December 19, 2023 – Konjit Sitotaw 

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሦስት ወረዳዎች ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያለ የሚጠራው አማጺ ቡድን በተመሳሳይ ሰዓት ጥቃቶችን ማድረሱን ዋዜማ በየሥፍራው ካሉ ምንጮቿ መረዳት ችላለች።

የቡድኑ ታጣቂዎች ካለፈው ቅዳሜ ከሌሊቱ 7:00 ሰዓት ጀምሮ ጥቃቶቹን የተፈጸሙት፣ በዋጫሌ ወረዳ ሙከጡሪ ከተማ፣ በደብረ ሊባኖስ ወረዳ ደብረጽጌ ከተማ እንዲኹም በያያ ጉለሌ ወረዳ ፊታል ከተማ እንደኾነ ምንጮች ተናግረዋል።

የጥቃቱ ዓላማ በዋናነት በየማረሚያ ቤቱ ያሉ የታጣቂ ቡድኑን አባላት ለማስፈታት ያለመ እንደነበር ዋዜማ ሰምታለች። ኾኖም የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ከቡድኑ ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ፣ የቡድኑ አባላት እስረኞቹን ማስፈታት ሳይችሉ እንደቀሩ ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ በደብረጽጌ ከተማ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍን በኃይል ሰብረው በመግባት ኮምፒውተሮችንና ሌሎች ንብረቶችን ማውደማቸውን የገለጡት ምንጮች፣ ኹለት የአዋሽ ባንክ የጥበቃ ሠራተኞችን ደሞ አፍነው መሠወራቸውን ጠቅሰዋል። በተኩስ ልውውጡ፣ በርካታ የታጣቂ ቡድኑ አባላት እንደተገደሉ ዋዜማ ከምንጮቿ ተረድታለች።