
ከ 5 ሰአት በፊት
የፈረንሳይ ፍርድ ቤት የቀድሞውን ሩዋንዳዊ ዶክተር በአገራቸው በአውሮፓውያኑ 1994 በተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ ተሳትፎ ነበራቸው ሲል 24 ዓመት ፈረደባቸው።
ሶስቴን ሙኒየማና በዘር ማጥፋት እና በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆነው ተገኘተዋል።
በጥቂት ወራት ውስጥ ከ800 ሺህ ህዝብ በላይ በተጨፈጨፈበት የሩዋንዳ የዘር ፍጅት ዶክተሩ ሰዎች እንዲሰቃዩ እና እንዲገደሉ አደራጅተዋል የሚል ክስም ቀርቦባቸዋል።
የፈረንሳይ አቃብያነ ህግ ጉዳዩን ለፍርድ ለማቅረብ እና ለማስበየን 28 ዓመታት ፈጅቶባቸዋል።
ዶክተር ሶስቴን የዘር ጭፍጨፋው በተፈጸመበት ዓመት በደቡባዊ ሩዋንዳ በምትገኘው ቡታሬ የማህጸን ሐኪም ነበሩ።
በሚገደሉ ሰዎች ላይ መንገዶችን በማዘጋት እንዲሰባሰቡ በማድረግ እንዲሁም ከመገደላቸውም በፊት በአካባቢው የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ እንዲቆዩ በማድረግ ተባብረዋል ተብሏል።
በተጨማሪም በቱትሲዎች ላይ እየደረሰ የነበረውን እልቂት የሚያበረታታ እና በሰፊው የተሰራጨ ደብዳቤ አዘጋጅተዋል የሚል ክስም ቀርቦባቸዋል። ይህ ደብዳቤ በቱትሲዎች ላይ በሚደርሰውም ጥቃት ጥቅም ላይ መዋሉንም አቃብያነ ህጉ አስረድተዋል።
- በሺዎች ሞት ሲፈለግ የነበረው የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ተጠርጣሪ ከ30 ዓመት በኋላ ተያዘ26 ግንቦት 2023
- የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት ለመቆም ብቁ አይደለም ተባለ7 ሰኔ 2023
- የሩዋንዳውን የዘር ማጥፋት ወንጀለኛ ፍለጋ በመቃብሩ ውስጥ ተጠናቀቀ13 ግንቦት 2022
በሩዋንዳው የዘር እልቂት የተጨፈጨፉት አብዛኛዎቹ የቱትሲ ብሔረሰብ አባላት ሲሆኑ ለዘብተኛ ወይም ጽንፈኛውን የሁቲ መንግሥት የሚቃወሙ ነበሩበት ተብሏል።
በአውሮፓውያኑ 1994 ወደ ፈረንሳይ ያቀኑት ዶክተሩ በፍርድ ሂደቱ ወቅትም ቱስቲዎችን በአካባቢው በሚገኙ መስሪያ ቤቶች እንዲጠለሉ በማድረግ ከጥቃት ለማዳን የሞከሩ ለዘብተኛ ሁቱ ነበርኩ ሲሉ በተደጋጋሚ ተከራክረዋል።
ቸሎቱ በፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ ለስድስት ሳምንታት ያህል የቆየ ሲሆን አቃብያነ ህጉም ዶክተሩ 30 ዓመታት እንዲፈረድባቸው ተከራክረው ነበር።
በአውሮፓውያኑ 1994 ወደ ፈረንሳይ የመጡት ዶክተሩ ባለቤታቸው ቀድሞውኑ በምትኖርበት በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍልም በህክምና ባለሙያነት ያገለግሉ ነበር። ዶክተሩ በቅርቡ ነው ጡረታ የወጡት።
ዶክተሩ ቅሬታ የቀረበባቸው በአውሮፓውያኑ 1995 ነበር። ዶክተሩ በሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ወቅት ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የዣን ካምባንዳ የቅርብ ጓደኛ ነበሩ። ካምባንዳ በተባበሩት መንግሥታት የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት በዘር ፍጅት ወንጀል ተፈርዶባቸው በማሊ የእድሜ ልክ እስራት ላይ ይገኛሉ።