

ዜና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በፀጥታ ችግር ምክንያት አገራዊ ጥናት ማድረግ አለመቻሉን አስታወቀ
ቀን: December 20, 2023
- የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ሰነድ በታሰበለት ጊዜ አይደርስም ተብሏል
በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚታዩ ግጭቶችና የፀጥታ ችግሮች ምክንያት፣ አገራዊ ይዘት ያለው ጥናት ማካሄድ እንዳልቻለ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) እንደገለጹት፣ ኢንስቲትዩቱ ቀደም ባሉት ጊዜያት ጥናት ሲያካሂድ፣ ከትግራይ ክልል በስተቀር›› ይባል የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ግጭቱ እየሰፋ በመሄዱ በሰፊው የተጀመሩ የምርምር ሥራዎችን ማካሄድ አልተቻለም ብለዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ይህን የተናገሩት ታኅሳስ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴርንና ተጠሪ ተቋማትን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት ሲያደርግ ነው፡፡
በፀጥታ ችግሩ ምክንያት በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጋቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ችግሩ በእጅጉ ሥራችን እየተገዳደረ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ከፀጥታ ችግሩ በተጨማሪ ክልሎች ኢንስቲትዩቱን ለመተባበር እንደማይፈልጉ፣ አንዳንድ ክልሎች የኢንስቲትዩቱ አጥኚዎች ሲላኩ ለማጋለጥና ገመና ይፋ ለማድረግ የመጡ እንጂ ለሥራ እንደማይመስላቸው ተናግረዋል፡፡ በትብብር መጥፋት ምክንያት በሚደረጉ ጥናቶች ከኢንስቲትዩቱ የምርምር ዝርዝር የወጡ ክልሎች እንደነበሩ አስታውቀዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፣ በሩብ ዓመቱ ከኤክስፖርት ምርቶች 1.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፣ 814 ሚሊዮን ዶላር ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ለዕቅዱ ማነስ ምክንያት በማዕድን ዘርፍ ያለው የፀጥታ ችግርና በግብርና ምርቶች ላይ የሚታየው የሕገወጥ ንግድ መስፋፋት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተመሳሳይ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 1.1 ቢሊዮን ዶላር ለመሳብ ታቅዶ ማሳከት የተቻለው 765 ሚሊዮን ዶላር ነው ብለዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ አገሪቱ ማሳካት የቻለችው አጠቃላይ ገቢ 109 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ በሩብ ዓመቱ ለአንድ ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ማሳካት የተቻለው 50 በመቶ እንደሆነ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ 4.1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ዕቃዎች ከውጭ መግባታቸውን አክለዋል፡፡
በተያዘው ዓመት ተጠናቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል ተብሎ የተነገረለት የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ሰነድ፣ የሥራው ሒደት ዝርዝር ውይይት የሚያስፈልገውና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊመክርበት ስለሚገባ፣ በታሰበው ጊዜ ሊደርስ እንደማይችል ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡