የካናዳ መልክዓ ምድር

23 ታህሳስ 2023

የምዕራቡ ዓለምን ለመኖሪያነት የሚመርጡ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ለበርካታ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎች ካናዳ ተመራጭ ሆናለች።

በተለይም በጥቂት ዓመታት ውስጥ በምቹነቷም ሆነ በተደራሽነቷ ምክንያት የመኖሪያ ቪዛ የሚጠይቁባት ተመራጭ አገር ሆናለች።

ለበርካታ የአፍሪካ እና የተለያዩ አገራት ሠራተኞች በሯን የከፈተችው ካናዳ፣ ቪዛ እና የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘትም ቀለል ያለ እንደሆነም ይናገራል።

ካናዳ ባላት ክፍት የኢሚግሬሽን ፖሊሲ ምክንያት በርካታ የውጭ አገራት የንግድ ባለቤቶችም መዳረሻቸው አድርገዋታል።

ለኢትዮጵያውያን እና ለአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን በምዕራቡ ዓለምም መስፈርት ካናዳ በምቹነት የምትመረጥ አገር ሆናለች።

የታዋቂው ኢኮኖሚስት ጋዜጣ አካል እና ምርምሮችን እንዲሁም ትንተናዎችን የሚያዘጋጀው ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት ‘ግሎባል ሊቨቢሊቲ ኢንዴክስ’ በየዓመቱ ለነዋሪዎች ምቹ የሆኑ ከተሞችን ደረጃ ያስቀምጣል።

ለዚህም የዓለማችን 173 ከተሞችን ገምግሞ ደረጃ የሚሰጥ ሲሆን፣ በዘንድሮው ግምገማውም ከአስሩ ምርጥ ከተሞች ውስጥ ሦስቱ የካናዳ ከተሞች መሆናቸውን ይፋ አድርጓል። ካናዳ በምቹነት ዝርዝር ውስጥ ከአስሩ ሦስት ከተሞችን በማስመረጥ ከፍተኛውን ቦታ ይዛለች።

ተቋሙ ከተሞቹን ሲመርጥ መስፈርት ያደረጋቸው መረጋጋት፣ የጤና ሥርዓት፣ ባህል እና ከባቢያዊ ሁኔታቸውን እንዲሁም የትምህርት እና የመሠረተ ልማት ሽፋንን በማጤን ነው።

በአስሩ ምርጥ ከተሞች ውስጥ የተካቱት ሦስቱ የካናዳ ከተሞች ቫንኮቨር፣ ካልጋሪ እና መዲናዋ ቶሮንቶ ናቸው።

ቫንኮቨር በአምስተኛ ደረጃ ስትቀመጥ፣ ካልጋሪ ከጄኔቫ ጋር ሰባተኛ ደረጃ እንዲሁም ቶሮንቶ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ከተሞቹ ምርጥ በሆነ የጤና ሥርዓት እና ጥራት በተሞላው ትምህርት ሽፋን የሚታወቁ ሲሆን፣ ለእነዚህም አዎንታዊ ትሩፋቶች የመንግሥት ፖሊሲዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ካናዳውያን ይናገራሉ።

“ተራማጅ ፖለቲካችን እንዲሁም ሁለንተናዊ የሆነው የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ካናዳን ለመኖሪያነት የተመረጠች ስፍራ ያደርጋታል” በማለት የቫንኮቨር ነዋሪ የሆኑት ሳማንታ ፋልክ ያስረዳሉ።

“ዶክተር ለመጎብኘት ወይም ልጄን ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ ገንዘብ በሚያስጨንቅበት ሁኔታ ወይም የካንሰር ታማሚዎች ለመታከም ሙሉ ጥሪታቸውን በሚያሟጥጡበት አገር ውስጥ መኖርን አላስበውም” ሲሉም እንዴት ካናዳ የጤና ሽፋን ሥርዓት ዜጎችን ያማከለ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የካናዳ መልክዓ ምድር

በካናዳ የእንክብካቤ ሥርዓቱ ፖለቲከኞችን ወይም ሕግ አውጪዎችን ብቻ ያማከለ አይደለም። የሰዎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ማኅበረሰብ አቀፍ ጥረቶች አሉ። ነዋሪው በሙሉ የማኅበረሰቡ አካል የሚሆንበትም መንገድ ኑሮን በተለየ መንገድ እንዲያዩ ያደርጋል።

“በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚደረጉ ድጋፎች፣ አረጋውያን ለመደገፍ የሚደረጉ ጥረቶች እንዲሁም ትንንሽ የንግድ ሥራ ባለቤቶችን ለመደገፍ የሚደረጉ ጥረቶች የአገራችን መለያዎች ናቸው። ካናዳውያን ወዳጅነት በመመሥረት እና በመደጋገፍ ይታወቃሉ” ይላሉ የቫንኮቨር ከተማ ነዋሪ የሆኑት እና ኦርጋናይዝድ ጄን የተሰኘ ሕይወት እና ንግድን የሚያደራጅ ድርጅት የሚመሩት ጄን ስቶለር።

“ይህ የመደጋገፍ እና የወዳጅነት ስሜት ነዋሪዎች በግል እና በሙያዊ ሕይወታቸው የሚያድጉበት እንዲሁም እርካታ የሚያገኙበት አዎንታዊ ከባቢን ያበረታታል” ይላሉ።

ካናዳ በሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎቶች እና ጎዳናዎች የምታፈሰው መዋዕለ ንዋይ በትልልቅ ከተሞቿ መጓጓዝን ቀላል ያደርገዋል። በካናዳ ከተሞች የግልዎት መኪና አያስፈልግዎትም።

ከተማዋ ውስጥ እንደፈለጉ የሚጓዙበት ባቡር፣ አውቶብስ በቀላሉ በየትኛውም ሰዓት፣ ቀን ተሌት ሳይሉ ያገኛሉ። በሞንትሪያል፣ ካልጋሪ እና ቶሮንቶ የኖሩት ሳማንታ እስከ 24 ዓመታቸው ድረስ መንጃ ፈቃዳቸውን አላወጡም ነበር። እንዲሁም የ53 ዓመት ጓደኛቸውም በቅርቡ መንጃ ፈቃድ ሊያወጡ እየተዘጋጀ ነው።

በተለይም ካናዳን ወይም ከተሞቹን ለነዋሪዎች ምርጥ እና ምቹ ያደረጋቸው ከቤት ወጥተው የሚዝናኑባቸው ሰፋፊ ፓርኮችን የከተማዋ ማዕከል ማድረጋቸው ነው።

“ሦስቱም እነዚህ ለኑሮ ምቹ የሆኑ ከተሞች ለተፈጥሮ ቅርብ መሆን ብቻ ሳይሆን በከተሞቹ ዲዛይን ውስጥም እንዲካተቱ ተደርገዋል” ይላሉ ሳማንታ።

“በቶሮንቶ ውስጥ ነዋሪዎች የሚዝናኑባቸው በጫካ የተሞሉ ሸለቆዎች እንዲሁም የባሕር ዳርቻዎች አሉ። በሞንትሪያል በዛፍ የተሸፈኑ ጎዳናዎች እንዲሁም ሞንት ሮያል የተሰኘ ፓርክ አለ። ቫንኮቨር ደግሞ ከዓለም ምርጥ የከተማ የተፈጥሮ ስፍራዎች ውስጥ አንዱ ምሳሌ የሆነው ስታንሊ ፓርክ አላት” ሲሉ ሳማንታ ያስረዳሉ።

ከተሞቹ ተፈጥሮን ማዕከል ባደረገ መልኩ ዲዛይን መደረጋቸውም ለነዋሪዎች የአዕምሮ እፎይታን ይለግሳሉ።

ሦስቱም የካናዳ ከተሞች የየራሳቸው ልዩ የሆነ ነገር ያላቸው ሲሆን፣ አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ለነዋሪዎች ባላቸው ምቹነት ነው። እስቲ ስለ ከተሞቹ ጥቂት እንበላችሁ፡

የቫንኮቨር ከተማ
የምስሉ መግለጫ,የቫንኮቨር ከተማ

ቫንኮቨር

ውብ በሆነው የካናዳ ምዕራባዊ ጠረፍ ላይ የምትገኘው ካንኮቨር በተፈጥሮ ሃብቷ የታደለች ናት።

“ቫንኮቨር ያሏት አስደማሚ ተራሮች እና ውቅያኖሶች” የምድር ላይ ገነት እንደሚያስብላትም ነው ሳማንታ የሚናገሩት።

በቫንኮቨር ከተማ ላለፉት 20 ዓመታት ቢኖሩም አሁንም የከተማዋ መልክዓ ምድር እንደ አዲስ ልባቸውን ይሰርቀዋል።

የቫንኮቨር ውበቷ መልክዓ ምድሯ ነው፣ እናም እየዘነበ ቢሆን “ውጭ ስትወጡ ሌላ ስሜት” ይሰማችኋል ይላሉ ሳማንታ።

በተለይም በሚዘንብበት ወቅት ከተማዋ ልዩ እንደምትሆን ነው ሳማንታ የሚናገሩት። ቫንኮቨር ከመጡ በከተማዋ ማዕከል 405 ሄክታር የሚሸፍነውን እና ዘመናትን በጠገቡ ዛፎች የተሸፈነውን ስታንሊ ፓርክን መጎብኘት ካለባቸው ስፍራዎች አንዱ ነው ትላለች። በተለይም ከ700- 800 ዓመታትን የጠገቡት የቀይ ዝግባ ዛፎች ሌላ መልክ ይሰጡታል።

ተራራ መውጣት ለሚፈልጉ ደግሞ የግሩስን ተራራ ቢወጡ ድንቅ የከተማዋ ውበትን ማየት ይችላሉ። በተራራዋ ጫፍ ላይ ከደረሱም በኋላ ዐይን በሚያስደምመው ዕይታ ታጅበው ወይንዎን መጎንጨት ወይም ቡናዎን መጠጣት ይችላሉ።

የተፈጥሮን መልክዓ ምድር ለመፈተሽ ብዙ ፍላጎት ለሌላቸው ደግሞ የከተማዋ የበርካታ ባህል መገኛነት እና የምግብ ዓይነቱ ዐይን አዋጅ ያሰኛል።

የኢትዮጵያውን እንጀራ በጥብስ ቢፈልጉ ወይም ወይም የቲቤት ሞሞስ የተሰኘውን ጣፋጭ ምግቦች ያገኛሉ። የቫንኮቨር ከተማ በተለይም ዋጋቸው ተመጣጣኝ በሆነው የጃፓን ሱሺ ምግብ ትታወቃለች። ከጃፓን ውጪም በጣፋጭነቱም ሆነ በተመጣጣኝ ዋጋውም ይታወቃል።

 የካልጋሪ ከተማ
የምስሉ መግለጫ,የካልጋሪ ከተማ

ካልጋሪ

በምዕራባዊ አልበርታ ግዛት የምትገኘው ካልጋሪ በታዋቂዎቹ ሮኪ ተራሮች አቅራቢያ ትገኛለች። ነዋሪዎች ካልጋሪን ሲገልጿት ትልቅ ከተማ ብትሆንም እንደ ትንሽ መንደር አቃፊ የሆነች ይሏታል። የኑሮ ውድነቷም ከሌሎች ከተሞች ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው።

“ካልጋሪ በካናዳ ውስጥ ካሉት ትላልቅ ከተሞች አንዷ ብትሆንም ለየት ያለ መለያም አላት። ከተማዋ ማኅበረሰብ ተኮር ናት፣ ነዋሪው ሰው ወዳጅ ነው፣ ሰላምተኛም ነው። ጉርብትናንም ለማጎልበት የተዘረጉም የግብርና ምርቶችንም በሚሸጡባቸው ገበያዎችም ትታወቃለች” ስትል የከተማዋ ነዋሪ እና የጉዞ ጦማሪ የሆነችው ሎራ ፖፕ ታስረዳለች።

በትልቅ ከተማ ውስጥ ሆነው የጉርብትና ስሜት ባለበት መንደር ውስጥ የሚኖሩ ቢመስልዎትም ካልጋሪ ታዋቂ ምግብ ቤቶችን፣ የባህል ፌስቲቫሎች እንዲሁም በደመቁ የምሽት ክበቦችም አይጎድልብዎትም።

ሁሉን እንደየ ሁኔታው ታስተናግዳለች። ከተማዋ የበርካታ የተለያዩ ሕዝቦችም መኖሪያ ናት። ከ240 በላይ ጎሳዎችን በመያዝ እና 165 ቋንቋዎች በመናገርም በካናዳ ውስጥ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ከተማዋ አትራፊ የጋዝ እና የዘይት ኢንዱስትሪዎች መገኛ በመሆኗም ሠራተኞች የሚገኙባት እና ተመጣጣኝ የኑሮን ሁኔታ የያዘች ናት።

ካልጋሪ እንደ ሌሎች የካናዳ ከተሞች በተፈጥሮ መልክዓ ምድሮች የታደለች ናት። ካልጋሪ ከ1 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው እና የሰሜን አሜሪካ መንገዶችን የሚያገናኙ፣ ለእግረኞች እና ለብስክሌት ነጂዎች ሰፊ ጥርጊያ መንገድ እና የብስክሌት መንገድ አዘጋጅታለች።

የቶሮንቶ ከተማ
የምስሉ መግለጫ,የቶሮንቶ ከተማ

ቶሮንቶ

የካናዳዋ መዲና ቶሮንቶ በሕዝብ ብዛቷ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። እንደ ሕዝብ ብዛቷ ከ1500 በላይ ፓርኮችን በመክፈት ነዋሪዎች ከቤታቸው ወጥተው መንፈሳቸውን የሚያድሱበት መንገድንም ቀይሳለች።

በቶሮንቶ ሲፈልጉ በአውቶብስ፣ በብስክሌት፣ በባቡር ወይም በእግር ቢጓዙ ደኅንነትዎ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። በየትኛውም ሰዓት ሰላም የሰፈነባት ናት።

ከተማዋ ስትቀየስ ሕዝብን ያማከለ መሠረተ ልማትን ቅድሚያ በመስጠቷም ከበርካታ ትላልቅ ከተሞች ሕይወት ቀለል ያለ ያደርጋታል – ቶሮንቶን።

በተለይም አጥንት የሚሰብረውን የካናዳውን ክረምት መቋቋም የሚችሉበት ከመሬት በታች ያለ የእግረኛ መንገድ ስለሆነው ‘ፖዝም’ ይናገራሉ።

በቅዝቃዜ ወቅትም ቢሆን “ከቢሮዬ እሰከ አየር ማረፊያው ወይም ባቡር ጣቢያው፣ ሬስቶራንቶች እንዲሁም የሕክምና ማዕከላት ሳይቀር የክረምት ኮት ሳያስፈልገኝ በተመቻቸ ሁኔታ መመላለስ እችላለሁ” ይላል የከተማዋ ነዋሪ እና በትንሽ ገንዘብ በቅንጦት መኖር እንዴት እንደሚችሉ የሚጦምረው ሆንግ አንህ ሌ።

የካናዳ ከተማ የበርካታ የተለያዩ ሕዝቦች ነዋሪ በመሆንም ትታወቃለች። ከቶሮንቶ ነዋሪዎች ውስጥ 51 በመቶዎቹ ከካናዳ ውጪ የተወለዱ ናቸው።

የተለያዩ ባህሎች እንዲሁም ቋንቋዎችን የሚማሩባትም ናት የካናዳዋ ቶሮንቶ። የካናዳዋ መዲና ሌሎች ባህሎች እና ቋንቋዎች መሳ ለመሳ የሚካሄዱባት እና እነዚህም በተለያዩ ፌስቲቫሎች የሚደምቁባት ስፍራ ናት።

ቶሮንቶ የሥራ ፈጠራዎች እንዲሁም የሥራ ፈጣሪዎችም ማዕከል ናት። ከትልልቆቹ ኩባንያዎች ኡበር፣ ጉግል፣ እና ፌስቡክ መቀመጫነት በተጨማሪ አዳዲስ ጀማሪዎችም የሚያብቡባት ናት።

ከኒው ዮርክ ከተማ እና ሲልከን ቫሊ በመቀጠልም በሰሜን አሜሪካ ካሉ ከተሞችም ሦስተኛዋ ትልቋ የቴክኖሎጂ ማዕከል ናት።