አንትራክስ

ከ 6 ሰአት በፊት

የዓለም ጤና ድርጅት በምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ በሚገኙ አምስት አገራት ውስጥ የባክቴሪያ በሽታ የሆነው አንትራክስ (አባ ሰንጋ) መቀስቀሱን ሪፖርት አድርጓል።

ድርጅቱ በቅርብ ወራት ውስጥ በኬንያ፣ በማላዊ፣ በኡጋንዳ፣ በዛምቢያ እና በዚምባብዌ ከበሽታው ጋር በተያያዘ 20 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አድርጓል።

የ20 ሰዎች ሞት ሪፖርት የተደረገው በበሽታው ሳይያዙ አይቀሩም የተባሉ 1100 ሰዎች ከተመዘገቡ በኋላ ነው።

ከአምስቱ አገራት መካከል ዛምቢያ በከፍተኛ ደረጃ በርካታ የበሽታው ተጠቂዎች የሚገኙባት አገር ሆናለች። ከአጠቃላይ ዘጠኝ ግዛቶቿ በ10ሩ በሽታው የተቀሰቀሰ ሲሆን፣ 682 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል። አራት ሰዎች ደግሞ ለሕልፈት ተዳርገዋል።

አንትራክስ ምንድን ነው?

አንትራክስ የሚለው ቃል የመጣው ከግሪክ ቃል አንትራኪስ ሲሆን ትርጉሙ ከሰል ማለት ነው። ለበሽታው ይህ ስያሜ የተሰጠው ቆዳን የሚያጠቃው የበሽታው ዓይነት የቆዳ ቀለምን ስለሚያጠቁር ነው።

አንትራክስ በዋናነት የሚያጠቃው የጋማ ከብቶችን ቢሆንም፤ የሰው ልጆች በበሽታው ከተጠቃ እንስሳ ጋር በቀጥታ ከተገናኙ አሊያም በበሽታው የተያዘ እንስሳ ምርትን በጥሬው ወይም በደንብ ሳይበስል ከተመገቡ ሊያዙ ይችላሉ።

በሽታው የሚከሰተው ባሲለስ አንትራሲስ በተባለ አፈር ውስጥ ለዓመታት ተደብቆ በአካል ላይ በሚኖር ቁስል ወደ እንስሳት በሚገባ ባክቴሪያ ነው።

የአንትራክስ ዓይነቶች እና ምልክቶች

አንትራክስ በሦስት ዓይነት መልክ ሊከሰት እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት ያመለክታል።

የቆዳ አንትራክስ፡ ይህ የሚከሰተው በሽታው በቆሰለ ቆዳ በኩል ሲገባ ሲሆን፣ ይህ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም እና ከተቀሩት አንጻር ለከፋ ጉዳት የማያጋልጥ ነው።

በሽታው ሲጀምር ቀይ እብጠት ቆዳ ላይ ይወጣል። ከዚያም እብጠቱ ውሃ ይቋጥርና ህመም ወደሌለው ጥቁር ቁስልነት ይቀየራል።

ከዚያም አንዳንድ ሰዎች ራስ ምታት፣ የጡንቻ ህመም፣ ትኩሳት እና ማስመለስ ሊጀምራቸው ይላለች።

የአንጀት አንትራክስ፡ ይህ ዓይነቱ አንትራክስ ከአፍ አንስቶ አስከ ሰገራ መውጫ ባለው የሰውነት ክፍል የሚከሰት ነው።

ህመሙ ሲጀምር የሚያሳየው ምልክት ከምግብ መመረዝ ጋር ተመሳሳይነት አለው። ይሁን እንጂ እየቆየ ሲሄድ በበሽታው የተያዘ ሰው ከፍተኛ የሆነ የሆድ ህመም፣ ደም ማስመለስ እና ከፍተኛ ተቅማጥ ሊያጋጥመው ይችላል።

የሳምባ አንትራክስ፡ ይህ ከሁለቱም በላይ አደገኛው ነው። ሲጀምር የሚያሳየው ምልክት ከጉንፋን በሽታ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ ምልክቶቹ በፍጥነት በመቀያየር ታማሚው መተንፈስ እንዲከብደው ያደርጋል።

አንትራክስ
የምስሉ መግለጫ,የአንትራክስ ባክቴሪያ በአጉሊ መነጽር

አንትራክስ ምን ያህል ገዳይ ነው?

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሆስፒታል ገብተው የጤና ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል። አንድ ሰው ለበሽታው መጋለጡ እርግጠኛ ከሆነ ሕመሙ ሳይበረታበት የመከላከያ ሕክምና መውሰድ ይችላል።

ብዙዉን ጊዜ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለማከም እንደ ፔንሲሊን ያሉ ፀረ ተህዋሲ (አንቲባዮቲክስ) መድኃኒቶች ይሰጣሉ።

በቆዳ አንትራክስ ተይዘው ሕክምና ከማያገኙ ሰዎች 20 በመቶ ያህሉ ለሕልፈት እንደሚዳረጉ የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ይገልጻል። ይሁን እንጂ በዚህ የአንትራክስ ዓይነት በሽታ ተይዞ ሕክምና የሚያገኝ በሙሉ ከበሽታው ይድናል።

ይሁን እንጂ በበሽታው የተያዘ የእንስሳ ውጤት በጥሬው ወይም በደንብ ሳይበስል በመመገብ የሚመጣው የእንጀት አንትራክስ ብዙ ጊዜ ገዳይ ነው።

ትክክለኛው ሕክምና ካልተሰጠ በበሽታው ከሚያዙት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሕይወታቸው ያልፋል። ይሁን እንጂ ትክክለኛውን ሕክምና በመስጠት በዚህ ዓይነት የአንትራክስ በሽታ ከሚጠቁት መካከል 60 በመቶ የሚሆኑትን ሕይወት መታደግ እንደሚቻል የሲዲሲ አሃዝ ያሳያል።

በትንፋሽ መልክ ወደ ሰውነት የሚገባው የሳምባ አንትራክስ ከሁለቱም በላይ እጅግ አደገኛው እና ገዳዩ ነው። በበሽታው የተያዘ ሕክምና ካላገኘ ሁሌም ሕይወቱ ሊያልፍ እንደሚችል ይታመናል። ትክክለኛውን ሕክምና ቢያገኙም ከሞት የሚተርፉት 55 በመቶ የሚሆኑት ናቸው።

አንትራክስ እንደ ጦር መሳሪያ?

ሲዲሲ እንደሚለው ሰዎችን ሆነ ብሎ ለማጥቃት አንትራክስን መጠቀም ቀላል ነው።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በሽታውን የሚያስከትለውን ባክቴሪያ በተፈጥሮ አካባቢዎች ማግኘት እንዲሁም በቤተ-ሙክራ መሥራት ቀላል በመሆኑ እና ባክቴሪያው ለረዥም ጊዜ በአካባቢያችን መቆየት መቻሉ ነው።

ቅንጣት የሚያክለውን ባክቴሪያውን ማንም ሰው ሊገምት በማይችልበት መልኩ በምግብ እና ውሃ ውስጥ፣ በዱቄት እና በሚረጩ ነገሮች ውስጥ መደበቅ ይቻላል።

በዚህ መልኩ የሚለቀቅን አንትራክስ በማየት፣ በማሽተት ወይም በጣዕም መለየት አዳጋች ነው።

ከአውሮፓውያኑ 2001 የመስከረም 11ዱ ጥቃት በኋላ አንትራክስ ወደ አሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቢሮዎች እና ወደ የመገናኛ ብዙኃን መላኩ ይታወሳል።