
ከ 3 ሰአት በፊት
ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2009 የተመሰረተውንና የአምስት አገራት ጥምረት የሆነውን የብሪክስ ቡድን ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ባለፈው ነሀሴ ተቀባይነት አግኝቷል።
የኢትዮጵያን ጨምሮ የስድስት አገራትን የአባልነት ጥያቄ የተቀበለው የጥምረቱ ጠቅላላ ጉባኤ ቡድኑን ማስፋት ላይ ወሳኝ የተባለውን ውሳኔ አሳልፏል።
ከ40 በላይ አገራት ቡድኑን ለመቀላቀል ፍላጎት ማሳየታቸውንና 20 የሚሆኑት ደግሞ ይፋዊ የእንቀላቀል ጥያቄ ማቅረባቸው ተነግሯል።
ስድስቱ አዲስ አባል አገራት ከምዕራባዊያኑ አዲስ ዓመት ጀምሮ በይፋ ብሪክስን ይቀላቀላሉ።
ቡድኑ 40 በመቶውን የዓለም ሕዝብና 26 በመቶውን የዓለም ምጣኔ ሀብት ይሸፍናል።
ብሪክስ በማደግ ላይ ላሉ አዳዲስ አገራትና ገበያቸው ትልቅ እድልንና ትብብርን ይዞ ብቅ እንደሚል ይታመናል። ኢትዮጵያስ ከዚህ ስብስብ በተጨባጭ ምን ታገኛለች? ትርፍና ኪሳራዋ ምንድን ነው?
- ኢትዮጵያ አባል ለመሆን ስለጠየቀችው ‘ብሪክስ’ የምናውቃቸው አራት ነጥቦች7 ሀምሌ 2023
- ኢትዮጵያን በአባልነት የተቀበለው ብሪክስ የአሜሪካን ልዕለ ኃያልነት ይገዳደር ይሆን?31 ነሐሴ 2023
- ብሪክስን መቀላቀል ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ምን ያስገኛል?26 ነሐሴ 2023
የኢትዮጵያ የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች ማኅበር (Ethiopian Economics Association) “ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ምን ያስገኝላታል? እይታና ዓለም አቀፍ አዝማሚያ” ሲል ባደረገው ጥናት የአገሪቱን ትርፍና ኪሳራ በባለሞያዎች አይን ተመልክቷል።
ማኅበሩ ካሉት አምስት ሺህ ገደማ የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ውስጥ 230 የሚሆኑ ከፍተኛ ባለሞያዎችን እይታ የጠየቀው ጥናቱ፣ የኢትዮጵያን የብሪክስ አባልነት ትርፍና ኪሳራ እንዲሁም የቤት ስራዎች አስቀምጧል።
የጥናቱ መሪ ዶ/ር ደግዬ ጎሹ እንደ ዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ፈንድ ያሉ የገንዘብ ተቋማት ዓላማቸውን ባለመፈጸማቸው እንደ ብሪክስ ያሉ ቡድኖች እንዲመሰረቱ አድርጓል ይላሉ።
ኢትዮጵያም ብሪክስን ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ሲያገኝ እንደ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ተመልክታዋለች።
ይኹን እንጂ 50 በመቶ ገደማ የሚሆኑ በጥናቱ የተሳተፉ ባለሞያዎች አገሪቱ የገጠማት የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ማዕቀብ ጥምረቱን እንድትቀላቀል ገፋፍቷታል ባይ ናቸው።
“መንግሥት የሚለው አሁን በራሷ ሜሪት [አቅም] ነው፤ እንዲህ ስለሆነች ነው፤ በአይዲዮሎጂዋ ነው የሚለው ነገር አለ። ያ አይደለም ምክንያቱ፤ ምዕራባዊያን ኃይሎች ከምንላቸው የገንዘብ ተቋማት ብዙ ጫናዎች ስለመጣባት፤ ብድር የመያዝ ነገርም ስለመጣባት፤ ጫና ስለበዛ ነው እንጂ ተገምግሞ አይደለም። መግባቷ መጥፎ ነው አይደለም፤ የመግባቷ ግፊቱ ይሄ ነው ብለው [ባለሞያዎቹ] ያስቀመጡት ነገር አለ” ብለዋል።
አገሪቱ አዲስ ምጣኔ ሀብት በመሆኗ ብሪክስን ተቀላቅላለች ያሉ ባለሞያዎች ደግሞ 47 በመቶ ናቸው።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ምን ያህል ጠቀሜታ አለው የሚለውን በአሀዝ መግለጽ ባይቻልም፤ 70 በመቶ የሚሆኑት የጥናቱ ተሳታፊ ባለሞያዎች ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ እንዳለው ያምናሉ።
ሆኖም ግን ፖለቲካዊ ዋጋው ከፍተኛ ነውም ብለዋል።
51 በመቶዎቹ ባለሞያዎች ከዋጋው ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል ቢሉም፤ 25 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ የሚያስከፍለው ዋጋ ያመዝናል ባይ ናቸው።

ከዚህ ዋጋ ውስጥ በዋናነት አብዛኞቹ የጥናቱ ተሳታፊ የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች አገሪቱ አዳዲስ ብድሮችን ልትከለከል ወይም ሊቀነስባት ይችላል የሚል እምነት አላቸው።
ከሚጠበቁ ተጽዕኖዎች ውስጥ ለመርሃ ግብሮች የሚለቀቅ ገንዘብ ላይ እክል፣ የመገበያያ ገንዘብ ብር የመግዛት አቅሙ እንዲዳከም ጫና ማድረግ፣ በመንግሥት ላይ ፖለቲካዊ እርምጃ እንዲሁም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ጫና እንደሚፈጥር መጠቆማቸውን ዶ/ር ደግዬ ተናግረዋል።
ከውጫዊ ተጽዕኖዎች ባለፈም ውስጣዊ ተጽዕኖዎች እንዳሉም ባለሞያዎቹ አመልክተዋል።
ከዚህም ውስጥ በጥምረቱ ላይ የሚደርስ የምዕራባዊያን ጫና፣ የብሪክስ በተለይም የልማት ባንኩ አቅም የሚገኝበት ሲሆን የ11ዱም የብሪክስ አባል አገራት የጥቅም ግጭትም የሚጠበቅ ነው ሲሉ ለአብነት ግብጽና ኢትዮጵያን ያነሳሉ።
ኢትዮጵያ ከምዕራባውያንና በእነሱ ይዘወራሉ ከሚባሉት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ ተደጋጋፊ መሆኑ፣ እንዲሁም በአቅም አለመፈርጠሟ የብሪክስ ተጠቃሚነቷን እንደሚገድበው ተመራማሪው ተናግረዋል።
“በአጭር ጊዜ ውስጥ ከብሪክስ ከፍተኛ ጥቅም ወይም ሙሉ ለሙሉ ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ልንወጣ የምንችልበት እድል በእኛ አቅም ምክንያት የለም” ብለዋል።
ዶ/ር ደግዬ፣ ብሪክስ ከተመሰረተባቸው ሰባት ዓላማዎች ውስጥ እንደ ዓለም አቀፍ ንግድ ያሉ ጥቅሞችን ለማግኘት የኢትዮጵያ የቤት ስራ ከፍተኛ ነው ይላሉ።
በዋናነትም የብሔራዊ ባንክን አቅምና ገለልተኝነትም ያነሳሉ።
“ንግድ ወይም ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ከተባለ እነሱ እኛ ጋር መጥተው በደንብ ሊሰሩ የሚችሉበት እድል መኖር አለበት። የንግድ ስርዓቱ በጣም የተሻለ መሆን አለበት። የኢትዮጵያ የገንዘብ ስርዓት፣ የገንዘብ ገበያ እድገት፣ አስተዳደሩ የመሳሰሉት በሙሉ [ከብሪክስ አባላት ጋር] የሚወዳደሩ አይደሉም። ለዚህ ብቁ የሚያደርጉን ብዙ የቤት ስራዎች አሉብን” በማለት አገሪቱ ዝግጁ እንድትሆን ምክረ ሀሳባቸውን ያቀርባሉ።
በመሆኑም የአገሪቱ ጥቅም “ሁኔታዎች” ላይ የተንጠለጠለ እንደሆነ ጠቁመዋል።
“ኢትዮጵያ ከብሪክስ የማትጠቀም ከሆነ በአብዛኛው ሊሆን የሚችለው በራሳችን ችግር ነው” በማለት የሚጎድሉ የቤት ስራዎችን ያነሳሉ።
ኢትዮጵያ ከብሪክስ (ምስራቅ) እና ከምዕራባዊያን ጋር የሚኖራት ግንኙነት ሚዛኑን ሳታዛንፍ መሳ ለመሳ ማስኬዱ እንደሚጠቅማትም ባለሞያው ተናግረዋል።
“ቢያንሰ ለአጭር ጊዜ ኢትዮጵያ ከሁለቱም ጋር መስራት ነው። ባለፉት ዓመታት [ከምዕራባዊያን ጋር] ከፍተኛ ጥገኝነት አለብን። ብዙ የልማት ድጋፎች፤ ብድሮች የመሳሰሉት ከእነዚህ ተቋማት ነው ወይም እነዚህ ተቋማትን በበላይነት ከያዙ አገራት የሚመጣ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ቆርጠን የምንተወው ነገር አይደለም፤ አንችልምም። ቢያንስ ለአጭር ጊዜ ከሁለቱም ጋር መስራትን አቅማችን በራሱ የሚያስገድደን ነው” ይላሉ።