
ከ 5 ሰአት በፊት
በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ስምምነት ያለውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ግብፅ የውሃ ድርሻዋን እና ብሔራዊ ደኅንነቷን “አስጠብቃለሁ” አለች።
ባለፉት ቀናት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በአዲስ አበባ ሲያደርጉት የነበረው የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ኢትዮጵያ እና ግብፅ አስታውቀዋል።
ለድርድሩ አለመሳካት ኢትዮጵያ እና ግብፅ አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ አድርገዋል።
ሦስቱ አገራት በሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል እንዲሁም ዓመታዊ የሥራ ሂደትን የተመለከተ መመሪያ ላይ ድርድር ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ይኹን እንጂ በአራት ዙር ሲካሄድ የቆየው “የመጨረሻ” ድርድር በአገራቱ መካከል ባሉ መሠረታዊ ልዩነቶች ምክንያት ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በድርድሩ ወቅት ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰቧን በመያዟ ስምምነት እንዳይደረስ እክል ሆናለች ብሏል።
የግብፅ የውሃ ሃብት እና መስኖ ሚኒስቴር በበኩሉ ኢትዮጵያ የሦስቱንም አገራት ጥቅም ሊያስጠብቅ እና ሊያስማማ የሚችል የሕግም ሆነ የቴክኒክ መፍትሄዎችን ለመቀበል ዝግጁ አይደለችም ብሏል።
አራተኛው ዙር የመጨረሻው ድርድርም በአዲስ አበባ ባለፉት ሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውሶ፣ በድርድሮቹ ላይ ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር በግድቡ ግንባታ፣ ውሃ አሞላል እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ያሏትን መሠረታዊ ልዩነቶችን ለመፍታት ጥረት አድርጋለች ብሏል።
ይኹን እንጂ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር አሞላል እና ዓመታዊ የሥራ ሂደትን የተመለከተ መመሪያ እና ደንቦች ላይ ሲደረግ የነበረው ድርድር ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን አቋሟን በመያዟ ስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት ሆኗል ብሏል።
- ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ከ5 ሺህ በላይ ግጭቶች መከሰታቸውን ጥናት አመለከተከ 6 ሰአት በፊት
- በቀይ ባሕር ላይ የተፈጠረው የደኅንነት ስጋት እና በዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ የደቀነው ጫናከ 6 ሰአት በፊት
- “መሪዎቻችን በአየር ንብረት ላይ ለመደራደር አቅም የላቸውም” ኢትዮጵያዊቷ የአየር ንብረት ተመራማሪከ 6 ሰአት በፊት

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ በፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መርኅ ላይ በመመሥረት የዜጎችን ፍላጎት ለማሟላት የምታደርገውን ጥረት እንደምትቀጥል ማሳወቅ ትፈልጋለች” ብሏል።
ግብፅ በበኩሏ “የግድቡን አሞላል እና ኦፕሬሽን በቅርበት በመከታተል መብቴን አስከብራለሁ” ስትል ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥታለች።
የግብፅ የውሃ ሃብት እና መስኖ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በግድቡ ምክንያት “ግብፅ የትኛውም አይነት ጉዳት ቢደርስባት በዓለም አቀፍ ቻርተሮች እና ስምምነቶች መሠረት የውሃ ድርሻዋን እና ብሔራዊ ደኅንነቷን የመጠበቅ መብቷ የተጠበቀ ነው” ብሏል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ይህ ግብፅ ከድርድሩ መጠናቀቅ በኋላ ያወጣችው መግለጫ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር እና የአፍሪካ ኅብረት ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌን የሚጻረር ነው በማለት መግለጫውን እንደማትቀበለው አስታውቃለች።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር ሲያነጋግራት ቆይቷል።
ኢትዮጵያ ሦስቱ አገራት በአባይ ወንዝ ላይ ባላቸው የውሃ ድርሻ ላይ መስማማት ከቻሉ ከሕዳሴ ግድብ የሚለቀቀውን የውሃ መጠን በተመለከተ አሳሪ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻልም አቋሟን ስትገልጽ ቆይታለች።
ግብፅ በበኩሏ የግድቡ ግንባታ ከአባይ ወንዝ የማገኘው የውሃ መጠን አቅርቦት ላይ አደጋ የጋረጠ እንዲሁም የታችኛውን ተፋሰስ አገራት ችላ ያለ ነው ስትል ቅሬታዋን አቅርባለች።
በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ሕጋዊ እና አስገዳጅ የሦስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ግብፅ ስትወተውት መቆየቷ ይታወሳል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ እስካለፈው ዓመት ድረስ ለአራት ዙር ግድቡን በውሃ የሞላች ሲሆን፣ ግንባታ ከ90 በማቶ በላይ የደረሰው የግድቡ ሁለት ተርባይኖችን በመጠቀም ኃይል ማመንጨት ከጀመረ አንድ ዓመት አልፎታል።