
ከ 4 ሰአት በፊት
እስራኤል በምድር፣ በባሕር እና በአየር በተቀናጀ ሁኔታ የማያባራ ጥቃት እየፈጸመችባት ያለችው ጋዛ ፈራርሳለች።
ሕንጻዎች ወደ ፍርስራሽ ክምርነት ተቀይረዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል።
ከእነዚህም አብዛኞቹ ሕጻናት ናቸው። ለፍልስጤማውያኑ ከጥቃት ለማምለጥ የሚያስችል አንዳችም መሸሸጊያ ቦታ ጋዛ ውስጥ የለም ቢባልም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከጥቃት ለማምለጥ ሻል ያሉ ናቸው ብለው ወደሚያስቧቸው ቦታዎች ተሰደዋል።
አንዳንዶች ደግሞ በቤተክርስቲያን ውስጥ ተደብቀዋል።
ቤተ ክርስቲያን የተቀደሰ ስፍራ ነው በሚል መሸሸጊያ ነው ብለው ለመረጡት ግን ይህ ሃሳባቸው ፉርሽ ሆኗል።
በጋዛ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው ያሉ ዜጎች ከሞት ጋር መፋጠጣቸውን ዘመዶቻቸው ይናገራሉ።
በሆሊ ፋሚሊ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እህቷ እንደተጠለለች የምትናገረው ፊፊ ሳባ ብትወጣ ሊተኮስባት ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ ናት ብላለች።
መውጣት ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያኗም ውስጥ ተጠልሎ መቆየት ከጥቃት አያስመልጥም።
በባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ አንዲት እና ሴት ልጃቸው በእስራኤል አነጣጣሪ ተኳሾች ጥይት መገደላቸውን የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ገልጸዋል።
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ጥቃቱን አውግዘዋል።
“ናሂዳ ካሊል አንቶን የተባሉት እናት እና ልጃቸው ሳማር ካማል አንቶን ወደ መታጠቢያ ቤት ሲሄዱ በተኳሾች ተገድለዋል ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል” ሲሉም እሁድ ዕለት ባወጡት መግለጫ ተናግረዋል።
“አንዳንዶች ይህ ሽብርተኝነት ነው ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ጦርነት! አዎ ጦርነት ነው። ሽብርተኝነት ነው” ሲሉም አክለዋል።
በአሜሪካ መቀመጫዋን ያደረገችው እና የካቶሊክ እምነት ተከታይዋ የጋዛ ተወላጇ ፊፊ ሳባ እህቷ፣ የእህቷ ባለቤት እና ሁለቱ የ9 እና የ12 ዓመት ሕጻናት ልጆቻቸው በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ መውጫ እንዳጡ ገልጻ ከፍተኛ ስጋት እንዳሳደረባት ተናግራለች።
እህቷን በቀጥታ ማግኘት ባትችልም እሷን በቀን አንድ ጊዜ ማነጋገር በቻለ የቤተሰብ አባል በኩል ዜናቸውን እየሰማች እንደሆነ ለቢቢሲ አስረድታለች።
“መውጫ አጥተው ነው ያሉት። መንገዱን እንኳን በደንብ ማየት አይችሉም። አብዛኛውን ጊዜም ከዓለም በተቆራረጠ ሁኔታ ውስጥ ነው እየኖሩ ያሉት። ስልክም ሆነ ኢንተርኔት ማግኘት ፈታኝ ነው። ዜናም አያገኙም” ስትልም ታስረዳለች።
በቅርቡ እህቷ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ያለው ሁኔታ “በጣም ፈታኝ ነው” ብላ መናገሯንም ሰምታ ነበር።
እህቷ በዚያችንም ያሉበትን ሁኔታ በጣም ፈታኝ ነው ያለችበት ምክንያት እናት እና ልጅ መገደላቸውን በመመልከቷ መሆኑንም መረዳቷን ፊፋ ታስረዳለች።
በዚያች ቀንም ቤተሰቡ በቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ውስጥ መሬት ውስጥ በሚገኝ ስፍራ ለሁለት ሰዓታት ተደብቀው እንዳሳለፉም ሰምታለች። የተደበቁትም የእስራኤል ጦር በማንኛውም ተንቀሳቃሽ ነገር እየተኮሰ እንደሆነ በማመናቸው እንደሆነም ተናግረዋል።
“እናት እና ልጅ ጥይት ተተኩሶባቸው የተገደሉት ወደ መጸዳጃ እያቀኑ በነበረበት ወቅት በመሆኑ ወደ መጸዳጃ ቤትም ለመሄድ ፈሩ” ትላለች።
- ልብሳቸው ተገፎ ጋዛ ውስጥ በእስራኤል ወታደሮች የተያዙ ፍልስጤማውያን ወንዶችን የሚያሳይ ቪድዮ ይፋ ሆነ8 ታህሳስ 2023
- ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ 100 ሺህ ሕንፃዎች የወደሙባት የፍርስራሽ ክምሯ ጋዛ በሳተላይት ዕይታ2 ታህሳስ 2023
- “ሐሎ! ከእስራኤል ደኅንነት ቢሮ ነበር የምደውለው። ቤትህን ልናጋየው ትዕዛዝ ተሰጥቶናል”9 ህዳር 2023
የቤተ ክርስቲያኗ ውሃ ለጥቂት ቀናት ተቋርጦ ነበር።
ያላቸውም ምግብ የተመናመነ ነው። ለሦስት ሳምንታት ያህል የተቀቀለ ፓስታ ያለምንም ማጣፈጫ ተመግበዋል።
ባለፉት ሁለት ቀናትም ምግባቸው ተሟጦ እንዳለቀ ታስባለች።
የኢየሩሳሌሙ የላቲን ፓትርያርክ ቅዳሜ ዕለት እንደተናገሩት ሁለት ክርስቲያን እናት እና ልጅ የእህቶች ገዳም ተብሎ ወደሚጠራው ቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ወደሚገኘው ስፍራ ሲራመዱ በተተኮሰባቸው ጥይት ተመትተው ተገድለዋል።
“አንደኛዋ የቆሰለችውን ተሸክማ ለማዳን ስትሞክር ነው የተገደለችው” ሲል መግለጫው አክሏል።
በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉ ሌሎችንም ለመጠበቅ ሲሞክሩ ተጨማሪ ሰባት ሰዎች በጥይት ተመትተው መቁሰላቸውን ፓትርያርኩ አክለው ተናግረዋል።
በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ያሉት ሰዎች ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ እንዳልተሰጣቸው የገለጹት ፓትርያርኩ ግድያውንም “ጭካኔ የተሞላበት ነው” ሲሉ ፈርጀውታል።
ሁለቱ ሴቶች ከመገደላቸው በፊትም የእስራኤል ታንኮች 54 አካል ጉዳተኞች ባሉበት የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ በኩል መተኮሳቸውን ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት ብቸኛው የሕንጻው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ምንጭ የሆነው ጄኔሬተር በቃጠሎው መውደሙን እና አንዳንድ አካል ጉዳተኞችም አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያዎችን እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል ብለዋል።
የቤተ ክርስቲያኗን መግለጫ ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ኃይል “እንደእነዚህ አይነት አሳሳቢ በሆኑ ቦታዎች ላይ ደረሱ የሚባሉ ጉዳቶችን ትኩረት ሰጥቼ እከታተላቸዋለሁ” ብሏል።
በቤተ ክርስቲያኗ አቅራቢያ በሚገኘው ሸጃያ አካባቢ ወታደሮቹ ዘመቻ ማካሄዳቸውን ገልጾ “የጦሩ የመጀመሪያ ግምገማም በቤተ ክርስቲያኗ አካባቢ ሐማስ ይንቀሳቀስበታል በተባለ ስፍራ ነው” ብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ጉዳዩን በጥልቀት እየገመገመው እንደሆነም አስታውቋል።
በቤተ ክርስቲያኗ ላይ በዘፈቀደ ጥቃት ፈጽሟል በሚል ስለቀረበበት ክስም ቢቢሲ ጦሩን ጠይቆም ነበር።
ለፊፊም ቢሆን የእስራኤል ጦር ቤተ ክርስቲያኗን ለምን ኢላማ እንዳደረጋት ግልጽ አይደለም።
“ባለፉት 72 ቀናት ሆስፒታሎች እንዴት ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው፣ ትምህርት ቤቶች የጥቃት ኢላማ እንደሆኑ፤ ቤተ መጻህፍት፣ ገበያዎች እና ዳቦ ቤቶች እንደሚጠቁ አይተናል” ትላለች።
“[ የእስራኤልን] ትርክት ለማመን ከባድ ነው” ትላለች።
የዩናይትድ ኪንግደም የፓርላማ አባል የሆኑት ላይላ ሞራን እስራኤል በጋዛ የሚገኘው ቤታቸው ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ክርስቲያን ፍልስጤማውያን የሆኑ የቤተሰባቸው አባላት ከጥቃቱ ለመትረፍ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
“እስከ ገና ድረስ በሕይወት ይቆዩ እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም” የሚሉት የፓርላማ አባሏ ቤተሰባቸው ምግብም ሆነ ውሃ ተሟጦባቸው በችግር ላይ እንዳሉ ያስረዳሉ።
የእስራኤል ወታደሮች ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ገብተው በአንደኛው ሕንጻ ውስጥ ሰፍረው እንደሚገኙም የቤተሰቦቻቸው አባላት ነግረውኛል ብለዋል።
ቤተሰቦቻቸው የላኩላቸውን ፎቶ ቢቢሲ የተመለከተው ሲሆን፣ የሁለት ሰዎች አስከሬንም ከቤተ ክርስቲያኑ ሕንጻ ወጣ ብሎ በሚገኘው ጎዳና ላይ ይታያል። አስከሬኖቹ ለቀናት የሚያነሳቸው አጥተው እየበሰሰቡ መሆናቸውንም የላይላ ቤተሰቦች መናገራቸውን ገልጸዋል።
የእስራኤል ወታደሮች ቤተ ክርስቲያኗን ለምን የጥቃት ዒላማ እንዳደረጓትም ሆነ ምንም አይነት ማስጠንቀቂያም ሆነ በራሪ ወረቀቶች እንዳልበተኑ ተናግረዋል።
“ሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ በተመለከተ መሳለቂያ የሆነ ይመስላል” ብለዋል። እስራኤል እየፈጸመችው ያለው የተቀናጀ ጥቃት ሐማስን “ለማጥፋት ያለመ” እና ቡድኑ መስከረም መጨረሻ ወደ ጋዛ የወሰዳቸውንም ታጋቾች ለመታደግ ነው ትላለች።
የእስራኤል ጦር በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አልፈጽምም ሲል ይሰማል። እስራኤል እየፈጸመችው ባለው የማያባራ ጥቃት 20 ሺህ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በአብዛኛው የተገደሉት ሕጻናት ሲሆኑ 50 ሺህ ሰዎችም መቁሰላቸውን ከጤና ሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።