም እንኳ የምንፈልገውን ዓይነት ምሥል ለማግኘት ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ቀላል አማራጭ ሆኖ ቢቀርብም ይዞት የሚመጣው ስጋትም አለ።

አንዳንዶች የገንዘብ ጥቅም እና የፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ የኤአይ ውጤቶችን በመጠቀም ሰዎችን ሆነ ብለው ሲያሳስቱ ታይተዋል። በርካቶች ገንዘባቸውን ተጭበርብረዋል ሌሎች ደግሞ መልካም ስማቸውን አጥተዋል።

በኤአይ የሚሠሩ ምሥሎች ለእውነት እጅጉን የቀረቡ ስለሆኑ እውነተኛነታቸውን መለየት እጅግ አዳጋች ሊሆን ይችላል።

ይሁን እንጂ በትኩረት ምሥሎችን በመመልከት በምሥሉ ላይ እርስ በእርስ ሊጣረሱ የሚችሉ ነገሮችን ልናስተውል እንችላለን።

በምሥሉ ላይ ማየት የሚቻል ከሆነ ብርሃን የሚመጣበትን እና በምስሉ ላይ ያለው ግለሰብ ጥላ ያረፈበትን አቅጣጫ እንመልክት። አቀማመጡ ተፈጥሯዊ ካልሆነ የፎቶውን ትክክለኛነት መጠርጠር ተገቢ ነው።

ከማይክሮፎን ፊት የተቀመጠ ሮቦት
የምስሉ መግለጫ,ሰው ሰራሽ አስተውሎት ከእውነተኛ ምሥሎች ባሻገርም ድምጽንም መፍጠር ይችላል

ሌላው ደግሞ ኤአይ ምስሎችን የሚያቀናብረው ኢንተርኔት ላይ ከሚሰበስባው ምሥሎች ስለሆነ በአንድ ሰው ምስል ላይ የተለያዩ የቆዳ ቀለም ያላቸው አካላትን ልንመለከት እንችላለን።

ፊቷ የጥቁር ሴት የሆነ ሴት ምስል ላይ እጆቿ፣ ጣቶቿ ወይም ሌላኛው የሰውነት ክፍሏ የተለየ የቆዳ ቀለም ሊኖረው ይችላል።

ሌላው ከግምት ውስጥ መግባት ያለበት ነገር የምሥል ጥራት ነው። የኤአይ ምሥሎች በጣም የጠሩ ናቸው። በምሥሉ ላይ የሚታዩት ሰዎች ፊት “እንደ መስተዋት ጥርት” ያለ፤ አካባቢውም እንከን የማይወጣለት ከመሰለ ፎቶ ተፈጥሯዊ ስለመሆኑ መጠርጠር ያስፈልጋል።

ሌላኛው የኤአይ ምሥል ሊለይ የሚችልበት መንገድ አብዛኛውን ጊዜ የኤአይ ምሥል ከጀርባ ያለውን ያደበዝዛል ወይም ውብ የሆነ ገጽታን ይሠጣል።

የሚመለከቱት ምሥል ትኩረቱ ጎልተው በወሰጡት ሰዎች ላይ ሆኖ ጀርባው እንዲደበዝዝ ተደርጓል?

ሌላኛው የኤአይ ምሥል ትክክለኛነትን ልናረጋግጥ የምንችልበት መንገድ ምሥሎቹን በሌላ የቴክኖሎጂ ውጤት መፈተሽ ነው።

በርካታ በኤአይ የተሠሩ ምሥሎችን የሚለዩ ድረ-ገጾች (ai image detector) ገጾች ስለሚገኙ የፎቶዎቹ መገኛ የሊንክ አድራሻን በማስገባት ወይም ፎቶግራፎቹን በመጫን ፍተሻ ማድረግ ይቻላል።