የኤክስ ማሕበራዊ ሚድያ  መለያ

ከ 1 ሰአት በፊት

የቀድሞው ትዊተር በዘንድሮ መጠሪያው ኤክስ የተሰኘው ግዙፉ ማሕበራዊ ሚድያ በመላው ዓለም ለአንድ ሰዓት ያህል ተቋረጠ።

ማሕበራዊ ሚድያዎች ሲቋረጡ መዝግቦ የሚያስቀምጠው ዳውንዲቴክተር [Downdetector.com] በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ 47 ሺህ ያክል የኤክስ እና የኤክስ ፕሮ ተጠቃሚዎች ማሕበራዊ ሚድያውን መጠቀም አቅቷቸው ነበር ብሏል።

በዩናይትድ ኪንግደም እና በአህጉረ እሰያ ያሉ የተወሰኑ ተጠቃሚዎችም እንዲሁ ኤክስ ላይ የተለጠፉ ይዘቶችን ማግኘት ተስኗቸው ቆይቷል።

ኤክስ ተቋርጦ በነበረ ሰዓት ወደ ማሕራዊ ሚድያው ያቀኑ ተጠቃሚዎች “እንኳን ወደ ኤክስ መጡ” [“Welcome to X!”] የሚል መልዕክት ነው የሚታያቸው።

የቢሊየነሩ ኢላን መስክ ንብረት የሆነው ኤክስ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠየቅም እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

ኢላን መስክ ባለፈው ዓመት ነው የቀድሞውን ትዊተር በ44 ቢሊዮን ዶላር ገዝቶ የግል ንብረቱ ያደረገው።

ኤክስ መሥራት ባቆመ በደቂቃዎች ውስጥ #TwitterDown የተሰኘው ሃሽታግ በብዙዎች ዘንድ ተጋርቷል።

ነገር ግን ኤክስ ከአንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ ወደ ቀድሞ ሥራው ተመልሶ ተጠቃሚዎች ማሕበራዊ ሚድያውን ድጋሚ ማግኘት እንደቻሉ ተዘግቧል።

ኢላን መስክ ትዊተርን ከገዛው በኋላ ስሙን ወደ ኤክስ ቀይሮታል።

ኤክስ የመስክ ንብረት ከሆነ በኋላ ከማስታወቂያ የሚያገኘው ገቢ መቀነሱ ተሰምቷል።

በቅርብ ጊዜ ደግሞ ፀረ-ሴማዊ መልዕክቶች ከማስታወቂያዎች ጋር አብረው ይመጣሉ የሚሉ ወቀሳዎች ተሰንዝረውበት ነበር።

ይህን ወቀሳ ተከትሎ የመስክ ኩባንያ ኤክስ እንዲህ ብሎ ስሙን ያጠፋውን ሚድያ ማተርስ ፎር አሜሪካ የተሰኘውን ድርጅት ከሶታል።

ባለፈው ወር መስክ ኤክስ ላይ ማስታወቂያ ማስኬድ ያቆሙ ድርጅቶችን ኃይለ ቃል በተሞላበት መንገድ ማሕበራዊ ሚድያውን ለመግደል የሚጡ ሲል ዘልፏቸዋል።

ኩባንያው ከአውሮፓ ሕብረትም ሕጋዊ ያልሆኑ ይዘቶችን በማሰራጨትና የተዛባ መረጃ በማስፋፋት [ዲስኢንፎርሜሽን] ወቀሳ ደርሶበታል።