
21 ታህሳስ 2023, 16:59 EAT
ከአገር ውጭ ያሉ ከ25 እስከ 60 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወንድ ዩክሬናውያን የአገሪቱን ጦር እንዲቀላቀሉ ጥሪ ሊቀርብላቸው ነው።
የአገሪቱ መከላከያ ሚንስትር ጥሪውን ተቀብለው በማይመጡት ላይ ማዕቀብ ይጣላል ብለዋል።
ይህ ከአገር ውጭ ለሚኖሩ ዩክሬናውያን ጥሪ ሊቀርብ የመሆኑ ዜና የተሰማው የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የአገሪቱ ጦር አመራሮች ግማሽ ሚሊዮን ተጨማሪ የሠራዊት አባላት እንዲመለመሉ ጥያቄ ማቅረባቸውን ከገለጹ በኋላ ነው።
በኪዬቭ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፕሬዝዳንቱ ሁለት ዓመት ሊደፍን የተቃረበውን ጦርነት እየመሩ ካሉ ጦር አዛዦች “ከ450 እስከ 500 ሺህ ሰዎችን” እንደሚፈልጉ ጥያቄ አቅርበዋል ብለዋል።
ዜሌንስኪ ተጨማሪ 500 ሺህ ወታደሮችን የመመልመል ጥያቄ ከማጽደቃቸው በፊት ተጨማሪ መረጃ እንዲቀርብላቸው ማዘዛቸውን ተናግረዋል።
በዩክሬን የተጨማሪ ወታደሮች መልመላን የተመለከቱ ሪፖርቶች በስፋት መሰማት የጀመሩት አገሪቱ በሩሲያ ጦር ላይ ጀምራው የነበረው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ውጤማ ሳይሆን ከቀረ በኋላ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ከሩሲያ የተቃጣባትን ወረራ ለመቀልበስ በአውሮፓ እና አሜሪካ እርዳታ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ ሆና የቆየችው ዩክሬን ከምዕራባውያን የምትቀበለው እርዳታ መዘግየት አጋጥሞታል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዩክሬን ከአሜሪካ ልታገኘ የነበረው የ60 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ በሪፐብሊካኖች አማካይነት በኮንግረሱ ውድቅ ተደርጓል።
ከአውሮፓ ኅብረት ደግሞ ሊሰጣት የነበረው የ50 ቢሊዮን ዩሮ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲሁ በሃንጋሪ ምክንያት ታግዷል።
- በአዲስ አበባ መሥሪያ ቤቶች ተመሳሳይ ብሔር ያላቸው አመራሮች ብዛት ከ40 በመቶ እንዳይበልጥ ሊደረግ ነው21 ታህሳስ 2023
- ሊቨርፑልን ከአርሰናል ያገናኘው የፕሪሚየር ሊግ ሳምንት ግምት21 ታህሳስ 2023
- የዓለም ጤና ድርጅት አዲስ የኮቪድ ዝርያ ዓለም አቀፋዊ ስርጭቱ ፈጣን መሆኑን ይፋ አደረገ21 ታህሳስ 2023
በአሁኑ ወቅት የተተኳሽ እጥረት እንዳጋጠማት እየተዘገበ የምትገኘው ዩክሬን፤ ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በውጭ ነዋሪ የሆኑ ዩክሬናውያንን በጦር ሜዳ የማሰለፍ ዕቅድ አላት።
የአውሮፓ ኅብረት የስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የሆነው ዩሮስታት አሃዝ እንደሚያሳየው የሩሲያን ወረራ ተከትሎ ከ18 እስከ 64 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 768ሺህ ወንዶች ከዩክሬን ወደ አውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ተሰደዋል።
የዩክሬን መከላከያ ሚንስትር ሩስቴም ኡሜሮቭ ቢልድ እና ፖሊቲኮ ከተባሉ መገናኛ ብዙሃን ጋር በነበራቸው ቆይታ ዩክሬናውያኑ ወደ አገር ተመልሰው የሚዋጉት “ለክብር” ሲሉ እንጂ “ቅጣትን ፈርተው” አይሆንም ብለዋል።

የመከላከያ ሚንስትሩ የሚመለመሉ የሠራዊት አባላት ቀድመው ምን አይነት ስልጠና እንደሚወስዱ፣ ምን አይነት ጦር መሳሪያ እንደሚታጠቁ እንዲሁም የት እና መቼ ለግዳጅ እንደሚሰለፉ እንዲያውቁ ማድረጉ ተገቢ ነው ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
“በፍቃዳቸው የማይመጡ ከሆነ ምን ማድረግ እንዳለብን ገና እየተነጋገርንበት ነው” ብለዋል።
ከዚህ ቃለ መጠይቅ በኋላ ግን የመከላከያ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ለግዳጅ ወደ አገር በማይመለሱት ላይ ምንም አይነት ቅጣት አይኖርም ሲሉ ማስተባበያ ሰጥተዋል።
“የዩክሬን ዜጎች ጦሩን ለመቀላቀል ፍላጎት ካላቸው መቀላቀል ይችላሉ። . . . በውጭ ላሉ ጥሪ የማቅረብ ንግግር የለም” ብለዋል።
ዩክሬን ከአገር ውጭ የጦር አባላትን የምትመለምልበት ተቋም የላትም እንዲሁም ዜጎችን ለጦር ግዳጅ ያለ ፍላጎት መመልመል የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ የላትም።