የጦር መሣሪያ

23 ታህሳስ 2023, 08:56 EAT

የሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አብደል ፋታሕ አል-ቡርሐን ዋድ ማዳኒ ከተማ በተቀናቃኝ ኃይሎች እጅ የወደቀችው “በችላ ባይ” ኮማንደሮች ምክንያት ነው ሲሉ ወቀሱ።

የገዚራ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው ዋድ ማዳኒን ጦሩ ጥሎ የወጣው ለመከላከል በቂ ጥረት ሳያደርግ ነው ብለዋል።

ገዚራ ላለፉት ስምንት ወራት ደኅንነቱ የተጠበቀ አካባቢ ተደርጎ ስለተወሰደ ከ300,000 በላይ ሰዎች ተጠልለውበታል።

ዋድ ማዳኒ ከተማ ከተያዘች በኋላ አል-ቡርሐን በይፋ ንግግር ሲያደርጉ የመጀመሪያው ነው።

“እያንዳንዱን ችላ ባይ ኮማንደር ተጠያቂ እናደርጋለን። ከተማዋን ለቀው የወጡ ያለ ርህራሄ ተጠያቂ መደረጋቸው አይቀርም” ብለዋል።

ጦሩ እንዴት “ድንገት ከከተማዋ እንደወጣ” ምርመራ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ጦሩ በመውጣቱ ተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል (አርኤስኤፍ) ከተማዋን መቆጣጠር ችሏል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አጠቃላይ ገዚራ ግዛትን እንደተቆጣጠረ ቢገልጽም ቢቢሲ ይህንን ማረጋገጥ አልቻለም።

ግጭት ሊባባስ ይችላል በሚል ፍራቻ በአቅራቢያው ያሉ የተራድኦ ሠራተኞች ለቀው እየወጡ ነው።

ላለፉት ስምንት ወራት ጦሩና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጦርነት ውስጥ ናቸው።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሱዳን መዲና ካርቱምን እና የዳርፉር ግዛትን 70 በመቶ መያዙ ይነገራል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከካርቱም ሸሽተው በጀዚራ ከተማ አል ማዳኒ ተጠልለዋል።

ኢስላሚክ ሪሊፍ የተባለው ተቋም ኃላፊ ኤልሳዲግ ኤልኖር በዚህ ከተማ ሳለ ነበር ግጭቱ የተነሳው።

በቦታው ያሉት አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ስለሆኑ ተደናግጠው እንደነበር ለቢቢሲ ገልጿል።

“ገና ከደረሰባቸው ድንጋጤ አልወጡም። አሁን ድጋሚ ወደሌላ ቦታ ሊሸሹ ነው። የት እንደሚሄዱና ማን እንደሚረዳቸው አያውቁም” ይላል።

ከተማዋ እርዳታ የሚሰጥባት በመሆንም ካርቱምን ተክታ ነበር።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከተማዋን ሲቆጣጠር ግን እርዳታ ሰጭዎች ሸሽተው ወጥተዋል።

ኢመርጀንሲ ኤንጂኦ የተባለው ተቋም የፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ጂና ፓርቴላ ሸሽተው እንደወጡ ትናገራለች።

የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው እያከሟቸው የነበሩ ሕሙማን የት እንደሚገኙ ማወቅ እንዳልቻሉ ትናገራለች።

“በጥቂት ቀናት ያሉበትን ማወቅ እንችላለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ትላለች።

አንድ የከተማዋ ነዋሪ እንዳሉት በከተማዋ ሱቆችና ሆስፖታሎች ተዘግተዋል።

ከከተማዋ የሸሹ ሲቪሎችና እርዳታ ሰጭዎች አሁን በገዳሪፍ፣ ሰነርና ዋይት ናይል ግዛቶች ለመጠለል ተገደዋል።

ኢስላሚክ ሪሊፍን ወደ ገዳሪፍ ለማዘዋወር እንደታሰበ ኃላፊው ይናገራል።

“ሁሉም ሰው ተደናግጧል። በገዳሪፍ ያሉትም ሳይቀሩ ጦርነቱ እዛ እንደሚደርስ ሰግተዋል” ይላል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ወደ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ገደማ በጦርነቱ ሳቢያ ተፈናቅለዋል።

የተመድ ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ እንደሚሉት የሱዳን ጦርነት በዓለም ከፍተኛው የተፈናቃዮች ቁጥር የሚመዘገብበት ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል።

የቀድሞው መሪ ኦማር አል-በሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ አሁን ጦርነት ውስጥ የገቡት ሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች በጋራ በሥልጣን ይቆያሉ ተብሎ ነበር።

ሆኖም ግን ባለመግባባታቸው ጦርነቱ ተነስቷል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ከመፈናቀላቸው በተጨማሪ ካርቱም ላይ ውድመት ደርሷል፣ ሰብአዊ ቀውስም ተከስቷል።

ጦርነቱ በዳርፉር ጎሳ ተኮር ግድያዎች መልሰው እንዲቀሰቀሱም ምክንያት ሆኗል።