የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎደሚር ዜሌንስኪ
የምስሉ መግለጫ,የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎደሚር ዜሌንስኪ

ከ 4 ሰአት በፊት

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ የአገሪቱ ጦር አመራሮች ግማሽ ሚሊዮን ተጨማሪ የሠራዊት አባላት እንዲጨመር መጠየቃቸውን ገለጹ።

በኪዬቭ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፕሬዝዳንቱ ሁለት ዓመት ሊደፍን የተቃረበውን ጦርነት እየመሩ ካሉ ጦር አዛዦች “ከ450 እስከ 500 ሺህ ሰዎችን” እንደሚፈልጉ ጥያቄ አቅርበዋል ብለዋል።

ዜሌንስኪ የአውሮፓውያኑ ዓመት ማብቂያን ምክንያት በማድረግ በሰጡት መግለጫ ላይ በአሁኑ ወቅት ከሩሲያ ጦር ጋር እየተዋጉ ያሉ ግማሽ ሚሊዮን ወታደሮች መኖራቸውን ተናግረው፤ ተጨማሪ 500 ሺህ ወታደሮችን የመመልመል ጥያቄ ከማጽደቃቸው በፊት ተጨማሪ መረጃ እንዲቀርብላቸው ማዘዛቸውን ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ ተጨማሪ የወታደር ምልመላ ጥያቄ የቀረበላቸው ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ኅብረት የጠየቁት ወታደራዊ ድጋፍ በዘገየበት ወቅት ነው።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አሜሪካ ለዩክሬን ለመስጠት ያቀደችው 60 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ በሪፐብሊካኖች አማካይነት ኮንግረሱ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

የዋይት ሐውስ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች አሜሪካ ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ለዩክሬን ለመስጠት ያቀደች ቢሆንም ያለ ኮንግረሱ ፍቃድ ድጋፍ ለዩክሬን መላክ አንችልም ብለዋል።

ከአሜሪካ ወታደራዊ እርዳታ በተጨማሪ የአውሮፓ ኅብረት ለዩክሬን ሊልክ የነበረው የ50 ቢሊዮን ዩሮ የፋይናንስ ድጋፍ በሃንጋሪ ምክንያት ታግዷል።

ሃንጋሪ የ50 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ማስቆሟን አስመልክተው አስተያየት የሰጡት የኔዘርላንድስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩት “አሁንም ጊዜ አለን፤ በሚቀጥሉት ሳምንታት እንነጋገርበታለን። ዩክሬን እርዳታውን አታገኝም ማለት አይደለም” ብለዋል።

ከሩሲያ የተቃጣባትን ወረራ ለመቀልበስ በአውሮፓ እና አሜሪካ እርዳታ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ ሆና የቆየችው ዩክሬን በአሁኑ ወቅት የተተኳሽ እጥረት እንዳጋጠማት እየተዘገበ ይገኛል።

ኪዬቭ ከወራት በፊት የጀመረችው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ስኬታማ ሳይሆን የቀረ ሲሆን፣ በቅርቡም በሩሲያ ሙሉ በሙሉ የወታደራዊ ኃይል የበላይነት ሊወሰድባት ይችላል።

የዩክሬን ቀዳማዊት እመቤት ኦሌና ዜሌንስኩ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ አገራቸው ከምዕራባውያን አገራት የምታገኘው ወታደራዊ እና የፋይናንስ ድጋፍ የሚቋረጥ ከሆነ ዩክሬናውያን የመሞት አደጋ ታጋርጦባቸዋል ሲሉ ተናግረው ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦራቸው ዓላማውን ሳያሳክ በዩክሬን የተጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ እንደማይጠናቀቅ ተናግረዋል።

ፑቲን “በዩክሬን እየተካሄድ ስላለው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ሲናገሩ የሩሲያ ሉዓላዊነት መረጋገጥ አለበት ብለዋል። “አገራችን ሉዓላዊነቷ ሳይረጋገጥ ልትኖር አትችልም። ፈጽሞ አትኖርም” ብለዋል።

ፑቲን በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ሩሲያ በዩክሬን እየተዋጉ ያሉ 617 ሺህ ወታደሮች እንዳሏት እና አስፈላጊ ከሆነ 800 ሺህ ተጨማሪ ወታደሮችን ለማሰማራት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንቱ የአገራቸው አየር ኃይል የአየር መቃወሚያ ሥርዓት ችግር እንደገጠው እና የሰው አልባ አውሮፕላኖች ምርት ሂደትን መጨመር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።