December 21, 2023

በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ አማኑኤል ከተማ ዙሪያ ከትናንት ጀምሮ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ መኖሩን ዋዜማ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች።

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው አንድ ነዋሪ፣ ከኹለቱም ወገኖች የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ግን ለጊዜው ማወቅ እንዳልቻሉ ገልጠዋል።

ዛሬ እኩለ ቀን ድረስ በከተማዋ ተኩስ መኖሩንና ኹሉም የመንግሥትና የግል ተቋማት ዝግ መኾናቸውን ዋዜማ ተረድታለች።

በተኩስ ልውውጡ ሳቢያ፣ ከደብረማርቆስ ወደ ባሕርዳር የትራንስፖርት አገልግሎቱ ከተቋረጠ ሳምንታት እንዳስቆጠረ ምንጮች ጠቁመዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ፈረስ ቤት ከተማና አካባቢዋም፣ ላለፉት ሦስት ቀናት በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከባድ ውጊያ መካሄዱን ዋዜማ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች።

ነዋሪዎቹ በግጭቱ በውል ባልታወቁ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል።