
ከ 6 ሰአት በፊት
የየመን ሁቲ አማጺያን በቀይ ባሕር ላይ የሚያልፉ ዕቃ ጫኝ መርከቦችን በሚሳኤል እና በድሮን ዒላማ ማድረጋቸው የነዳጅ እና የሌሎች ምርቶችን ዋጋ ከፍ ያደርጋል ተባለ።
ሰፊ የየመን ግዛትን ተቆጣጥረው የሚገኙት ሁቲ አማጺያን ከእስራኤል እና ከሐማስ ጦርነት መቀስቀስ ወዲህ በቀይ ባሕር በኩል በሚያልፉ ግዙፍ የጭነት መርከቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
አማጺያኑ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ለገባው ሐማስ ያላቸውን ድጋፍ በይፋ ከገለጹ በኋላ፣ በቀይ ባሕር በኩል አድርገው ወደ እስራኤል የሚያቀኑ መርከቦችን ዒላማ እንደሚያደርጉ በይፋ አሳውቀዋል።
የሁቲ አማጺያን ባለፉት ሳምንታት ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ነዳጅ እና የተለያዩ ምርቶችን ጭነው የሚንቀሳቀሱ ግዙፍ መርከቦችን በሚሳኤል እና በድሮን ሲያጠቁ እና አገታ ሲፈጽሙ ነበር።
ታዲያ ይህ ስጋት ውስጥ የከተታቸው የዓለማችን ዋነኛ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅቶች ቀይ ባሕርን ከመጠቀም ይልቅ ረዥም ጊዜ እና ብዙ ነዳጅ አባክነው በደቡብ አፍሪካ በኩል አድርገው ወደ መዳረሻቸው እያቀኑ ነው።
ተንታኞች ታዲያ ይህ በሁቲ አማጺያን በቀይ ባሕር ላይ የተፈጠረው የደኅንነት ስጋት በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ እና በሌሎች ምርቶች ዝውውር ላይ ጫናን በመፍጠር የዋጋ ጨማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከትናንት በሰቲያ ሰኞ በነዳጅ ዋጋ ላይ አነስተኛ ሊባል የሚችል የ1 በመቶ ጭማሪ የተመዘገበ ሲሆን፣ አሁን ላይ 78 ዶላር እየተሸጠ በሚገኘው አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ የሚቀር አይመስልም።
- ግዙፉ ነዳጅ አምራች ኩባንያ በቀይ ባሕር በኩል ነዳጅ ማመላለስ አቋረጠ18 ታህሳስ 2023
- በመርከቦች ላይ በቀጠለው ጥቃት ግዙፉ የመርከብ ጭነት አጓጓዥ በቀይ ባሕር በኩል ማለፍ አቆመ15 ታህሳስ 2023
- የዩኬ ባሕር ኃይል በቀይ ባሕር አካባቢ የሁቲ ድሮን ተኩሶ ጣለ17 ታህሳስ 2023
በመርከብ የንግድ ሥራ ላይ ዘገባዎችን የሚሰራው ሎይድስ ሊስት ጋዜጣ ዋና አርታኢ የሆኑት ሪቻርድ ሜድ የንግድ መርከቦች የጉዞ አቅጣጫቸውን መቀየራቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ፣ በዓለም አቀፍ የምርት አቅርቦት ስንሰለት ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ስለሚያስከትል በዋጋ ላይ የሚመጣው ጭማሪ ቀላል አይሆንም ይላሉ።
ሪቻርድ ሜድ በየዓመቱ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ምርት የሚመላለስበት የቀይ ባሕር መስመር ከአገልግሎት ውጪ መሆን የሚያስከትለው ጭማሪ በነዳጅ ዋጋ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር እንዳልሆነ ያሳስባሉ።
ከቀናት በፊት ኤቨርግሪን ላይን እና ሜርስክ የተባሉት የዓለማችን ግዙፍ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅቶች እና ብሪቲሽ ፔትሮሊየም (ቢፒ) የተባለው የነዳጅ አምራች ኩባንያ በደኅንነት ስጋት ምክንያት በቀይ ባሕር በኩል ጉዞ እንደማያደርጉ አሳውቀዋል።
የጋዜጣው ዋና አርታይ ታዲያ “የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችን፣ አልባሳትን፣ የፍጆታ ዕቃዎችን. . . የሚጭኑት ግዙፍ ኮንቴይነር ተሸካሚ መርከቦች ናቸው የጉዞ አቅጣጫ እየቀየሩ ያሉት” በማለት የዋጋ ጭማሪው ከነዳጅ በተጨማሪ በሌሎች ቁሶች ላይ ሊከሰት እንደሚችል ይገልጻሉ።
የኤክስፖርት ኤንድ ኢንተርናሽናል ትሬድ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ማርኮ ፎርጂኦና ደግሞ መርከቦች አቅጣጫ እንዲቀይሩ መገደዳቸው ከምርት ዋጋ በተጨማሪ የመርኮችን የነዳጅ እና የመድን ወጪን ይጨምራል ይላሉ።
ይህም ብቻ አይደለም መርከቦች አቅጣጫቸውን ወደ አንድ ወደብ ወይም መተላለፊያ የሚያዞሩ ከሆነ በወደቦች መጨናነቅ እና መዘግየት ሊፈጥር ይችላል።
ይህ የነዳጅ እና የሌሎች ምርቶች ዋጋ ጭማሪ በኮቪድ እና በተለያዩ ጦርነቶች ጫና በደረሰባቸው የአገራት ምጣኔ ሀብት ላይ ሌላ ዙር የዋጋ ንረትን ያስከትላል።

ቀይ ባሕር እና የዓለም ንግድ
ቀይ ባሕር ወደ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ሰሜን እና ምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም ወደ እስያ ለሚላኩ ምርቶች ቁልፍ መተላለፊያ ነው።
በሰሜን በኩል የግብፁን ሱይዝ ካናል እንዲሁም በደቡብ አቅጣጫ ጂቡቲ፣ የመን እና ኤርትራን በሚያዋስነው የባብ አል-ማንዳብ መካከል የሚገኘው ቀይ ባሕር የዓለማችን 12 በመቶ ወይም አንድ ትሪሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ምርት በየዓመቱ የሚተላለፍበት የውሃ ክፍል ነው።
የፋይናንስ መረጃዎችን በመተንተን ትልቅ ስም ያለው ኤስ አንድ ፒ ግሎባል ማርኬት ኢንተለጀንስ በቅርቡ የሠራው የገበያ ጥናት እንዳሳየው አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ወደ አገር ውስጥ ካስገቧቸው ምርቶች 15 በመቶ ያክሉ ከእስያ እና ከባሕረ ሰላጤው አገራት በቀይ ባሕር በኩል ያለፈ ነው።
ቀይ ባሕር ከፍጆታ ዕቃዎች በተጨማሪ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ እና ጋዝ ምርት መተላለፊያ ነው።
የኤስ ኤንድ ፒ ግሎባል ማርኬት ኢንተለጀንስ ትንተና እንደሚያሳየው፣ ምንም እንኳ አሁን የተከሰተው መስተጓጎል ከፍተኛ የንግድ መርከብ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ወቅት ባይሆንም ጉልህ ተጽእኖ የሚያርፈው በፍጆታ ዕቃዎች ላይ እንደሚሆን አሳይቷል።

የግብፅ ራስ ምታት
ቀይ ባሕር ላይ የተፈጠረው የደኅንነት እጦት ብዙ ካከሰራቸው አገራት መካከል ቀዳሚዋ ግብፅ ናት።
መርኮቦች ወደ የቀይ ባሕር የውሃ ክልል የሚገቡት ወይም የሚወጡት የሱይዝ ካናል መተላለፊያ ቦይን ተጠቅመው ነው።
ግብፅ በዚህ ሰው ሰራሽ በሆነው መተላለፊያ ከሚያልፉ መርከቦች ከፍተኛ ገንዘብ ትሰበስባለች። ሱይዝ ካናል ከግብፅ ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ መንገዶች መካከል አንዱ ነው።
የቻይና ዜና ወኪል ዢንዋ የግብፅ የሱይዝ ካናል አመራሮች ጠቅሶ እንደዘገበው ግብፅ በአውሮፓውያኑ 2022-23 የበጀት ዓመት ከመተላለፊያው 9.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢን ማግኘት ችላለች።
በተጠቀሰወ ጊዜ ውስጥም 1.5 ቢሊዮን ቶን ጭነት የያዙ 25 ሺህ 887 መርከቦች በሱዩዝ ካናል በኩል አልፈው ነው።
በቀይ ባሕር በሚተላለፉ መርከቦች ላይ የሁቲ ታጣቂዎች የደቀኑት ስጋት መንገዳቸውን እንዲቀይሩ በማድረጉ ገቢዋ አደጋ ላይ የወደቀው የግብፅ ባለሥልጣናት ሁኔታው እንዳሳሰባቸው እና በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን ገልጸዋል።
የሱዩዝ ካናል ባለሥልጣን ዋና ሰብሳቢ ኦሳማ ራቢ ከሁለት ቀናት በፊት ባወጡት መግለጫ ከኅዳር 9/2016 ዓ.ም. ወዲህ 55 መርከቦች የጉዞ አቅጣጫቸውን ቀይረዋል ስለማለታቸው ሮይተር የዜና ወኪል ዘግቧል።
አንዳንድ ሪፖርቶች ግብፅ በሱዩዝ ካናል በኩል ከሚያልፉ መርከቦች በአማካይ 250 ሺህ ዶላር እንደምታስከፍል ይጠቁማሉ።

የአማጺያኑን ጥቃት መቀልበስ ለምን አዳገተ?
ምዕራባውያን ግዙፍ መርከቦቻቸው በሚቀዝፉበት ቀይ ባሕር ላይ የጦር መርከቦቻቸው ይገኛሉ። በርካቶቹም ለባብ አል-ማንደብ ቅርብ በሆነችው ጂቡቲ ውስጥ ጦር ሠፈር እና ወታደሮቻቸው ይገኛሉ።
ታዲያ ይህን በዓለም የንግድ ሰንሰላት ላይ ስጋት የደቀነውን የየመን ሁቲ አማጺያን ጥቃትን ማስቆም ለምን ከባድ ሆነባቸው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።
በሰሜን ካሮላይና ክምፕቤል ዩኒቨርሲቲ የባሕር ኃይል ታሪክ መምህር የሆኑት ሳል ሜርኮጂሊያኖ የሁቲ አማጺያንን ጥቃትን መከላከል ከባድ ያደረገው አማጺያኑ የሚተኩሱት ተወንጫፊ ሚሳኤል በመሆኑ ነው ይላሉ።
“ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን መካላከል በጣም ከባድ ነው። በታሪክ መርከቦች በባሊስቲክ ሚሳኤል ዒላማ ሲደረጉ ስንመለከት ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።”
መምህሩ ጨምረውም ባሊስቲክ ሚሳኤሎች ዒላማቸውን ከመምታታቸው በፊት አየር ላይ እንዳሉ መትቶ የመጣል ወታደራዊ አቅም ያላቸውም በጣም ውስን መርከቦች ብቻ ናቸው ይላሉ።

የሁቲ አማጺያን ሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላን እየተጠቀሙ ደኅንነቱን ያራቁበትን የቀይ ባሕርን ሰላም መልሶ ለማረጋገጥ አሜሪካ ቆርጫለሁ እያለች ነው።
አሜሪካ መስተጓጎሉን ለመቅረፍ እና በቀይ ባሕር ላይ የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን ለመጠበቅ ከሌሎች አገራት ጋር በመጣመር ዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ዘመቻ ጀምራለች።
ይህን ጥምረት እንደ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ባሕሬን፣ ኖርዌይ እና ስፔንን የመሳሰሉ አገራት ተቀላቅለዋል።
በጉዳዩ ላይ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ከ40 በላይ ከሚሆኑ አገራት ከተወጣጡ ሚኒስትሮች ጋር በነበራቸው ውይይት ሌሎች አገራት ለደኅንነት ሥራው የበኩላቸውን አንዲያዋጡ ጠይቀዋል።
“ግድየለሽ የሆነው የሁቲ አማጺያን ጥቃት ጠንካራ ዓለም አቀፍ ምላሽን የሚፈልግ ከባድ ዓለም አቀፍ ችግር ነው” ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስቴር የሚሳኤል ጥቃቶችን ማክሸፍ የሚችለው ግዙፍ የጦር መርከብ ዓለም አቀፍ ጥረቱን እንደሚቀላቀል አስታውቋል።
ምዕራባውያኑ የቀይ ባሕር ደኅንነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ አቋማቸውን ቢያሳዩም አጓጓዦች ግን አሁንም ደኅንነት አይሰማንም በማለት ጊዜ እና ነዳጅ የሚጨርሰውን ረጅሙን የሕንድ ውቅያኖስ መስመርን እንደመረጡ ናቸው።
ሜርስክ ወደ ቀይ ባሕር መቼ እንደምመለስ አሁን ላይ አላውቅም ብሏል።
ግዙፉ የዴንማርክ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅት ሜርስክ የቀይ ባሕር ደኅንነትን ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ጥረቶች መጀመራቸው እጅግ የሚበረታት ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ መርከቦቹ ወደ ቀይ ባሕር መቼ እንደሚመለሱ ለመወሰን ከባድ ነው ብሏል።
ግዙፎቹ የመርከብ ጭነት አጓጓዦች ቀይ ባሕርን ትተው በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል በመጓዛቸው ለተጨማሪ 10 ቀናት 6 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠበቅባቸዋል።