
ከ 1 ሰአት በፊት
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካዋ ኮሎራዶ ግዛት በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳይሳተፉ በግዛቱ ፍርድ ቤት ታገዱ።
የግዛቱ ፍርድ ቤት ዳኞች ፕሬዝዳንቱ ከሦስት ዓመታት በፊት በተከሰተው በካፒቶል ሂል አመጽ ተሳትፈዋል በሚል ነው 3 ለ 2 በሆነ ድምጽ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት በምርጫ ከመሳተፍ ያገዷቸው።
ይህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በ2024 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ሆኖ ለመቅረብ ያቀዱትን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሙሉ በሙሉ ከተወዳዳሪነት የሚያግድ ባይሆንም በኮሎራዶ እንዳይወዳደሩ በማገድ ለተቀናቃኞቻቸው የተሻለ የማሸነፍ ዕድልን ይሰጣል።
የትራምፕ ጠበቆች የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጥብቀው ተችተው፣ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንወስደዋለን ብለዋል።
የኮሎራዶ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ዶናልድ ትራምፕ ከካፒቶል ሂል አመጽ በፊት “ለደጋፊዎቻቸው የትግል ጥሪ አስተላልፈዋል . . . ደጋፊዎቻቸውም ለዚህ ጥሪ ምላሽ ሰጥተዋል” በማለት ትራምፕ በአመጹ በቀጥታ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
የትራምፕ ጠበቆች ግን ፕሬዝዳንቱ በአመጹ በቀጥታ አልተሳተፉም በማለት ሲከራከሩ ቆይተዋል።
- ግብፅ ድርድሩ ያለ ስምምነት ከተበተነ በኋላ “የውሃ ደርሻዬን” አስጠብቃለሁ አለችከ 5 ሰአት በፊት
- ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ከ5 ሺህ በላይ ግጭቶች መከሰታቸውን ጥናት አመለከተከ 6 ሰአት በፊት
- የአፍሪካ ልማት ባንክ ዓለም አቀፍ ሠራተኞቹን ከኢትዮጵያ ሊያስወጣ መሆኑ ተነገረከ 5 ሰአት በፊት
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ትራምፕን በኒው ሃምፕሻየር፣ በሚኒሶታ እንዲሁም ሚሺጋን ግዛቶች በምርጫ እንዳይወዳደሩ ለማገድ የተደረጉ ጥረቶች ሳይሰምሩ ቀርተዋል።
የትራምፕ ቃል አቀባይ ስቲቭን ቼኡንግ የኮሎራዶ ግዛት ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ውሳኔ “ሙሉ በሙሉ ጉድለት ያለበት ነው” ያሉ ሲሆን ውሳኔውን የሰጡ በዴሞክራቶች የተወከሉትን ዳኞች ወቅሰዋል።
በኮሎራዶም ሆነ ከዚህ ቀደም ትራምፕ በቀጣይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳይሳተፉ ለማገድ ጥረት በተደረገባቸው ኒው ሃምፕሻየር፣ ሚኒሶታ እና ሚሺጋን ግዛቶች እአአ 2020 በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ የነበሩት ጆ ባይደን ናቸው።
የትራምፕ ቃል አቀባይ በኮሎራዶ የተላለፈውን እግድ በተመለከተ ወግ አጥባቂ ዳኞች ለሚበዙበት የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።
ይህ የኮሎራዶ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ የሪፐብሊካን ፓርቲ የምክር ቤት ተወካዮችን አላስደስተም።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ማይክ ጆንሰን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ “ወገንተኝነት የታየበት ጥቃት ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትናንት ማክሰኞ በአይዎ ግዛት የምርጫ ቅስቀሳ ቢያደርጉም፣ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በተመለከተ ያሉት ነገር የለም።
ይሁን እንጂ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናቸው ለደጋፊዎች በላከው የኢሜይል መልዕክት ላይ “አምባገነኖች የሚፈጠሩት በዚህ መልኩ ነው” ብሏል።
ትራምፕ በአሁኑ ወቅት አራት የወንጀል ክሶች ተመስርቶባቸው ይገኛሉ። ትራምፕ በኒው ዮርክ ግዛት ከግብር ማጭበርበር ጋር የተያያዘ የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
እንዲሁም በጆርጂያ ግዛት የምርጫ ውጤት ለማስቀየር ጫና አሳድረዋል የሚል ሌላ የወንጀል ክስ በግዛት ደረጃ ተከፍቶባቸዋል።
በፌደራል ደረጃ ደግሞ ከምሥጢራዊ ሰነዶች አያያዝ ጋር በተገናኘ ክስ እንዲሁም በምርጫ ውጤት ጣልቃ በመግባት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዳይኖር አድርገዋል የሚል ክስም ቀርቦባቸዋል።