በቻይና የቀዶ ህክምና እያደረገላቸው የነበሩትን ህመምተኛ በቡጢ የደበደበው ዶክተር

22 ታህሳስ 2023, 11:44 EAT

በቻይና የቀዶ ህክምና እያደረገላቸው የነበሩትን ህመምተኛ በቡጢ የደበደበው ዶክተር ቁጣን ቀሰቀሰ።

የቻይና ባለስልጣን በሆስፒታሉ የተከሰተውን ድብደባ አስመልክቶ ምርመራ መክፈታቸውን አስታውቀዋል።

በዚህ ሳምንት በቻይና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተለቆ በርካቶች ያዩት ቪዲዮም ከፍተኛ ቁጣንም ቀስቅሷል።

ሆስፒታሉን በበላይነት የሚያስተዳድረው ኤየር ቻይና ድብደባውን ፈጽሟል ያለውን የቀዶ ህክምና ባለሙያን እንዲሁም ድርጊቱ የተፈጸመበትን የሆስፒታሉን ዋና ስራ አስፈጻሚም አሰናብቷል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ የኤየር ቻይና አስተያየትን ጠይቆ ነበር።

ቪዲዮው የአይን የቀዶ ህክምና እየተደረገላቸው የነበሩት ህመምተኛ ሶስት ጊዜ በዶክተሩ በቡጢ መመታታቸውን ያሳያል።

የአይን ሆስፒታሎችን በበላይነት የሚያስተዳድረው ኤየር ቻይና ክስተቱ በአውሮፓውያኑ 2019 በደቡብ ምዕራባዊቷ ቻይና በጉይጋንግ ሆስፒታል የተፈጸመ ነው ብሏል።

ህምምተኛዋ የ82 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ሲሆኑ “በቀዶ ህክምናው ወቅት በተሰጣቸው ማደንዛዣ ምክንያት መቁነጥነጥ እየተሰማቸው” ነበር።

እጃቸውን እንዲሁም አይናቸውን በርካታ ጊዜ ማንቀሳቀሳቸውንም መግለጫው ጠቅሷል።

ግለሰቧ ዶክተሩ ያስጠነቅቃቸው የነበረውን የማንዳሪን ቋንቋም ስላልገባቸው ግራ ተጋብተው እንደነበር የተገለጸ ሲሆን “በድንገተኛ ህክምና ላይ የነበሩት ህመምተኛ በከፋ ሁኔታ ተይዘዋል” ተብሏል።

የአካባቢው ባለስልጣናት ህመምተኛዋ በድብደባው ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበር እና ግንባራቸውም በልዞ እንደነበር አስረድተዋል።

ከቀዶ ህክምናውም በኋላ የሆስፒታሉ አስተዳዳሪዎች ለህመምተኛዋ ይቅርታ ጠይቀው 500 ዩዋን (70 ዶላር) በካሳነት መስጠታቸውንም የህመምተኛዋ ልጅ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።

በተጨማሪም የእናቱ ግራ አይን እንደታወረ የገለጸ ሲሆን ከዚህ ክስተት ጋር ስለመያያዙ ግልጽ አይደለም።

ኤየር ቻይና ሆስፒታሉ ስለ ጉዳዩ ለዋናው መስሪያ ቤት ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅበት ነበር።

ሐሙስ ዕለትም የጉይጋንግ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ከስራ መታገዳቸውን እንዲሁም የሆስፒታሉ ዲን የሆነው የቀዶ ህክምና ባለሙያም “ሌሎች ያልተጠቀሱ ጥሰቶችን ጨምሮ በተደጋጋሚ በፈጸመው ከባድ ጥሰቶች” መባረሩ ተነግሯል።

ምንም እንኳን ክስተቱ የተፈጸመው በአውሮፓውያኑ 2019 ቢሆንም የህዝብ ትኩረት ያገኘው ታዋቂዋ ቻይናዊት ዶክተር አይ ፌን ድብደባውን የሚያሳይ የሲሲሲቲቪ ቪዲዮ ማጋራታቸውን ተከትሎ ነው።

ዶክተሯ በውሃን ላይ የተከሰተውን የኮቪድ ወረርሽኝን በተመለከተ ህዝቡን ካስጠነቀቁ የዶክተሮች ቡድን መካከል አንዷ ሲሆኑ ይህንንም ቪዲዮ ሁለት ሚሊዮን ተከታዮች ባላቸው ዌይቦ በተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አጋርተዋል።