December 21, 2023 – Konjit Sitotaw

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የፖሊስን የጥርጣሬ መነሻና የተጠርጣሪውን መከራከሪያ ነጥብ ተመልክቷል።ተጠርጣሪው በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክ/ከተ ወረዳ 8 ነዋሪ መሆኑን አስመዝግቧል።
የአ/አ ፖሊስ መርማሪ ተጠርጣሪው በታህሳስ 7 ቀን 2016 ዓ.ም በከተማዋ በተለምዶ ቦሌ ኤድናሞል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከምሽቱ 4:00 ላይ አባተ አበበ የተባለ ግለሰብን በ3 ጥይት በመምታት ህይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል ተብሎ መጠርጠሩን ጠቁሞ ምርመራ መጀመሩን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አብራርቷል።
በጅምር ምርመራ መዝገቡ የሰው ማስረጃ ቃል ለመቀበል እና የአስከሬን ምርመራ ውጤት ለማቅረብ የ14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት መርማሪ ፖሊስ ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩላቸው ደንበኛቸው ላይ ፖሊስ የጠየቀው የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ረጅም መሆኑን በመጥቀስ የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄውን በመቃወም ተከራክረዋል; ጠበቃዋ ደንበኛዬ ስሜ በማህበራዊ ሚዲያ እየጠፋነው በማለት ፖሊስ ጣቢያ ለማመልከት እራሳቸው በሄዱበት ወቅት ነው የተያዙት በማለት ገልጸዋል።
ደንበኛዬ በመገናኛ ብዙሃን እንደጥፋተኛ ተደርገው ንፁህ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በጣሰ መልኩ እየተዘገበባቸው ነው በማለትም ጠበቃዋ አቤቱታ አቅርበዋል።
ጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን የተመለከቱት ዳኛ በኩልም ተጠርጣሪ ተብሎ ቢዘገብ ችግር እንደሌለው ተገልጿል።
እንደአጠቃላይ የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ፖሊስ የጠየቀውን የምርመራ ማጣሪያ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል። የምርመራ ማጣሪያ ውጤቱን ለመጠባበቅ ለታህሳስ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል።