የንግድ መርከቦች መተላለፊያ የሆነው ቀይ ባህር ላይ ጥቃቶች በተደጋጋሚ መከፈታቸው ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ሥጋት ደቅነዋል

ፖለቲ

ዮናስ አማረ

December 20, 2023

ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ከመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ርቀው ቢገኙም፣ የጦርነቱ እሳት ግን ሊፈጃቸው የቀረበ መስሏል፡፡ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ታኅሳስ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ከዓለም ግዙፍ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ቢፒ ወርልድ (BP World)፣ በቀይ ባህር የሚያደርገውን የንግድ ምልልስ ለጊዜው ማቆሙን አስታውቋል፡፡ ቢፒ ወርልድ ይህን ዕርምጃ ለመውሰድ የተገደደው ደግሞ ከፊል የመንን የተቆጣጠሩትና በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማፂያን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቀይ ባህር የንግድ መተላለፊያ ላይ የሚፈጸሙት ጥቃት በመጨመሩ ነው፡፡

የአፍሪካ ቀንድ የደረሰው የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት ወላፈን | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የአፍሪካ ቀንድና የዓረብ ባህረ ሰላጤ ተጠጋግተው የሚገኙበት የባብኤል መንዴብ በጂቡቲና ኤርትራ መጋጠሚያ፣ እንዲሁም በየመን መካከል የሚገኘው ጠባብ የባህር መተላለፊያ በእስራኤልና በሐማስ የወቅቱ ቀውስ የተነሳ ከባድ የፀጥታ ችግር እየገጠመው ነው፡፡

እስራኤል በጋዛ በፍልስጤማዊያን ላይ እየወሰደች ያለውን ጥቃት ለመበቀል የሁቲ አማፂያን በእስራኤልና በምዕራባዊያን አጋሮቿ መርከቦች ላይ ጥቃት መክፈት ጀምረዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ወደ አሥር በመቶ የዓለም ንግድ መተላለፊያ ነው የሚባለው ባብኤል መንዴብ ቀጭን የባህር ወሽመጥ የንግድ እንቅስቃሴ እየተስተጓጎለ ነው የሚገኘው፡፡

የሁቲ አማፂያን የፓናማ ባንዲራ በምታውለበልብ መርከብና በሌሎች መርከቦች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፡፡ የድሮን ጥቃት ጭምር ያካተተ ነውም ተብሏል፡፡ ከጂቡቲ ሰሜን ምሥራቅ 117 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በቀይ ባህር፣ እንዲሁም ለባብኤል መንዴብ ወሽመጥ 56 ኪሎ ሜትር በራቀ ሥፍራ ላይ ጥቃት ከፍተዋል፡፡

‹‹ባብኤል መንዴብ›› ወይም ‘The Gate of Grief or Tears’ እያሉ የሚጠሩት ይህ ወሳኝ የዓለም የንግድ ጉሮሮ የሆነ የባህር ወሽመጥ፣ ልክ እንደ ስሙ በሰቆቃና በቀውስ የተሞላ መገናኛ እየሆነ ነው ተብሏል፡፡

የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት በአፍሪካ አገሮች ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ የሚፈትሽ ጽሑፍ ያስነበበው ዘ ኢስት አፍሪካን፣ ጦርነቱ በአፍሪካ አገሮች ያሉ ግጭቶችን ትኩረት እንዳያገኙ ያደርጋል ሲል ነው የገለጸው፡፡ እንደ ሱዳን ባሉ አገሮች ከባድ ቀውስ ያደረሰ ግጭት ቢኖርም፣ ነገር ግን የጋዛው ጦርነት ፍፁም ትኩረት እንዲያጣ አድርጎታል ይላል፡፡

ዘገባው ሲቀጥል በጋዛ ጦርነት ሲካሄድ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሞተና የቆሰለ የለም ይላል፡፡ ይሁን እንጂ የጋዛው ጦርነት ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የአፍሪካ አገሮች ሕዝቦችን እያደማ ይገኛል ይላል፡፡

የአልሸባብን አቋም እንደ አንድ ማሳያ አድርጎ የሚያቀርበው ዘገባው የሐማስን ፀረ እስራኤል ጥቃት ቀድሞ መደገፉን ይናገራል፡፡ አልሸባብና ሐማስ ቀጥተኛ ግንኙነት ባይኖራቸው እንኳን በሃይማኖትና በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለማዊ ቁርኝት በመፍጠራቸው የተነሳ፣ አልሸባብ ሐማስን ለማገዝ ሲል በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ላይ ጥቃት ሊከፍት እንደሚችል ግምቱን ያስረዳል፡፡

ሃዋ ኑር (ዶ/ር) የተባሉ አንዲት ተመራማሪ በዚሁ ዘገባ ላይ እንደተናገሩት ከሆነ፣ የአፍሪካ አገሮች በእስራኤልና ሐማስ ጦርነት ጉዳይ አንዱን ወገን ደግፈው መቆም የለባቸውም፡፡

‹‹በዓለማችን ላይ አክራሪነት እየነገሠ ነው ያለው፡፡ የእስራኤልና የፍልስጤም ጉዳይ ደግሞ ይህን የፅንፍ ፖለቲካ የበለጠ እንዲንሰራፋ የሚያደርግ አንድ አጋጣሚ ነው፡፡ እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች በእንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ከማንም ጋር አለመወገንና ድምፃቸውን ማጥፋት ነው የሚበጃቸው፤›› ሲሉ ለአፍሪካውያን ያዋጣል ያሉትን መክረዋል፡፡

እንደ አልሸባብ ያሉ በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ቀጣና የሚንቀሳቀሱ የሃይማኖት ፅንፈኛ ቡድኖች ብቻ ሳይሆኑ፣ በየመን ያሉ የሁቲ አማፂያንም ለሐማስ ያላቸውን አጋርነት ለመግለጽ በቀይ ባህር ቀጣና ጥቃታቸውን ከሰሞኑ ማስፋፋት ጀምረዋል፡፡

ሁቲዎች ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው በሚሏቸው የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መክፈታቸው የዓለም ነዳጅ ገበያ አናግቶታል እየተባለ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የሁቲ አማፂያን ጥቃት እንደ ስንዴ ያሉ የምግብ ሰብሎችንና የፓልም ዘይት ምርት ምልልስንም ይጎዳል እየተባለ ነው፡፡

በቀይ ባህር በኩል የሚካሄደው የመርከብ ንግድ ልውውጥ ደቡባዊና ምዕራባዊ አፍሪካን ተሽከርክሮ፣ በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል ከሚካሄደው የንግድ ልውውጥ በእጅጉ ያጠረ ነው ይባላል፡፡

አንዳንድ ሪፖርቶች በስዊዝ ቦይ በኩል የሚደረገውና ባብኤል መንዴብን የሚሻገረው የንግድ ጉዞ፣ ከአትላንቲክ ውቂያኖስ ጉዞ በአሥር ቀናት ያጠረ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የንግድ መስመር በየመን የሁቲ አማፂያን ጥቃት የተነሳ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው የንግድ መርከቦች ዙሪያ ጥምጥም ለመሄድ ተገደዋል እየተባለ ነው፡፡

በአጭር ጊዜ በመላው ዓለም አገሮች ዘንድ ሥጋት ያሳደረው በቀይ ባህር ላይ የሚተላለፉ መርከቦችን ዒላማ ያደረገው የሁቲ አማፂያን ጥቃት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ አፍሪካ አገሮችን የወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ እንደሚጎዳ እየተገመተ ይገኛል፡፡

ከዚህ ቀደምም ከሶማሊያ በሚነሱ የባህር ወንበዴዎች ጥቃት ብዙ ችግር ገጥሞት የነበረው የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ መጋጠሚያ የንግድ ቀጣና፣ አሁን ይህን ችግር በሁቲ አማፂያን ጥቃት እያስተናገደ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2010 ለምሳሌ የሶማሊያ የባህር ዘራፊዎች 219 ጥቃቶችን በዚህ አካባቢ አድርሰዋል፡፡ ይህ ቁጥር በመላው ዓለም ከደረሰው የዚያን ዓመት የባህር ውንብድና 49 በመቶ የሚሸፍን ነበር፡፡ የሶማሊያ ባህር ዘራፊዎች በጊዜው 49 የንግድ መርከቦችን አግተው ነበር፡፡ በጊዜው 1,016 ባህርተኞችን (የመርከብ ሠራተኞችን) በማገትም ማስለቀቂያ ወረታ ገንዘብ ሲጠይቁ ነበር፡፡

የሶማሊያ የባህር ወንበዴዎች በዚህ ዓይነቱ የመርከበኞች ዕገታ እ.ኤ.አ. በ2010 ብቻ 238 ሚሊዮን ዶላር የዕገታ ማስለቀቂያ ገንዘብ እንደተቀበሉ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡

ከዚያ ወዲህ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳረጋገጠው ከሆነ ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ2005 እስከ 2012 ድረስ 154 የመርከብ ዕገታዎች ሲፈጸሙ፣ በአጠቃላይ ለታጋቾች ማስለቀቂያ ወደ 413 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሏል፡፡

ጥናቶች እንዳረጋገጡት ከሶማሊያ የተነሱ የባህር ወንበዴዎች ለተከታታይ ዓመታት ባደረሱት የመርከብና የሠራተኞቻቸው ዕገታ የተነሳ የዓለም ንግድ እንቅስቃሴ ክፉኛ ነው የተናጋው፡፡ በዚህ ሕገወጥ የባህር ንግድ ውንብድና የተነሳ የዓለማችን ንግድ እስከ 16 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጥሞታል ነው የተባለው፡፡

ይህ ጉዳት የቀጥታ በዕገታው ያጋጠመ የንግድ ኪሳራ እንጂ ቀጥተኛ ባልሆነ ሁኔታ የደረሰውን ኪሳራና ጉዳት አይጨምርም ነው የሚባለው፡፡

ለምሳሌ በንግድ እንቅስቃሴ መጓተት ወይም በዕቃዎች ምልልስ ላይ የሚፈጠር መዘግየት ቀጥተኛ ካልሆኑ ጉዳቶች አንዱ ነው፡፡ ብዙ የመርከብ ድርጅቶች የባህር ውንብድናን ፍራቻ ሠራተኞች ለቀውባቸዋል ወይም ከመደበኛው በጣም የጨመረ ክፍያ ጠይቀዋቸዋል፡፡ መርከቦች ጉዟቸው ስለሚዘገይ ወይም የጉዞ መስመራቸው ስለሚቀየር የነዳጅ ፍጆታቸው በእጅጉ ያሻቀበ ሆኖም ነበር፡፡

የመርከብ ድርጅቶች ለሠራተኞችና ለነዳጅ የሚያወጡት ወጪ መጨመር ብቻ ሳይሆን፣ ለኢንሹራንስ የሚፈጽሙት ክፍያ ማሻቀቡም ሌላ ችግር ሆኖ ነበር፡፡ በጊዜው ኢትዮጵያ በምታንቀሳቅሳቸው የንግድ መርከቦች ላይ የደረሰ ጥቃት ባይኖርም፣ ከቻይና እስከ አውሮፓና አሜሪካ ድረስ በርካቶች በሶማሊያ የባህር ወንበዴዎች እንቅስቃሴ ሥጋት ገብቷቸው ታይተዋል፡፡ በጊዜው ይህን ችግር ለማስቆም የማይግባቡ አገሮች ሳይቀሩ በጋራ ቆመው በቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ ቀጣና የጦር መርከቦችን ሲያሰማሩ መታየታቸው የሥጋቱን ከፍተኝነት ያሳየ ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ እ.ኤ.አ. በማርች 2021 ኤቨር ጊቭን የተባለች የጃፓን መርከብ የግብፅ ስዊዝ ቦይን ስታቋርጥ አሸዋ ውስጥ ተቀርቅራ በአግድመት መተላለፊያውን በመዝጋቷ፣ በዓለም ንግድ እንቅስቃሴ ላይ ባህር ዘራፊዎችን ያስታወሰ ከባድ ጉዳት ፈጥራ ቆይታለች፡፡

ለስድስት ቀናት የቀይ ባህር ንግድ መተላለፊያ ኮሪደርን የዘጋችው ኤቨር ጊቭን በዓለም ንግድ እንቅስቃሴ ላይ በየቀኑ የዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንዳስከተለች መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ የግብፅ ባለሥልጣናት በስዊዝ መተላለፊያ የወደብ አገልግሎት በመስጠት ያገኙት የነበረውን ገቢ በማጣታቸው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ካሳ መጠየቃቸውም አይዘነጋም፡፡

የቀይ ባህር የንግድ ኮሪደር በግብፅ ስዊዝ ቦይ እንዲሁም በባብኤል መንዴብ ጠባብ መተላለፊያ ወሽመጥ የተነሳ ሁሌም ሥጋት እንዳጠላበት የሚኖር መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ የንግድ መተላለፊያ መስመር ለዓለማችን ከአሥር እስከ 40 በመቶ የንግድ ልውውጥ ግልጋሎት ይሰጣል ነው የሚባለው፡፡ በዚህ ቀጣና ጥቂት ችግር ያጋጠመ ቀን ኪሳራውና ጉዳቱ ከፍተኛ ነው የሚባለው፡፡

ይህ ጉዳት ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ የአፍሪካ አገሮች በተለያየ መንገድ ወላፈኑ እንደሚፈጃቸው ይነገራል፡፡

ከሰሞኑ እስራኤልን ለመበቀል በሚል የሁቲ አማፂያን እያደረሱት ባለው ጥቃት መስተጓጎል የገጠመው የቀይ ባህር ንግድ መተላለፊያ ኮሪደር ጉዳይ፣ በተለያዩ መንገዶች ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት፣ እንዲሁም በእስራኤል በሐማስ ግጭት የተነሳ የዓለም ኢኮኖሚ ከባድ መናጋት እንደገጠመው ሲነገር ቆይቷል፡፡ የዓለም የነዳጅ ግብይት ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ፣ ኢትዮጵያ በተከታታይ ጊዜያት የዋጋ ማስተካከያ ጭማሪዎች ስታደርግ መቆየቷ አይዘነጋም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ  ቤንዚን በሊትር 77 ብር ሲሸጥ፣ ናፍጣ ደግሞ 79 ብር እየተቸረቸረ ይገኛል፡፡ የዓለም ሰላምና መረጋጋት መሻሻል አሳይቶ የዓለም ነዳጅ ግብይት ተመልሶ የማይረጋጋ ከሆነ፣ በኢትዮጵያም የዋጋ ጭማሪው እንደሚቀጥል ነው የሚገመተው፡፡

በሌላ በኩል የዩክሬን ሩሲያና የእስራኤል የሐማስ ግጭቶች እንደ እህል፣ ማዳበሪያና የምግብ ዘይት በመሳሰሉ ወሳኝ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ መቃወስ አስከትለዋል፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ጭምር ተፅዕኖው ሲታይ ቆይቷል፡፡

ይህ ሁሉ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ባለበት አሁን ደግሞ የሁቲ አማፂያን ጥቃት የቀይ ባህር መተላለፊያን የንግድ እንቅስቃሴ ማስተጓጎሉ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እየተሠጋ ነው፡፡

ከዚሁ ቀጣናዊና አገራዊ ጉዳይ ጋር በተገናኘ የኢትዮጵያ የማሪታይም ባለሥልጣን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሥራ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ጥረት የተደረገ ቢሆንም ለጊዜው ምላሻቸው ባለመድረሱ ማካተት አልተቻለም፡፡

እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮች ይህ ጉዳይ ስላሠጋቸው ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የባህር ኃይል ወደ ሥፍራው ለመላክ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ታውቋል፡፡