December 19, 2023 

ኢትዮጵያ እና ብድሮቿ የፈጠሩት ስጋት!

( ኤሊያስ መሰረት ) 

ኢትዮጵያ ምናልባትም በቅርብ ግዜ ታሪኳ ለመጀመርያ ግዜ የመክፈያ ግዜው የደረሰ የዩሮቦንድ ብድር ኩፖን ሳትከፍል ቀኑ አልፏል።

ይህ ባሳለፍነው ሳምንት ሰኞ እለት ክፍያው ይጠበቅ የነበረ የ33 ሚልዮን ዶላር ክፍያ (የዩሮቦንዱ አጠቃላይ መጠን 1 ቢልዮን ዶላር ነው) ሳይከፈል በመቅረቱ በአበዳሪዎች ዘንድ ግርምታን እና መበሳጨትን ያስከተለ ሲሆን ከሁሉም በላይ ግን “Fitch” የተባለው የብድር ደረጃ አስቀማጭ ድርጅት የሀገሪቱን ደረጃ ወደ “የማይረባ” ደረጃ ወይም CC አውርዶታል።

በዚህም ኢትዮጵያ በቅርብ አመታት ብድራቸውን መክፈል ካልቻሉ ሌሎች ሁለት የአፍሪካ ሀገራት፣ ማለትም ጋና እና ዛምቢያ ጋር ተመድባለች (አዎ፣ እነዚህን ትልልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን መረጃዎች ትልልቆቹ የመንግስት ሚድያዎች አይዘግቡም)።

ይህ ውጤቱ አስከፊ ሊሆን ይችላል፣ ምክንያቱም የብድር ከፋይ ደረጃው በዚህ ደረጃ ወረደ ማለት ከዚህ በኋላ አበዳሪ መንግስታትም ሆኑ ተቋማት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ እንደ ነዳጅ፣ ማዳበርያ፣ መድህኒት… ወዘተ ያሉትን ገዝቶ ለማስገባት እንኳን ብድር ሊፈቅዱ አይችሉም።

የኢትዮጵያ ፋይናንስ ሚኒስቴር ይህ የ33 ሚልዮን ዶላር ክፍያ ሊከፈል የሚችል ቢሆንም ሌሎች አበዳሪዎችንም እኩል ማየት ስላለበት ይህን ብቻ ከመክፈል እንደተቆጠበ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ብድሯን እየከፈለች እና ብድሯን እያሸጋሸገች እስከዚህኛው አመት ደርሳለች፣ ነገር ግን ባለፈው ሶስት አመት የተከሰቱ ሀገራዊ ውጥንቅጦች እና ጦርነቶች የብድር ሽግሽግ ሂደቱን እንዳሰናከሉት በተደጋጋሚ ይገለፃል።

ባለኝ መረጃ ኢትዮጵያ ከፓሪስ ክለብ ጨምሮ ከውጭ አበዳሪዎች 28.2 ቢልዮን ዶላር ብድር አለባት፣ ቻይና ደግሞ የዚህን 30 ፐርሰንት ገደማ ይዛለች። ከሀገር ውስጥ የቦንድ ሽያጮችም ከዚህ ያልተናነሰ ብድር ተከማችቷል፣ አጠቃላይ የብድር መጠኑ ወደ 57 ቢልዮን ዶላር ገደማ እንደሆነ አንድ የUNDP ጥናት ይጠቁማል።

ሬውተርስ ዛሬ እንዳስነበበን ሀገራችን ከአይ ኤም ኤፍ ተጨማሪ 3.5 ቢልዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ንግግር ጀምራለች። ይህ መጠን ሀገሪቱ በአንድ አመት ውስጥ እንድትበደር ከሚፈቀድላት በላይ ሲሆን የተለየ አስተያየት ተደርጎ ብድሩን እንድታገኝ ሀሳብ አቅርባለች። ከአለም ባንክም ተጨማሪ 3.5 ቢልዮን ዶላር ብድር ለማግኘት እቅድ ተይዟል።

ነገር ግን እነዚህ የብድር ጥያቄዎችም ሆኑ መጪ የበጀት ድጎማ እና የአንገብጋቢ የውጭ እቃዎች ግዢ እጣ ፈንታው አልታወቀም። በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እና የአምራች ኢንደስትሪ ዘርፍ መዳከም ለሚታይበት የሀገራችን ኢኮኖሚ ይህ የውጭ ብድር ጉዳይ አዲስ ሳንካ ሆኗል።

የሰሜኑ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት የደርግን አይነት “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” አካሄድ በስፋት ተንፀባርቋል፣ ጦርነቱ ቢልዮን ዶላሮችን ፈጅቷል፣ አሁን ድረስ ለጦርነት የሚውሉ ቁሶች ግዢ እየተጧጧፈ እንደሆነ በይፋ በመንግስት ይነገራል፣ አስፈላጊ ሲሆን ፕሮጀክቶችን በማጠፍ ጭምር ለጦርነት ዝግጅት ማድረጊያ ማድረግ እንደሚቻል በይፋ ተነግሯል።

እውነት ለመናገር እንደ ሀገር ሰከን ብለን ካለንበት እጅግ አሳዛኝ፣ አስደንጋጭ እና አታካች አዙሪት የምንወጣበት ጉዳይ ላይ ልንመክር ይገባል።

As a nation, we have to do some soul searching!  = ( ኤሊያስ መሰረት )