ዶ/ር አኪንውሚ አዴሲና
የምስሉ መግለጫ,የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አኪንውሚ አዴሲና

20 ታህሳስ 2023, 16:20 EAT

የአፍሪካ ልማት ባንክ ሠራተኞቹን ለእስር እና ጥቃት የዳረገው ክስተት “ሙሉ በሙሉ” የማይፈታ ከሆነ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት ላይ “አሉታዊ” ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል አስጠነቀቀ። የኢትዮጵያ መንግሥት የባንኩን ሠራተኞች እስርን አስመልክቶ ስላካሄደው ምርመራ መረጃ እንዳላቀረበለትም ባንኩ አስታውቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም አህጉራዊው የገንዘብ ተቋም በኢትዮጵያ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ሠራተኞቹን “በአስቸኳይ” ከአገሪቱ ሊያስወጣ መሆኑን ዛሬ ረቡዕ ታኅሣሥ 19/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ከአንድ ወር በፊት ባወጣው መግለጫ ሁለት ሠራተኞቹ በአዲስ አበባ ከተማ “ከሕግ ውጪ” በፀጥታ አካላት ታስረው እንደነበር እና አካላዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው አስታውቆ ነበር። ባንኩ በጥቅምት ወር ላይ የተፈጠረውን ይህንን ክስተት “የዲፕሎማሲያዊ መብት ጥሰት” እንደሆነ ገልጾ ነበር።

የባንኩ ዓለም አቀፍ ሠራተኞች ለሰዓታት በእስር ከቆዩ በኋላ የተፈቱት ባንኩ ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካሳወቀ በኋላ መሆኑን በኅዳር ወር መግለጫው አስታውቆ ነበር። ተቋሙ ዛሬ በወጣው መግለጫም፤ “ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ባደረገችው የአስተናጋጅ አገር ስምምነት ውስጥ የሚገኙት የግል የዲፕሎማሲያዊ ያለመከሰስ መብት፣ [ሌሎች] መብቶች እና ልዩ ጥቅሞችን በከፍተኛ መጠን የጣሰ ድርጊት ነው” ሲል ተመሳሳይ ሃሳብ አንጸባርቋል።

ይህንን ክስተት ተከትሎ ባንኩ የኢትዮጵያ መንግሥት “ሙሉ እና ግልጽ” ምርመራ እንዲያካሂድ ይፋዊ በሆነ “የቃል ማስታወሻ” መጠየቁን በዛሬው መግለጫው ላይ አስታውሷል። ከዚህ ባሻገር የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አኪንውሚ አዴሲና በኅዳር ወር አጋማሽ ገደማ የባንኩን ምክትል ፕሬዝዳንት ያካተተ ከፍተኛ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ ልከው እንደነበር በመግለጫው ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከባንኩ ሠራተኞች ጋር ንግግር እንዲያደርግ የተላከው ይህ ልዑክ ያደረገው ምልከታ ጉዳዩ “በአጥጋቢ መንገድ” እንዳልፈታ ማመልከቱን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

ዶ/ር አኪንውሚ፤ “የአፍሪካ የልማት ባንክ ሠራተኞች የጥቃት ፍራቻ ሳይኖርባቸው ሥራቸውን ማከናወን እና በአገሪቱ ውስጥ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ሙሉ እምነት የሚያሳድር አይደለም” ሲሉ ልዑኩ በምልከታው ያስተዋለውን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ድረስ ክስተቱን አስመልክቶ “ሪፖርትም ሆነ ስለ ተደረገ ምርመራ መረጃ” ለባንኩ አለማቅረቡን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል። በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን አለማድረጉ ባንኩን የሚያሳስበው ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ዶ/ር አኪንውሚ፤ “የጥቅምቱ ክስተት በአፍሪካ ልማት ባንግ ግሩፕ ሠራተኞች ላይ፤ በተለይም በኢትዮጵያ ቢሮ በሚገኙት ዘንድ ከፍተኛ ጭንቀት መፍጠሩን ቀጥሏል። ክስተቱ በባንኩ ባለድርሻዎች፣ በሌሎች ዘርፈ ብዙ የልማት ባንኮች፣ ዓለም አቀፍ የፋይናን ተቋማት፣ በሰፊው የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ እንዲሁም በሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ላይ ስጋት ፈጥሯል” ብለዋል።

ለዚህ ሲባል የኢትዮጵያ መንግሥት የምርመራ ውጤቱን እና በጥፋተኛ አካላት ላይ የወሰደውን እርምጃ ለሕዝብ ይፋ እስከሚያደርግ ድረስ በአገሪቱ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ሠራተኞቹ ከኢትዮጵያ ወጥተው በርቀት እንዲሰሩ እንደተወሰነ መግለጫው አስታውቋል።

ባንኩ ዓለም አቀፍ ሠራተኞቹን “በአስቸኳይ” ቢያስወጣም፤ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ግን በአገሪቱ ውስጥ በሥራቸው እንደሚቀጥሉ ጠቅሷል። በአዲስ አበባ ያለው የባንኩ ቢሮም “በተወካይ ኃላፊ” ስር ሆኖ እንደሚቀጥል አክሏል።

ባንኩ የኢትዮጵያን ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ እድገት ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ ተናግረው፣ ይሁንና በዚህ ክስተት ምክንያት የአፍሪካ ልማት ባንክ እና ኢትዮጵያ አሁን ያላቸው እንዲሁም ወደፊት ሊኖራቸው የሚችለው ግንኙነት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል የባንኩ ፕሬዝዳንት እንደተናገሩ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አኪንውሚ፤ “ይህ አስከፊ ክስተት እስከፈጠር ድረስ ባንኩ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን እጅግ ጥሩ የሆነ ግንኙት የሚያደንቅ ቢሆንም፤ ክስተቱ ሙሉ ለሙሉ የማይፈታ ከሆነ አሁንም የቀጠሉት የባንኩ ሥራዎች እና ባንኩ ወደፊት በአገሪቱ የሚኖረው ህልውና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል” ብለዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ 1.24 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ 22 ፕሮጀክቶችን እያከናወነ እንደሚገኝ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ ልማት ባንክ በሠራተኞቹ ላይ ያጋጠመውን ጉዳይ በተመለከተ ባለፈው ኅዳር ወር የወጣውን መግለጫ በተመለከተ እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የሌለ ሲሆን፣ በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ አሁን ከባንኩ የወጣውን መግለጫ አስመልክቶም የሰጠው ምላሽ የለም።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም. ሠራተኞቹ ያለ ይፋዊ ማብራሪያ በኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሕገ-ወጥ መንገድ ተይዘው አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸው ለሰዓታት ታስረዋል እንደነበር የተቃውሞ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

ባንኩ እንግልት ደረሰባቸው ያላቸውን ሠራተኞቹን ማንነት፣ የሥራ ድርሻ እና ክስተቱ ያጋጠመበትን ሁኔታ በተመለከተ በኅዳር ወርም ሆነ አሁን ባወጣው መግለጫ ላይ የሰጠው ዝርዝር የለም።