
ከ 6 ሰአት በፊት
ፈረንሳይ ውስጥ 4.2 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጥንታዊ የአፍሪካ ጭምብልን በ150 ዩሮ ብቻ እንድንሸጥ ተጭበርብረናል በማለት ክስ የመሠረቱት አዛውንት ጥንዶች ክሳቸው በፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ።
ጥንዶቹ ከአንድ የምዕራብ አፍሪካ የቅኝ ግዛት አገረ ገዥ ቤት ያገኙትን ከጋቦን የመጣ ነው የተባለ ጭምብልን ነው ትክክለኛ ዋጋውን ሳይውቁ ለደላላው በጥቂት ገንዘብ የሸጡት።
ማዕከላዊ ፈረንሳይ የሚኖሩት በ80ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙት እነዚህ ከሳሽ የዕድሜ ባለፀጋ ጥንዶች ከግለሰቡ ጋር የተገናኙት ቤታቸውን እንዲያፀዳላቸው ከተስማሙ በኋላ ነበር።
ታዲያ ጥንዶቹ ሽያጩን ከፈጸሙ ከስድስት ወራት በኋላ ጭምብሉ ለጨረታ ቀርቦ አንድ በስም ያልተጠቀሰ ግለሰብ በ4.2 ሚሊዮን ዩሮ መግዛቱን ሲሰሙ ነበር ተጭበርብረናል ሲሉ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱት።
ክሳቸውን የተመለከቱት ዳኛ ግን ጥንዶቹ በእጃቸው የነበረን የጥበብ ሥራ ትክክለኛ ዋጋ ማወቅ ተስኗቸዋል ብለዋል። ዳኛው ጨምረውም በእጃቸው የነበረን የጥበብ ሥራ ትክክለኛ ዋጋ ለማጣራት ምንም ዓይነት ጥረት አላደረጉም በሚል ክሳቸውን ውድቅ አድርገዋል።
- አፄ ኃይለ ሥላሴን የሚዘክር ዝግጅት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ተካሄደ30 ጥቅምት 2023
- የናፖሊዮን ቦናፓርት ባርኔጣ እስከ 800 ሺህ ዩሮ በሚገመት ዋጋ በጨረታ ሊሸጥ ነው19 ህዳር 2023
- ቱርክን ወደ ኦቶማን ዘመን ዝናዋ ለመመለስ የሚጥሩት ኤርዶዋን ምን እያደረጉ ነው?7 ህዳር 2023
የታሪክ አዋቂዎች ይህ ንጋሊ የተባለው ጭምብል በጋቦን ፋንግ በተባለ ጎሳ አባላት መሠራቱን እና ተመሳሳይ የሆኑ ጭምብሎች በቁጥር ከ10 እንደማይበልጡ ይነገራል።
ከጥንዶቹ የአንዳቸው አያት የነበሩት ሬኔ-ቪክተር ፎርኒዬ የተሰኙ አስተዳደሪ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በምዕራብ አፍሪካ ቅኝ ገዢ ሆነው ባገለገሉበት አጋጣሚ ጭምብሉን ወደ ፈረንሳይ ይዘው ሳይመጡ አቀይርም የሚል ግምት አለ።
ጥንዶቹ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዘው ከመሄዳቸው በፊት በውድ ዋጋ የተሸጠውን ጭምብል በ150 ዶላር የገዛው ደላላ ለጥንዶቹ 300 ሺህ ዩሮ ሊሰጣቸው ተስማምቶ ነበር።
ይሁን እንጂ ጥንዶቹ ክስ ከመሠረቱ በኋላ 300 ሺህ ዩሮ ጉርሻ ለመስጠት ያቀረበውን ሃሳብ ትቶታል።
በሌላ በኩል ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋቦን ጭምብሉ ከአገሪቱ ተዘርፎ የወጣ በመሆኑ የጭምብሉ ባለቤት መሆኗን እና እንዲመለስላት ጥያቄ አቅርባ ነበር።
ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ ብይን የሰጡት ዳኛ የጋቦንን የይገባኛል ጥያቄንም ውድቅ አድርገውታል።
ፈረንሳይ 90 ሺህ ገደማ ከአፍሪካ በተለይ ደግሞ ከሰሃራ በታች አፍሪካ አገራት የተወሰዱ ጥንታዊ ቅርሶች በእጇ ይገኛሉ።