ሱፐር ሊግን የሚቃወሙ መልእክቶች

ከ 17 ደቂቃዎች በፊት

አዲሱን የአውሮፓ ሱፐር ሊግ የጠነሰሱት አዘጋጆች፤ ደጋፊዎች እና ክለቦች በአውሮፓ ሱፐር ሊግ ሐሳብ መሳባቸው አይቀርም ይላሉ።

በአውሮፓውያኑ 2021፤ 12 ቡድኖች የአውሮፓ ሱፐር ሊግ የተሰኘ የአህጉሪቱን እግር ኳስ አስተዳዳሪ የሚገዳደር ሊግ ለማቋቋም አቅደው ነበር።

ሐሙስ ዕለት የአውሮፓ ፍትሕ ችሎት የአውሮፓ ክለቦችን እንዳይሳተፉ መከልከል ሕጋዊ አይደለም፤ እንደ አዲስ የተጠነሰሰው ሐሳብም ፍትሐዊ አይደለም ብሏል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበራት ኃላፊ አሌክሳንደር ቼፌሪን አዲሱን የሱፐር ሊግ ሐሳብ ተሳልቀውበታል።

ሐሙስ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ቼፌሪን “እግር ኳስ ለሽያጭ የሚቀርብ አይደለም” ብለው ሁለት ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድር ለማየት እንደጓጉ ተናግረዋል።

“የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ። እኛ ልናስቆማቸው አንችልም” ብለዋል።

ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ቡድኖች መካከል ስድስቱ በ2021 ሱፐር ሊግ እንዲቋቋም ሐሳብ ሲቀርብ ለመሳተፍ ወስነው ነበር።

ነገር ግን ሐሙስ ዕለት ከስድስቱ ቡድኖች መካከል አራቱ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበር ሐሳብ ላለማፈግፈግ ቃል ገብተዋል።

ኤ22 የተባለው የሱፐር ሊግ አዘጋጅ ድርጅት መሠረት አዲሱ ሐሳብ እንደሚያሳየው በሊግ አወቃቀር 64 የወንድ እና 32 የሴት ቡድኖች ይቋቋማሉ።

የአውሮፓ ሱፐር ሊግ በየዓመቱ ወደታች የሚወርዱና ወደላይ የሚወጡ ቡድኖች የሚኖሩት ሲሆን ቋሚ አባላት ግን አይኖሩትም።

ከሁለት ዓመት በፊት የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ሐሳብ ሲነሳ ከመላው ዓለም ከደጋፊዎችና ከአውሮፓ ሊጎች ከፍተኛ እንዲሁም ከመንግሥታት ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን በ72 ሰዓታት ውስጥ ዕቅዱ ሊከሽፍ ችሏል።

በአውሮፓ ያሉ የሊግ ውድድሮች አዲሱን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ለማድረግ ጊዜ አልፈጀባቸውም።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ የተሰኘ ሐሳብን ሙሉ በሙሉ እንደሚቃወመው ግልፅ አድርጓል።

የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ባለድሎቹ ማንቸስተር ሲቲዎች የአውሮፓ ሱፐር ሊግን በተመለከተ ሐሳባቸውን እንዳልቀየሩ ገልጸዋል።

ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ቼልሲ እና ቶተንሃምም እንዲሁ የሱፐር ሊግን ሐሳብ የተቃወሙ ሲሆን ባየር ሚዩኒክ ደግሞ “የሱፐር ሊግ በር ተዘግቷል” ሲል መግለጫ አውጥቷል።

ሲቲ፣ ዩናይትድ፣ ቼልሲ እና ስፐርስ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ መጀመሪያ ሲቋቋም አባል የነበሩ እና በደረሰባቸው ተቃውሞ ምክንያት ራሳቸውን ያገለሉ ክቦች ናቸው።

የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ጣጣ የጀመረው በአውሮፓውያኑ 2021 የእንግሊዞቹን አርሰናል፣ ቼልሲ፣ ሲቲ፣ ሊቨርፑል፣ ዩናይትድ እና ቶተንሃምን ጨምሮ 12 ክለቦች ተገንጥለው የራሳቸውን ሊግ ለመመሥረት ባቀዱበት ወቅት ነው።

ከ12 ክለቦች መካከል የስፔኖቹ ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ሐሳባቸውን ሳይቀይሩ ሲቀሩ ሌሎቹ ቡድኖች አፈገፈጉ።

አሁን ሐሳቡ እንደ አዲስ ሲነሳ ተቃውሟቸውን ካላሰሙ ክለቦች መካከል ማድሪድ እና ባርሴሎና ይገኙበታል።