ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዳዲስ ዋና ስራ አስፈጻሚዎች

ከ 4 ሰአት በፊት

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመንግሥታዊዎቹ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዳዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችን ሹመት አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ሹመቶቹን በሙሉ ድምጽ ያጸደቀው ዛሬ ማክሰኞ ታኅሣሥ 9/ 2016 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ነው።

ለሁለቱ መንግሥታዊ የመገናኛ ብዙኃን በሥራ አስፈጻሚነት የተሾሙት አዲሶቹ ኃላፊዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በቅርበት የሠሩ ናቸው።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን ሰብሳቢ ሹመት ካጸደቀ በኋላ በመቀጠል የአዲሱን የአትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ሥራ አስፈጻሚ ሹመት አጽድቋል።

መንግሥታዊውን የብሮድካስቲንግ መገናኛ ብዙኃን (ኢቢሲ) እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ጌትነት ታደሰ ናቸው።

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የጋዜጠኝነት ሙያን የተቀላቀሉት አቶ ጌትነት ከኢቢሲ በፊት ሁለት የመገናኛ ብዙኃንን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት መርተዋል።

አቶ ጌትነት ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም. ለሁለት ዓመታት የዋልታ ሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽንን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ።

ከዚያም በመቀጠል አቶ ጌትነት ያመሩት በዋናነት አዲስ ዘመን እና ኢትዮጵያን ሄራልድ (Ethiopian Herald) ጋዜጦችን ወደ ሚያሳትመው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነው።

አዲሱ የኢቢሲ ተሿሚ የፕሬስ ድርጅትን ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት አምስት ዓመታት አስተዳድረዋል።

በአቶ ጌትነት የዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሥልጣን ዘመን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት 80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ከሁለት ዓመት በፊት ግንቦት ወር 2013 ዓ.ም. በደመቀ ሁኔታ አክብሯል።

የዚህ ክብረ በዓል አካል የሆኑ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕዮች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተካሂደዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ ክብረ በዓል ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሦስት ዓመታት የፓርላማ ንግግሮችን የያዘ መጽሐፍ “ዐሻራ” በሚል ርዕስ አሳትሟል።

አቶ ጌትነት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በታሪክ በዲፕሎማ፣ በጋዜጠኝነት እና በተግባቦት ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም በጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው።

እንደ አቶ ጌትነት ሁሉ ሌላኛው ተሿሚ አቶ መሳፍንት ተፈራም ሹመታቸው በምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል። አቶ መሳፍንት የተሾሙት አቶ ጌትነት ለአምስት ዓመታት የመሩትን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን እንዲያስተዳድሩ ነው።

በብሮድካስት ጋዜጠኝነት የተመረቁት አቶ መሳፍንት የመገናኛ ብዙኃን ዘርፉን ሲቀላቀሉ የመጀመሪያቸው ነው። ከዚህ በፊት በነበራቸው የሥራ ልምድ ያገለገሉት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሕዝብ ግንኙነት ውስጥ ነው።

አቶ መሳፍንት የሥራ ዓለሙን የተቀላቀሉት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በዘጋቢነት ነው። በዚህ መሥሪያ ቤት ለሁለት ዓመታት ቆይተው፤ በሳይንስ እና ኢንፎርሜሽን ማዕከል በእውቀት አስተዳደር ሥርጭት ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ እና ዳይሬክተርነት ሆነው ሠርተዋል።

አቶ መሳፍንት ከዚህ ኃላፊነት ቀጥሎ ያቀኑት ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ነው። እዚያም ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ኤክስፐርት ሆነው ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል።

አቶ መሳፍንት የዛሬው ሹመት እስከሚሰጣቸው ድረስ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ።