
23 ታህሳስ 2023, 08:56 EAT
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት የጋዛ ሰርጥ ተጨማሪ ዕርዳታ እንዲገባ የሚጠይቀውን የውሳኔ ኃሳብ አጸደቀ።
ምክር ቤቱ ወደ ጋዛ የሚገባውን ዕርዳታ ማጠናከር ቢደግፍም አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥሪ ማድረግ ተስኖታል።
ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላትና የምክር ቤቱ ቋሚ አባል አሜሪካ ውሳኔውን ውድቅ እንዳታደርገውም በሚል ለቀናት ድርድር ከተካሄደም በኋላ ነው ውሳኔው ማለፍ የቻለው።
አሜሪካ የእስራኤል ቁልፍ አጋር ስትሆን ከፍተኛ ወታደራዊ እርዳታም በማድረግ ታግዛታለች።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ወደ ጋዛ ዕርዳታ ለማድረስ ዋነኛው ችግር “የእስራኤል የማያባራ እና ቀጣይነት ያለው ጥቃት” መሆኑን አስረድተዋል።
ጦርነቱ በዚህ ከቀጠለም የጋዛ ህዝብ ለከፋ ረሃብ እንደሚጋለጥም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተደጋጋሚ አስጠንቅቋል።
መስከረም መጨረሻ ሐማስ በእስራኤል ባደረሰው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች ሲገደሉ 240 ሰዎች ደግሞ ታግተዋል። እስራኤል ለዚህ ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ ነው በሚልም የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት እየፈጸመች ትገኛለች።
በነዚህም ጥቃቶች ቢያንስ 20 ሺህ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
- ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት የጋዛ ነዋሪዎች ከሞት ጋር ተፋጠዋል22 ታህሳስ 2023
- ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ 100 ሺህ ሕንፃዎች የወደሙባት የፍርስራሽ ክምሯ ጋዛ በሳተላይት ዕይታ2 ታህሳስ 2023
- ልብሳቸው ተገፎ ጋዛ ውስጥ በእስራኤል ወታደሮች የተያዙ ፍልስጤማውያን ወንዶችን የሚያሳይ ቪድዮ ይፋ ሆነ8 ታህሳስ 2023
ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ህጻናት መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ከሚገኘው የጤና ሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የጸጥታው ምክር ቤት ጋዛን በተመለከተ አርብ ዕለት ያሳለፈውን የውሳኔ ሃሳብ ያስተዋወቀችው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ናት።
ድምጽ ከመሰጠቱ ከደቂቃዎች በፊት ከአምስቱ ቋሚ የምክር ቤት አባላት አንዷ የሆነችው ሩሲያ አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲጨመርበት ማሻሻያ ሃሳብንም አቅርባ ነበር።
ያለ ተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ ተጨማሪ ጥቃቶችን እንድትፈጽም ነጻነት የሚሰጥ ነው ስትልም ተከራክራለች።
የሩሲያ ማሻሻያ ውድቅ የተደረገ ሲሆን ሩሲያ እና አሜሪካም ምክር ቤቱ ያሳለፈውን ውሳኔ በድምጸ ተአቅቦ አልፈውታል።
ሌሎች 13 የምክር ቤቱ አባላት ግን “ግጭትን ለማቆም” ሁኔታዎችን ማመቻቸት የሚለውን የውሳኔ ኃሳብ ደግፈውታል። የውሳኔ ኃሳቡ በጋዛ የተራዘሙ የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ፋታዎችን እንዲሁም ዕርዳታ ለማስገባት የማመላለሻ ኮሪደሮችን መክፈትን ያለመ ነው።
በጋዛ ሰርጥ ላሉ የፍልስጤም ሰላማዊ ህዝቦች አፋጣኝ፣ ያልተገደበ፣ ያልተቆራረጠ እርዳታ እንዲደርስ ሁሉም ወገኖች ሊያመቻቹ እና ሊፈቅዱም ይገባል ብሏል።