December 22, 2023 – Konjit Sitotaw
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት መስሪያቤት ዉስጥ የሚሰሩትን ሰራተኞች ዛሬ አርብ ታህሳስ 12/2016 ዓ.ም. እንደሚሰጥ ቢነገርም በመፈተኛ ቦታቸዉ የተገኙት ተፈታኞች ሳይፈተኑ ለረዥም ሰዓታት በፌዴራል ፖሊስ መጠበቃቸውን ተናግረዋል ።
ለካፒታል የተናገሩት የመንግስት ሰራተኞች ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ 4 እና 5 ኪሎ ለመፈተን ወደ ተቋሙ ከ 6:30 ጀምሮ በተመደቡበት መፈተኛ ክፍል ቢደርሱም እስከ 11:30 ድረስ ከፌዴራል ፖሊስ በስተቀር ማንም ፈታኝ ባለመምጣቱ ከረዥም ሰዓታት እንግልት በኃላ እንዲበተኑ መደረጉ ተሰምቷል።
በቅርቡ ለሚተገበረዉ የሠራተኞች ድልድል ሲባል ከ14 ሺህ በላይ የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኞች ለፈተና እንደሚቀመጡ የተነገረ ቢሆንም ዛሬ 13865 ተማሪዎች ሳይፈተኑ በምን ምክንያት እንደሆነ ባልተገለፀበት መረጃ ላልተወሰነ ቀን መራዘሙን እንደሰሙ የካፒታል ምንጮች ተናግረዋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት እና አስተዳደር፣ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር፣ ትራንስፖርት፣ ፐብሊክ ሰርቨሲ እና ሰው ሀብት ልማት፣ ፕላን እና ልማት፣ ሥራ እና ክህሎት፣ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮዎች ቤቶች ኮርፖሬሽን ጨምሮ አጠቃላይ ከ13 ሺህ በላይ ሰራተኞች ፈተናዉን አለመዉሰዳቸዉ ተገልጿል።
በወቅቱ ረዥም ሰዓታት ፈተናዉን በመጠባበቃቸዉ ምክንያት የጩኸት ድምፅ ያሰሙ ሰራተኞች ለእስር መዳረጋቸውን እና የተለያዩ እንግልቶች እንደደረሰባቸው ተናግረዋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ከሚኖሩ ዳይሬክተሮች እና ቡድን መሪዎች መካከል ተመሳሳይ የብሔር ማንነት ያላቸው አመራሮች ብዛት ከ40 በመቶ እንዳይበልጥ ሊያደርግ መሆኑ መነገሩ ይታወሳል ።