ኢትዮጵያዊቷ ተመራማሪ መለይ መኮንን (ዶ/ር)
የምስሉ መግለጫ,ኢትዮጵያዊቷ ተመራማሪ መለይ መኮንን (ዶ/ር)

ከ 6 ሰአት በፊት

በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት በዱባይ ያካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ በታዛቢነት የተሳተፉት ኢትዮጵያዊቷ ተመራማሪ መለይ መኮንን (ዶ/ር) ተወልደው ያደጉት መቀለ ውስጥ ነው።

ከኅዳር 20 እስከ ታኅሣሥ 2/2023 (እአአ) በዱባይ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ 200 የሚሆኑ አገራት፣ ተመራማሪዎች፣ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በኖርዌይ ዩኒቨርሲቲ ኦቭ ላይፍ ሳይንስ የእጽዋት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የአካባቢ ኢኮኖሚ ተመራማሪ የሆኑት መለይ መኮንን (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲውን ወክለው ከተሳተፉ የምርምር ታዛቢዎች መካከል አንዷ ናቸው።

መለይ (ዶ/ር)፣ በአየር ንብረት ላይ የሚሠሩት የምርምር ሥራ የሚጀምረው በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ በምትገኘው ወንዶ ገነት ከተማ በተማሩት የእጽዋት ትምህርት ነው።

በተመሳሳይ ጊዜ ኢኮኖሚክስ እያጠኑ ነበር።

ከዚያም በኖርዌይ የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝተው በዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥናት የሁለተኛ ዲግሪ ከተማሩ በኋላ ለሦስተኛ ዲግሪያቸው አስቀድመው የተማሯቸውን ትምህርቶች አጠቃሎ የሚይዝ የእጽዋትና የሃብት ኢኮኖሚክስ ላይ አተኮሩ።

ምሁሯ፣ እስካሁን ሲያካሂዷቸው በቆዩ ጥናቶች በተለይም ትኩረት ባደረጉባቸው ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገራት ውስጥ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ጋር ሠርተዋል።

መለይ መጀመሪያ ላይ ትኩረት ያደረጉት በትሮፒካል ደን ጥበቃ ላይ ነበር።

ነገር ግን መሬት ላይ መሥራት ሲጀምሩ በአተገባበር እና በሥነ ምግባር ዙሪያ ብዙ ክፍተቶች ያሏቸውን ነገሮች መታዘብ እንደጀመሩ ይናገራሉ።

ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2008 የበለጸጉ አገራት፣ በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት ውስጥ የሚያካሄዱትን የደን ጭፍጨፋ እንዲያቆሙ እና እንዲክሱ የሚለው ውሳኔ ከደን ጭፍጨፋ እና መበስበስ የሚመጣ ልቀትን ለመከላከል ያለመ ነው።

“የቀረበው ካሳ አንድ ቶን የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት ለሚቀንስ አምስት ዶላር ነው የሚል ነው ”ይላሉ ያለውን ኢፍትሃዊነት ሲያነሱ።

አክለውም “ይህ ብዙ የሥነ ምግባር ጥያቄዎችን እንዲነሳ ያደርጋል። ማለትም የካሳ ክፍያው እዚህ ግባ የሚባል ስላልሆነ ያደጉ አገራት የበካይ ጋዝ ልቀትን እንዲቀጥሉ እና ድሃ አገራት መኖር እንዲያቆሙ የሚያደርግ ዓይነት ነው።”

“በሁለተኛ ደረጃ ድርድሩ የሚካሄደው በአገር አቀፍ ደረጃ ነው፤ ይህ መሬት እንደሚወርድ ምንም ዋስትና የለውም። መሬት ደግሞ የመንግሥት ነው [ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ አንድ አይነት የመሬት ፖሊሲ አላቸው]። ስለዚህ መንግሥት ይህን አካባቢ ለካርቦን ፕሮጀክት እፈልገዋለሁ ካለ ሊያግደው ይችላል። ይህ ሲታይ ድሃውን መልሶ የሚያደኽይ ይመስላል። በዚህ ምክንያት ነው እዚያ ላይ ትኩረት ማድረግ የጀመርኩት” ሲሉ ያስረዳሉ።

ደቡብ ሱዳን በአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዱ የደሃ አገራት መካከል አንዷ ነች
የምስሉ መግለጫ,ደቡብ ሱዳን በአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዱ የደሃ አገራት መካከል አንዷ ነች

“መሪዎቻችን አቅም የላቸውም”

የመለይ የምርምር ሥራ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ውስጥ እንደ ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ እና ዛምቢያ ባሉ አገራት ላይ ያተኩራል።

በእነዚህ አገራት ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት እንደ የእንጨት ሥራ ውጤቶች ላይ የተመሠረተ ነው የሚሉት ምሁሯ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ውሳኔዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወሰኑ በመሆናቸው አንዳንዶቹ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች የሚፈጥሩት ግጭት እንደሚያሰጋቸው ይናገራሉ።

የዚህ ምክንያት ሲያስረዱ “በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት የመደራደር አቅም የሌላቸው፤ የቀረበውን ውሳኔ ተቀብለው የሚመለሱ” በመሆናቸው ነው ይላሉ።

“ስምምነት እና ተግባራዊነት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ብዙ የአፍሪካ መሪዎች ይህንን እንደ ትልቅ ጉዳይ ያዩታል፤ ይሁን እንጂ ትልቁ ጥያቄ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከፈለው ካሳ እየተጎዳ ላለው ሰው ይደርሰዋል ወይስ አይደርሰውም? የሚል ነው።”

የዘርፉ ተመራማሪዎች ተስፋ ካስቆረጣቸው ነገር አንዱ፣ የድርድሩ የአፈጻጸም ሂደት እንደሚጠብቁት የሚሄድ አለመሆኑ ነው። ምክንያቱም የተለያዩ አገራት የተለያየ ፖሊሲ ስላላቸው፣ ፍላጎታቸውን መሠረት አድርገው የሚከተሏቸው በመሆኑ ነው።

“በአየር ንብረት ላይ ስናተኩር ወደ ኢኮኖሚ ድርድር ውስጥ ይገባል፤ በተለይም የካርቦን (በካይ ጋዝ) ልቀት የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤ ስለሆነ፣ ይህም ከነዳጅ የሚመጣ ነው። ስለዚህ ይህን ማስቆም ማለት ኢኮኖሚያቸው በነዳጅ ላይ የተመሠረተ አገራትን የሚጎዳ ስለሆነ ትግበራው አዝጋሚ ይሆናል” ይላሉ ዶክተር መለይ።

መለይ በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ሲሳተፉ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፣ የዘንድሮው በአገራት መካከል የበለጠ ትብብር እና ተሳትፎ እንዳዩበት ይገልጻሉ።

“በመጀመሪያ ማድሪድ በተካሄደው ኮፕ25 ተሳትፌ ነበር። ያኔ ስለ አየር ንብረት እጽፋለሁ እንጂ ድርድሮች እንዴት ይካሄዳሉ የሚለውን አላውቅም ነበር። ሌሎች ‘በዚህ አንደራደርም፤ ይህ ነው የአገራችን ጥቅም ወይም ኢኮኖሚ’ እያሉ ቤቱን ዘግተው (እንደ ቻይና፣ ሕንድ. . .) ተደራደሩ።

“እኛ መሪዎች [የአፍሪካ] ወይም ባላደጉ አገራት ዝርዝር ውስጥ ሆነው የሚደራደሩት ግን ለምን ዓላማ እንደመጡ እንኳን የሚያውቁ አይመስለኝም – የመደራደር አቅም የላቸውም።”

በዚህ ምክንያት የተመለከቱት ሁኔታ አስደንጋጭ ነበር። ግብፅ ውስጥ በተካሄደው ኮፕ27 ላይ ደግሞ ለውጥ አይተዋል። ብዙ የአየር ንብረት ተቆርቋሪ ቡድኖች፣ ጉዳዩን በቁም ነገር የወሰዱ እና ለምን እንደመጡ የሚያውቁ ሁሉንም የሚሞግቱ ስለነበሩ ብዙ ለውጥ ማየታቸውን ይመሰክራሉ።

በሚቀጥሉት ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ ድሃ ሀገራት ካሳ እንደሚሰጥና እና ታዳሽ ካልሆኑ የኃይል ምንጮች (Fossil fuel ) ከመጠቀም ሽግግር እንደሚደረግ ይጠበቃል
የምስሉ መግለጫ,በሚቀጥሉት ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ ድሃ አገራት ካሳ እንደሚሰጥ እና ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል ምንጮችን ከመጠቀም ሽግግር እንደሚደረግ ይጠበቃል

የአየር ንብረት ለውጥ እና ሰላም

በኢትዮጵያ፣ በአጠቃላይ በምሥራቅ አፍሪካ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ ድርቅ እና ጎርፍ ሲከሰት ቆይቷል፤ እየተከሰተም ነው። መደበኛ ያልሆነ ዝናብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመፈናቀል እና ለረሃብ እየዳረገ ይገኛል።

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው የአየር ሙቀት መጨመር ደግሞ የከባድ ዝናብ መንስኤዎች ከሆኑት ውስጥ አንዱ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

እነዚህን ተጽእኖዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ስጋትን የመተንበይ አቅማቸው ውስን እንደሆነ የሚገልጹት ምሁሯ፣ በኢትዮጵያም ሆነ በአጠቃላይ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ ነገር ሰላም እና ደኅንነት እንዲኖር የማድረግ አስፈላጊነት ነው ይላሉ።

“ለምሳሌ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት ወይም ክልሎች ከተባበሩ የአንበጣ መንጋ በሚፈለፈልበት ላይ መቆጣጠር ይቻላል። ችግሩ ግን እ.ኤ.አ. በ2020 የአንበጣ መንጋ ከሳዑዲ አረቢያ እና ከየመን የሚነሳ ስለነበር ነው። የመን ጦርነት ላይ ነች፤ ኢትዮጵያ የራሷ ችግር ነበረባት። ስለዚህ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዘው ተፅዕኖ እየተባባሰ ይሄዳል። እኛ ማድረግ የምንችለው ሰላም እና ደኅንነትን ማስጠበቅ ብቻ ነው።”

የእነዚህ አደጋዎች ተጽእኖ ደግሞ በሴቶች፣ በሕጻናት እና በአረጋውያን ላይ የከፋ እንደሚሆን መለይ (ዶ/ር) ይጠቅሳሉ። ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የደን ቃጠሎ፣ ወረርሽኝ፣ ስደትን እና ሌሎች ቀውሶች የአየር ንብረት ለውጥ ይዟቸው ከሚመጣ ነገሮች መካከል እንደሆኑ ይጠቅሳሉ።

የወደፊት ዕጣ ፈንታችን ምን ይመስላል ካልን ግን የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ግልጽ አደጋ መገንዘብ እና ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።

“በ40 ዓመት አንዴ ይከሰት የነበረው የአንበጣ ወረራ አሁን ተደጋጋሚ እየሆነ ነው። ከዚያም ድርቅ መጣ፤ በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ፣ በኬንያ እና በኡጋንዳ እየጨመረ እንደሚሄድ ጥናቶች ያመለክታሉ። ስለዚህ ምንም ነገር ካላደረግን፥ የወደፊት ዕጣ ፈንታችን ጨለማ ይሆናል። የእኛን ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ልንቆጣጠረው አለመቻላችን ነው” በማለት ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

ኢትዮጵያዊቷ ተመራማሪ መለይ መኮንን (ዶ/ር)
የምስሉ መግለጫ,መለይ መኮንን (ዶ/ር) ዱባይ ላይ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ተሳታፊ በነበሩበት ጊዜ

ኢትዮጵያዊቷ ተመራማሪ በኮፕ 28 ላይ ምን ታዘቡ?

ዘንድሮው የተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ፣ ኮፕ 28፣ እስካሁን ከተካሄዱት ጉባኤዎች በተለየ መልኩ የአገራት መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው መዘዝ ላይ አወንታዊ ለውጥ ያመጣሉ የተባሉ ሁለት ዐበይት ስምምነቶች በማድረጋቸው ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት እንደሆነ ይነገራል።

በዚህም መሠረት በሚቀጥሉት ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ ድሃ አገራት ካሳ እንደሚሰጥ እና ታዳሽ ካልሆኑ የኃይል ምንጮች (ከሰል እና የከሰል ምርቶች፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ያልተጣራ ድፍድፍ ነዳጅ፣ የፔትሮሊየም ምርቶችን የመሳሰሉ) ከመጠቀም ሽግግር እንደሚደረግ ይጠበቃል።

“ልቀት የሚያስከትሉ በተለይ ያደጉ አገራት ናቸው፤ የአየር ንብረት ተጽእኖው የሚታየው በድሃ አገራት ላይ ነው – በአጠቃላይ በአፍሪካ። በአየር ንብረት ለውጡ ሳቢያ ሀብታቸውን እያጡ ያሉ ድሃ አገራት ካሳ ማግኘት አለባቸው የሚል ለረዥም ዓመታት ሲያከራክሩ ከቆዩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሆኖ፣ በጉባኤው የመጀመሪያ ቀን ልንክስ ግድ ነው ብለው ተስማምተዋል” ይላሉ ዶክተሯ።

ለአየር ንብረት ድንገተኛ አደጋዎች ተጠያቂ የሆኑት እጅግ የበለፀጉ አገራት እስካሁን ለደረሰው ኪሳራ እና ጉዳት ፈንድ (loss and damage fund) በድምሩ 700 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

ይኹን እንጂ ይህ በማደግ ላይ ያሉ አገራት በዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት ከደረሰባቸው የማይተካ ኢኮኖሚያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ኪሳራዎች ጋር ሲነጻጸር 0.2% ነው በማለት ባለሙያዎች በቂ እንዳልሆነ ይከራከራሉ።

መለይ (ዶ/ር) “ከችግሮቹ አንዱ የሚሰበሰበው ገንዘብ ከሚያስፈልገው ጋር የሚመጣጠን አይደለም፤ በተጨማሪም ገንዘቡን በመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት የዓለም ባንክ እንዲቆጣጠረው ነው የተወሰነው። ስለዚህ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት በዚህ አሠራር አልተስማሙም። አንዱ ምክንያት ገንዘቡ በቂ አለመሆኑ ነው፤ ሌላው ከባንኩ ጋር ያላቸው ልምድም ገለልተኝነት የጎደለው ነው” በሚል እንደሆነ ያብራራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ይህንን ገንዘብ የሚሰጡ አካላት የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን ስለሚያስቀምጡ፣ አገራቱ (በተለይን የአፍሪካ አገራት) አቅም ስለሌላቸው እንደ ሌሎቹ የአየር ንብረት ድጋፎች ይህንን ገንዘብ ለማግኘት ይቸገራሉ።

“ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ዛምቢያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሴራሊዮን፣ ካሜሩን፣ ጋና እና ቤኒንን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተወካዮችን አነጋግሬአለሁ፤ ተመሳሳይ ስጋት አላቸው” ይላሉ ተመራማሪዋ።

እስካሁን የተገቡት ቃል ኪዳኖች ከሚፈለገው አንፃር እጅግ በጣም አነስተኛ ሲሆን፣ በማደግ ላይ ያሉ አገራት የሚደርስባቸው ኪሳራ እና ጉዳት በዓመት ከ400 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚገመት እና እየጨመረ እንደሆነ ይገመታል።

ለጉዳት የሚያወጡት ዓመታዊ ወጪም ከ100 ቢሊዮን እስከ 580 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይጠቅሳሉ።

አስተናጋጇ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ እና ጀርመን እያንዳንዳቸው 100 ሚሊዮን ዶላር፣ ጣሊያን እና ፈረንሳይ 108 ሚሊዮን ዶላር የሰጡ ሲሆን፤ በታሪክ እጅግ የከፋ የበካይ ጋዝ ልቀት ያላት እና በዚህ ዓመት ደግሞ ትልቋ የነዳጅ እና ጋዝ አምራች የሆነችው አሜሪካ እስካሁን 17.5 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች።

አሜሪካን እና ቻይናን ተከትላ በሦስተኛ ደረጃ ትልቅ ኢኮኖሚ ያላት ጃፓን 10 ሚሊዮን ዶላር ሰጥታለች።

ሌላው እስካሁን በተካሄዱት የአየር ንብረት ጉዳይ (ኮፕ) ጉባኤዎች ላይ ተነስቶ የማያውቅ ግን በዚህ ዓመት ትልቅ እመርታ የተባለለት ከታዳሽ ኃይል ምንጮች ሽግግር እናድርግ የሚል ነው።

ይህ 21 ገጽ ያለው ስምምነት አገራት “በአግባቡ፣ ሥርዓቱን በጠበቀ መንገድ እና ፍትሃዊ በሆነ አግባብ” ከቅሪተ አካላት ነዳጅ የኃይል ምንጮች (fossil fuels) ሽግግር ያደርጋሉ ይላል።

በተጨማሪ ከአውሮፓውያኑ 2025 በፊት [በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ] የዓለምን ሙቀት የሚጨምሩ የጋዞች ልቀት ከፍተኛው ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል የሚለውም የሚያሳስብ ጉዳይ ነው።

በዚህ ደረጃ ስምምነት ላይ መደረሱ፣ የዓለም ሙቀት ጭማሪን በ1.5 ዲግሪ መገደብ አለብን የሚለውን “የፓሪስ ስምምነት” የሚደግፍ በመሆኑ ዐቢይ ጉዳይ እንደሆነ ዶክተር መለይ ያስረዳሉ።

ተግባራዊነቱ መቼ ይጀመራል ለሚል ጥያቄ “ግልጽ ቁርጠኝነት እና ግልጽ ማዕቀፍ አልተቀመጠም። ይህም ማለት ከፍተኛ ልቀት የሚያስከትሉ የኃይል ምንጮችን የሚያመርቱ እና የሚጠቀሙ አገራት እንደተለመደው የማይቀጥሉበት ምክንያት እንዳለ የሚያሳይ ነገር የለውም” ይላሉ።