
ከ 5 ሰአት በፊት
በኦክላሆማ ግዛት የሚገኙ አንድ ዳኛ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል ባልፈፀመው ወንጀል ማረሚያ ቤት የነበረውን ግለሰብ ነፃ ብለውታል።
ግለሰቡ በአውሮፓውያኑ 1974 ነው የግድያ ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ እሥር ቤት የገባው።
የ70 ዓመቱ ግሊን ሲመንስ ባለፈው ሐምሌ ፍርድ ቤት ጉዳዩ እንደ አዲስ ይታይ ማለቱን ተከትሎ ነው ነፃ የወጣው።
48 ዓመታትን እሥር ቤት ያሳለፈው ሲመንስ በአሜሪካ ታሪክ ባልፈፀመው ወንጀል ረዥም ጊዜ የታሰረ ግለሰብ ሆኗል።
የኦክላሆማ ግዛት ዋና ዳኛ ኤሚ ፓሉምቦ፤ ሲመንስ ንፁሕ ሰው ነው ሲሉ ማክሰኞ ዕለት አውጀዋል።
“ይህ ፍርድ ቤት እንደደረሰበት ሲመንስ የተከሰሰበት፣ የተፈረደበት እና የታሰረበት ወንጀል እሱ የፈፀመው አይደለም” ብለዋል ዳኛዋ።
ከውሳኔው በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጠው ሲመንስ “ይህ የፅናት እና የቁርጠኝነት ውጤት ነው” ብሏል ሲል አሶሺየትድ ፕረስ ዘግቧል።
“ማንም ሰው ይህ አይሆንም ብሎ እንዲላችሁ አትፍቀዱ። ምክንያቱም እውን መሆኑ አይቀርም።”
ሲመንስ በኦክላሆማ ከተማ በሚገኝ አንድ የአልኮል መጠጥ መሸጫ በነበረ ዘረፋ ካሮላይን ሮጀርስን ገድሏል ተብሎ ነው የተፈረደበት።
- ትራምፕ በኮሎራዶ ግዛት በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳይሳተፉ በፍርድ ቤት ታገዱ20 ታህሳስ 2023
- በአዲስ አበባ መሥሪያ ቤቶች ተመሳሳይ ብሔር ያላቸው አመራሮች ብዛት ከ40 በመቶ እንዳይበልጥ ሊደረግ ነውከ 6 ሰአት በፊት
- የአፍሪካ ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙት “አሉታዊ ተጽዕኖ” ሊገጥመው እንደሚችል ገለጸ20 ታህሳስ 2023
ግለሰቡ 48 ዓመታት ከአንድ ወር ከ18 ቀናት እሥር ቤት አሳልፏል።
ባልፈፀሙት ድርጊት የታሰሩ ሰዎችን ታሪክ የሚመዘግበው ቢሮ እንደሚለው ሲመንስ በአሜሪካ ታሪክ ለረዥም ዓመታት ታሥሮ ነፃ የተባለ ግለሰብ ነው።
ሲመንስ ከተባባሪው ዶን ሮበርት ጋር የግድያ ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ የሞት ፍርድ ሲፈረድበት የ22 ዓመት ወጣት ነበር።
በኋላ ቅጣቱ እንዲቀል ተደርጎ በሞት ፈንታ የዕድሜ ልክ እሥር ተፈርዶበታል።
ሲመንስ እንደሚለው ግድያው በተፈፀመበት ወቅቱ እሱ ሉዊዚያና ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ነበር።
ባለፈው ሐምሌ የግዛቱ ፍርድ ቤት እንደተመለከተው የዓይን እማኝ ሌላ ተጠርጣሪ ጠቁሞ እንደነበር የሚያሳየውን መረጃ አቃቤ ሕግ ከሲመንስ ጠበቃዎች ሸሽጎ ነበር።
ወንጀሉ በተፈፀመ ወቅት በሥፍራው የነበረና በጥይት የተመታ አንድ ታዳጊ በሰጠው ምስክርነት መሠረት ነው ሲመንስ እና ሮበርትስ የተፈረደባቸው።
ነገር ግን የዓይን እማኙ ሌሎች ተጠርጣሪዎችንም ጠቁሞ ነበር።
ዶን ሮበርትስ በአውሮፓውያኑ 2008 በአመክሮ ከእሥር ቤት ወጥቷል።
ባልፈፀሙት ድርጊት ለእሥር የተዳረጉ ግለሰቦች በኦክላሆማ ግዛት ሕግ መሠረት 175 ሺህ ዶላር ካሳ ይከፈላቸዋል።
ለሲመንስ የተቋቋመ እና በርካታ ሺህ ዶላሮችን ማሰባሰብ የቻለ የጎፈንድሚ ድረ-ገፅ ግለሰቡ የጉበት ካንሰር እንዳለበት ይጠቁማል።
የተሰበሰበው ብር ኑሮውን ለመግፋት እና የኬሞቴራፒ ሕክምና እንዲያገኝ የሚያግዝ ነው።