December 21, 2023 

ተቃዋሚው እናት ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመንግሥት ሠራተኞች እየሰጠው የሚገኘው ምዘና እንዲኹም በምዘናው የሚሰጠው የሠራተኞች ምደባ ባስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል። ፓርቲው፣ ፈተናና ምዘናው መንግሥት የማይፈልጋቸውን ሠራተኞች በማስወገድ የሚፈልጋቸውን ለመተካት ኾን ብሎ ያዘጋጀው ስልት መኾኑን ለመገመት አያዳግትም ብሏል።

ከፈተናው በፊት የፈተናው መልስ በየትምህርት ቤቶች አስቀድሞ ተለጥፎ መገኘቱን ከመረጃ ምንጮቹ መረዳቱን የጠቀሰው ፓርቲው፣ ይህን ተከትሎ ፈተናው ለጊዜው መቋረጡን እንደደረሰበት ገልጧል። ፓርቲው፣ በአዲስ አበባ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እየሠሩ የሚገኙ ሠራተኞች የብሄር ማንነታቸውን እንዲሞሉ የሚያስገድደው ቅጽ ባስቸኳይ እንዲቆምም ፓርቲው ጠይቋል።

ፓርቲው በዚኹ መግለጫው፣ የከተማዋ አስተዳደር ሠራተኞች የፈተና አሰጣጡን፣ ምደባውንና “ብሄር” የሚጠይቀውን ቅጽ በሰላማዊ መንገድ እንዲቃወሙ ጥሪ አድርጓል።