December 19, 2023 – Konjit Sitotaw 

ኢትዮጵያ ከዓለማቀፉ ገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ለመበደር ንግግር ላይ መኾኗን ከምንጮች መስማቱን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።

የአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያዎች፣ የውጭ ፋይናንስ ፍላጎት ማለትም አይ ኤም ኤፍ እና ሌሎች የልማት አጋሮች ሊሰጡ የሚችሉት ብድርና ድጋፍ ገና ውይይት እየተደረገባቸው መኾኑን ድርጅቱ መናገሩን ዜና ምንጩ አመልክቷል።

አገሪቱ፣ ከዓለም ባንክ ሌላ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ማግኘት እንደምትፈልግም ዘገባው ጠቅሷል።

መንግሥት ባለፈው ሳምንት ከዓለማቀፍ ቦንድ ገዢዎች ጋር ባካሄደው ስብሰባ፣ ከጥር እስከ መጋቢት ከአይ ኤም ኤፍ ጋር የብድር ስምምነት ላይ እደርሳለኹ ብሎ እንደሚያስብ ገልጧል ተብሏል።

ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ እስከ 2027/28 ዓ፣ም ድረስ 11 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የበጀት ክፍተት እንደሚኖርበት መስማቱንም ሮይተርስ ጠቅሷል።