
23 ታህሳስ 2023
የሆሊውድ ተዋናይ እና ፕሮዲውሰር ነች- መቀለ ተወልዳ በስድስት አመቷ ወደ አሜሪካ ያቀናችው ፍርቱና ገብረስላሴ።
ፊልም አፍቃሪዎች፤ አይ አም ሂር ቱ ኢንድ ዩ (I am here to End You)፣ ማኒፌስት (Manifest 2018)፣ እና ብሉ ብለድስ (Blue Bloods 2010) ላይ ስትተውን ያውቋታል።
እርሷም፣ ጥበብን የሌሎችን ሕይወት የምትለውጥበት መንገድ፤ ሆሊውድን ደግሞ ትምህርት ቤቴ በማለት ትገልፀዋለች – የሆሊውዷ ተዋናይት ፍርቱና ገብረስላሴ።
ፍርቱና ገብረ ስላሴ ምንም እንኳ በሆሊውድ በትወና መስራት ብትጀምርም ከዚያ በኋላ ግን ፕሮዳክሽን ዲዛይነር፣ ፕሮዳክሽን ማናጀር እንዲሁም ፕሮዲውሰር በመሆን ሰርታለች።
ፍርቱና፤ ወደ ግዙፉ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ሆሊውድ በገባች በአጭር ግዜ ውስጥ ከ10 በላይ ፊልሞች ሠርታለች።
ትወናን የጀመረችው በዘ ዱስ (The Deuce) ሲሆን፣ ማኒፌስት (Manifest) ፣ ብሉ ብለድስ (Blue Bloods) ፣ ሃርለም (Harlem)፣ ሞደርን ላቭ (Modrene love)፣ ስዊት ቢተር (SweetBitter)፣ ሃይ ታውን (High Town)፣ ካቲ ኬን፣ ዘ ራይት ፓዝ (The wright Path) በተሰኙ ፊልሞች ላይ ተሳትፋለች።
እኒህ ፊልሞች ፍርቱና በትወና የደመቀችባቸው በኔትፍሊክስ፣ ሲቢኤስ፣ አማዞን ፕራይም እና ስታር ኔትዎርክ የሚተላለፉ ተከታታይ ፊልሞች እና ቲቪ ሾዎች ናቸው።
ለፍርቱና የሆሊውድ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ፣ የጥበብ ፍላጎቷን ከመወጣት እንዲሁም ገንዘብ ከማግኘቱ ባሻገር ሐሳቧን ወደ ተግባር የምትቀይርበት መንገድ ነው።
“ጥበብ ሌሎችን ለማነቃቃት፣ ተስፋ ለመስጠት ወይም የሥራ እድል ከሆነ፣ እንዴት ነው ይህንን ተጠቅሜ ሌሎችን መርዳት የምችለው ብዬ አስባለሁ። በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ደግሞ ብዙ እድሎች አሉ። ስለዚህ ጥበብ ለኔ የራሴን እና የሌሎችን ሕይወት የምቀይርበት ትልቅ እድል ወይ መንገድ ነው።”
አክላም “. . . ጎበዞች እና ምርጥ ዳይሬክተሮች፣ ተዋንያን፣ ፀሃፍት እና ድምፃውያን ሁሉም በሆሊውድ አሉ። እኔ ደግሞ ችሎታዬን ማሳደግ ስለምፈልግ ሆሊውድ ለኔ ሃብት እና ትምህርት ቤት ነው” ትላለች።
- ምሥሎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዴት ይሠራሉ? ከእውነተኞቹስ እንዴት መለየት ይቻላል?19 ታህሳስ 2023
- ጦርነት እንዲቆም በሚጠይቅ አጭር ፊልም ታዋቂ ሽልማትን ያገኘው ወጣት ኢትዮጵያዊ17 ታህሳስ 2023
- ‘የጠፉ መጽሐፍት አዳኙ’ ኤልያስ ሜክሲኮን እስከ ወዲያኛው ይሰናበታት ይሆን?10 ታህሳስ 2023
ከትግራይ መቀለ ወደ ሆሊውድ …..

ተዋናይት፣ ደራሲ፣ ድምፃዊት፣ ፕሮዲውሰር እና ዳይሬክተር በመሆን በሆሊውድ ኢንዱስትሪ የምትሰራው ፍርቱና የተወለደችው በትግራይ ዋና ከተማ መቀለ ነው።
የስድስት ዓመቷ ህፃን ፍርቱና ከቤተሰቦቿ ጋር በመሆን ከመቀለ ወደ ሲያትል አሜሪካ የሄዱት የዲቪ ሎተሪ ዕድለኛ በመሆናቸው ነበር።
አባቷ ግን ቀድሞውንም በአሜሪካ ለትምህርት ሄደው እዚያው መኖር ጀምረው እንደነበር ፍርቱና ትናገራለች።
“አባቴ የትምህርት እድል አግኝቶ ወደ አሜሪካ ሄዶ ስለነበር እዚያ ይኖር ነበር። እናቴ፣ እኔ እና ታላቅ እህቴ ደግሞ በዲቪ ሎተሪ ነው ወደ አሜሪካ የመጣነው።”
ከመዋዕለ ህፃናት እስከ መሰናዶ ትምህርቷን ዋሺንግተን ግዛት በሚገኘው ሲያትል የተማረችው ፍርቱና፣ ገና በልጅነቷ በውስጧ ያደረውን የጥበብ ፍቅር እውን ለማድረግ ወደ ኒውዮርክ ወደ NYU Tisch School of the Arts አምርታለች።
“ከዋሽንግተን ሲያትል ወደ ኒውዮርክ በመሄድ ትወና አጠናሁኝ። ከዚያ ማናጀር [ኤጀንት] በመያዝ ስራ ጀመርኩኝ” ትላለች ወደ ሆሊውድ ኢንዱስትሪ የገባችበትን አጋጣሚ ስትገልፅ።
ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ትወና በማጥናትም ከኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪዋን አገኘች።
ለሦስት ዓመታት ካጠናችው ትወና በተጨማሪ ፍርቱና፤ ደራሲ፣ ዳይሬክተር፣ ፕሮዲዩሰር፣ ድምፃዊት እና ዳንሰኛ ናት።
እነዚህ ተጨማሪ ሙያዎች በዩኒቨርሲቲ በመደበኛ ፕሮግራም ከምትማረው ውጪ፣ በግሏ በምታደርገው ጥረት ያዳበረቻቸው ናቸው።
ባሌት ደግሞ በጣም ከምትወዳቸው የዳንስ ዓይነቶች መካከል አንዱ ነው።
“ይህ ኢንዱስትሪ በጣም ከባድ ስለሆነ በአንድ ሙያ ብቻ መስራት በቂ አይደለም። ተወዳዳሪ ለመሆን ሁሉንም ዘርፍ ማወቅ አለብሽ። በመለማመጥ የሚሆን አይደለም። ራስሽ እድሉን መክፈት አለብሽ። ይህንን ከግምት በማስገባት ነው ዘርፈ ብዙ ባለ ሙያ መሆን የቻልኩት” ትላለች።
የብዙ ሙያ ባለቤት መሆኗ ደግሞ መሰናክል በሚያጋጥምበት ግዜ መውጫ እንዲኖራት እና በሁሉም አይነት መስክ ውስጥ ገብታ እንድትሰራ እንዳስቻላት ትገልፃለች።
ፍርቱና የሆሊውድ ሕይወቷ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት ባገኘው እና በሲቢኤስ ወደ ተመልካቾች እየቀረበ ባለው ‘ዘ ዱስ’ (The Deuce) በመተወን ነው አሃዱ ብላ የጀመረችው።
“መጀመርያ ‘ዘ ዱስ’ ላይ ስገባ ለአንድ ክፍል ነበር። በአንድ ክፍል ላይ ባሳየሁት ብቃት ስለ ወደዱኝ ቀጣይ ክፍል ላይ ትገቢያለሽ አሉኝ። በአንድ ክፍል የጀመርኩት አሁን ምዕራፍ አምስት ደርሻለሁ” ትላለች የመጀመርያ ስራዋን ስትገልፅ።
ከ2010 ጀምሮ ለ 13 ተከታታይ ምዕራፍ (ሲዝን) በሲቢኤስ ወደ ተመልካቾች እየቀረበ ያለው ‘ብሉ ብለድስ’ (Blue Bloods) ፍርቱና በከባድ ፉክክር አልፋ ለመተወን የበቃችበት ተከታታይ ድራማ ነው።
አንድ ተዋናይ በዓመት በርካታ ‘ኦዲሽን’ (ችሎታቸውን አሳይተው የሚቀጠሩበት ሁኔታ)እንዳለው የምትናገረው ፍርቱና፣ እሷ በሁለት ዓመት ብቻ በ10 ፊልሞች መተወን መቻሏ ከጠበቀችው በላይ መሆኑ ትገልፃለች።
“አንድ ተዋናይ በዓመት ከ 500 ኦዲሽን አንድ ወይም ሁለት ቢያገኝ ነው፤ ብዙ ኦዲሽን ሰርተውም ምንም የማያገኙ አሉ። እኔ በሁለት ዓመታት ውስጥ ነው 10 ፊልሞችን የሰራሁት። ይህ ለራሴም አስደንግጦኛል። በጣም ብዙ ብጥርም የእግዚአብሄር ፈቃድ ስለሆነ ነው በአጭር ግዜ ይህንን ሁሉ መስራት የቻልኩት” ትላለች።
በአጭር ግዜ በብዙ ፊልሞች እና ተከታታይ ድራማዎች ላይ መተወን የቻለችው ፍርቱና፣ በትወና ብቻ ተወስና መስራት አልፈለገችም።
በሆሊውድ ባገኘችው ልምድ ኒውዮርክ ውስጥ የራሷ የፊልም ፕሮዳክሽን ተቋማት ከፍታለች።
“በሆሊውድ ልምድ ከያዝኩኝ በኋላ የራሴ ፕሮዳክሽን ኩባንያ ከፈትኩኝ። ኤልፒኤ ፊልምስ እና ስላሴ ሃውስ ፕሮዳክሽን የሚባሉ ሁለት ኩባንያዎች አሉኝ። የሞያ አጋሬ ደግሞ ሎሬንዞ አዳምስ ይባላል። “ስትል ታስረዳለች
አሁን ከሎሬንዞ ‘ዋይሞናሬ’ የሚባል ወጥ ፊልም እና ሌሎች አጫጭር ፊልሞች አሉን። ሲሞን (Simone)፣ ኬረን ቢንክል፣ ዘይ ሉክ ላይክ አስ፣ ዘ ቦይ ኢን ዘ ክሎዜት፣ ሃሎዊን 63 የሚባሉ ፊልሞች በመስራት ላይ እንገኛለን። ሲሞን ፊልም ወደ ‘ፌስቲቫል 400’ ለውድድር ገብታለች።”
ፍርቱና በልጅነቷ ድምፃዊት መሆን ትፈልግ ስለነበር ይህንን የልጅነት ህልሟን መተው አልፈለገችም።
ከራፐር Q.RAP ጋር በመሆን ‘በጃኺ’፣ ‘አደዳይ’ እና ‘ እንተዝኽእል ነይረ’ የሚሉ ስራዎችን ወደ አድናቂዎቿ አድርሳለች፤ የራሷ ሙዚቃዎችንም በመስራት ትገኛለች።

“በልጦ መገኘት ብቸኛው አማራጭ ነው….”
በሆሊውድ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ አንድ ተዋናይ የመተወን እድል ለማግኘት በከባድ ፉክክር እንደሚያልፍ የምትናገረው ፍርቱና፣ በዚህ ብርቱ ፉክክር ያለበት ኢንዱስትሪ ለማሸነፍ ትጉህ መሆን እና በልጦ መገኘት ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ ትገልፃለች።
“እውነት ለመናገር ልምምድ ያስፈልጋል። እኔ ሁሌም ትምህርት ላይ ነኝ። በተውኔት፣ ድርሰት፣ የሙዚቃ ፕሮዳክሽን ሁሌም እማራለሁ፤ ልምምድም አደርጋለሁ። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በልጠሽ መገኘት አለብሽ” ትላለች።
ወደ ሆሊውድ ኢንዱስትሪ ከገባችበት አሁን እስከ ምትገኝበት ደረጃ በእያንዳንዱ አጋጣሚ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባት ተምራለች።
“ስትጀምር በጣም ፈታኝ ነው። ኮ ስታር፣ ሪከሪንግ ኮ ስታር፣ ሲዝን ሬጉለር፣ ሰፖርቲንግ ሊድ እያልሽ በደረጃ ነው የምታድጊው። ለምሳሌ፣ መጀመርያ ላይ ረዳት ተዋናይ (ኮ ስታር) ነበርኩኝ፤ በ ብሉ ብለድስ ግን ሪከሪንግ ኮስታር ነኝ ያለሁት [ከአንድ ኢፕሶድ በላይ በተከታታይ ክፍል የሚተውን]”
ከልምዷ በመነሳትም ሴቶች፣ በአጠቃላይም ወጣቶች በሚገኙበት ዘርፍ ስኬታማ እንዲሆኑ በሚፈልጉት ዘርፍ ላይ እውቀት እና ልምድ ማዳበር አለባቸው ትላለች።
“አንደኛ ወደ ትምህርት ቤት በመሄድ ወይም በኦንላይን የሚፈልጉትን ሙያ መማር ያስፈልጋል። በሚሄዱበት አገር ሌሎች ብዙ ተወዳዳሪዎች ስላሉ ክህሎትህን በደምብ ማወቅ ያስፈልጋል።
ሁለተኛ ዓላማ ሊኖር ይገባል። ለምንድን ነው ይህን እያደረግኩት ያለሁት? ራዕይዬ ምንድን ነው? ለምሳሌ፣ አንዳንድ ሰዎች ፊልም ስላዩ ብቻ ወደ ዘርፉ መግባት የሚፈልጉ አሉ። ወደ ስራው ከገቡ በኋላ ግን ስራው ከባድ ስለሚሆን ፍላጎት ያጣሉ። ምክንያቱ ዓላማቸው ጠንካራ ስላይደለ ትንሽ ችግር ሲያጋጥማቸው ይህማ ለኔ አይሆንም’ ብለው ይተዉታል።
ስለዚህ ለምን እንደሚያደርጉት ዓላማ፣ ራዕይ እና ምክንያት ሊኖራቸው ይገባል። ይህን ሲኖር ተፈትነው ያልፋሉ እንጂ ተስፋ ቆርጠው፣ ወድቀው አይቀሩም” በማለት ምክሯን ታካፍላለች።
- የጦርነት ዳፋ የመጨረሻው ውጤት የሚታየው ጦር ሜዳ ላይ ሳይሆን ቤተሰብ ውስጥ ነው – ይፍቱሥራ ምትኩ12 ህዳር 2023
- “የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቼ የፈውሴ ምንጭ ናቸው” ትዕግሥት ሳሙኤል22 ጥቅምት 2023

“ተጋሩ ለኔ ኢንስፓይሬሽን እና ተስፋ ናቸው”
ለሁለት ዓመታት በትግራይ የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በፕሪቶርያ ስምምነት ከተገታ በኋላ የሆሊውድ ተዋናይቷ ፍርቱና ወደ ትውልድ ስፍራዋ ትግራይ ሄዳ ነበር።
“በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ብዙ ችግር ተፈጥሯል። በትግራይ ሕይወት በጣም ተቀይሯል። በጣም አዝኛለሁ። ይህ ሕዝብ ይህን ሁሉ ነገር ተፈፅሞበት እንዴት ቻለው? ሊገባኝ አይችልም። ከዚህ ሕዝብ ብዙ ነገር ተምርያለሁ። ተጋሩ ለኔ ‘ኢንስፓይሬሽን’ እና ተስፋ ናቸው” ትላለች።
ፍርቱና የተጋሩ ታሪክ እና ባህል በዓለም እንዲታወቅ ገና ብዙ ሥራ እንደሚጠብቅ ትገልፃለች።
“ባህላችን በጣም ያማረ ነው፤ ሰዉም እንደዛ። ከመቀለ ትግራይ የወጣሁኝ መሆኔ በጣም እደሰታለሁ። የኛ ባህል፣ ታሪክ፣ ፍቅር እና ደስታ እንዴት ወደ ዓለም ማድረስ እችላለሁ ብዬ ነው የማስበው እና የምሰራው።
“የትግራይ ታሪክ፣ በትግራይ የተፈፀመው ሁሉ ሊነገር እና ሊታወቅ ይገባል። አሁን እዚሁ አሜሪካ የተለያዩ ጸሐፍት አሉኝ። በትግራይ ታሪክ እና ባህል፣ በትግራይ ስለ ተፈፀመው ‘ጄኖሳይድ’ (የዘር ማጥፋት) ተባብረን እየሰራን እንገኛለን። አሁን ዋነኛው ትኩረቴ እዚህ ላይ ነው” በማለት ለመጪው የምታልመውን እና አሁን በዋናነት እየሰራችበት ያለችውን ለቢቢሲ ገልፃለች።