

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላት ወርቅ ኃይሉ ሹመት
ዜና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት የተሰጠው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሹመት የሕግ ጥሰት አለበት…
ቀን: December 20, 2023
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን ከፖለቲካ ከፓርቲዎች ጋር ምክክር ሳያደርጉ በቀጥታ ለሹመት ማቅረባቸው፣ የሕግ ጥሰት የታየበት መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ታኅሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ዘጠነኛ መደበኛ ስብሰባው፣ ወ/ሮ ሜላተ ወርቅ ኃይሉን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ መርጧል፡፡
የማንኛውም የፖለቲካ አባል አለመሆናቸውን፣ በጉምሩክ ኮሚሽን ለአሥር ዓመታት፣ በግል የሕግ የማማከር አገልግሎትና የሕግ ሰነዶች ላይ የሠሩና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን እስከ የካቲት 2015 ዓ.ም. ድረስ ያገለገሉ በመሆናቸው፣ የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት የመወጣት ብቃት እንዳላቸው በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ ተናግረዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም. ተሻሽሎ በወጣው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1133 የሥራ አመራር ቦርድ አባላት አሰያየምን በሚያብራራው አንቀጽ አምስት መሠረት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕጩ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ስም ዝርዝርን ከመልማይ ኮሚቴው ከተቀበለ በኋላ፣ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር በቀረቡት ዕጩዎች ላይ ምክክር እንደሚያደርግ ተደንግጓል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክክር ካደረጉ በኋላ በቦርዱ ውስጥ ባሉት ክፍት ቦታዎች ዕጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው እንዲሾሙ እንደሚያደርግ ተብራርቷል፡፡
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ኮሚቴው መልምሎ ያቀረበላቸውን ዕጩ በቀጥታ ወደ ፓርላማው መላካቸውንና ይህም ሒደት የሕግ ጥሰት ያለበት መሆኑን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
አዋጁ፣ ‹‹በአዋጁ መሠረት ውይይት ይደረግበታል›› ይላል፣ ነገር ግን ይህ ሳይደረግበትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይመክሩበት ወደ ፓርላማ መላኩ የሕግ ጥሰት እንዳለ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የጋራ ምክር ቤቱ የቀድሞ ሥራ አስፈጻሚ የነበሩትና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) አመራር ራሔል ባፌ (ዶ/ር)፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊያማክሩን ይገባ ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሲባል ብልፅግና ብቻ ተደርጎ ታስቦ፣ ያለ ምክር ቤቱ ዕውቅና በቀጥታ ወደ ሹመት መላኩ የሕግ ጥሰት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ጉዳዩ ሕዝባዊ ሆኖ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕውቅና ብቻ ሹመት መሰጠቱ፣ ግልጽ የሆነ የሕግ ጥሰት አለው ሲሉም አክለዋል፡፡
ያም ሆኖ ‹‹ነፃና ገለልተኛ ሥርዓት በሌለበት አገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልአክም አምጥተው ቢያስቀምጡ ምንም ፋይዳ የሌለው ተግባር ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም የአገር ሰላምና የኑሮ ሁኔታ ሳይስተካከል መሾሙ ትርጉም የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የቀድሞው የቦርዱ ሰብሳቢ በሥራ ላይ በነበሩበት ወቅትም ምርጫ ያልተካሄደባቸው በተለይም በትግራይ፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል፣ በኦሮሚያና በሌሎች አካባቢዎች ምርጫ ለማካሄድ ሰላም መቅደም ያለበት በመሆኑ፣ መንግሥት አገራዊ ሁኔታውን በሹመት ሸፋፍኖት ሊያልፍ አይገባም ብለዋል፡፡
በፈቃዳቸው ሥራ እንደለቀቁ የተነገረላቸውንና ቦርዱን ከአራት ዓመታት በላይ በሰብሳቢነት የመሩትን ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የተኩት ወ/ሮ ሜላተ ወርቅ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዎች በሕግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ አስተዳደር የሁለተኛ ዲግሪ ምሩቅ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ሹመቱን በአንድ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ያፀደቁት ሲሆን፣ ድምፀ ተዓቅቦ ያሰሙት የሐረሪ ክልል ተመራጭና የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጥያቄ፣ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባዔ አባላት አመራረጥን በተመለከተ የምርጫ ቦርድ አመራሮች ሆን ብለው ሕግ ሲጥሱ መስተዋሉን ገልጸው፣ የተቋሙ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ወ/ሮ ሜላተ ወርቅም የዚሁ የሕግ ጥሰት ተባባሪ ስለነበሩ አሁን ቃለ መሃላ ሲፈጽሙና በቀጣይ ወደ ሥራ ሲገቡ የገቡትን ቃለ መሃላ እንዲያከብሩ አሳስበዋል፡፡
ፈቲህ (ዶ/ር) ያነሱት ቅሬታ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለታዳጊ ክልሎች 20 ወንበር መሰጠቱን፣ ከዚህ ውስጥ በሐረሪ ክልል ካሉት ሁለት የምከር ቤት ወንበሮች መካከል አንድ ወንበር ለሐረሪዎች ብቻ እንዲሆን በሕግ ሲሠራበት የቆየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ የፓርላማ መቀመጫም የሐረሪ ብሔር ብሔረሰቦች ብቻ መወዳደር የነበረባቸው ቢሆንም፣ የሐረሪ ብሔር ብሔረሰቦች ያልሆኑ ሌሎች ብሔረሰቦች እንዲወዳደሩበት መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ይህ ሲሆን ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ውሳኔ፣ የክልሉ ምክር ቤትን ውሳኔ፣ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔንም ሆነ ባለፈው አምስት የምርጫ ዘመን የነበረውን አሠራር ቦርዱ መጣሱን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ አዲስ የተሾሙት አመራር ይህን አሠራር እንዲመረምሩ ጠይቀዋል፡፡