December 23, 2023 – Getachew Shiferaw

መሬት ላይ ያለውን ንቅናቄ በሚዲያ አትውጉት!

መሬት ላይ ያለው የአማራ ንቅናቄ በልኩ የፖለቲካና የሚዲያ አጋዥ አላገኘም። በርካታ በጎ ነገር በአሉታዊ መንገድ ይዘገባል። ለረዥሙ የአማራ ትግል ከሚጠቅመው ይልቅ የዕለቱን እይታ የሚያስገኘው ገፅ ይጎላል። ለምሳሌ ሰሞኑን ከሽማግሌዎቹ አንፃር በርካታ ተቆርቋሪ ነን ያሉ ሚዲያዎች የሰሩት መሬት ላይ ከተደረገው የተለየ፣ ለቀጣይ የአማራ ፖለቲካ የማይጠቅም፣ የአማራን ንቅናቄ ያለ አግባብ ስም የሚያሰጥና ከጀርባ የሚወጋ ነው። የፋኖ መሪዎች የሽምግልና አካሄድ ብልሹነቱን፣ የአገዛዙን ንቀት ወዘተ አውግዘው፣ ሽማግሌዎቹን ግን በሚታየው መልኩ አክብረው፣ ጦርነቱ በዚህ የአካባቢ ሽምግልና እንደማይፈታ አስተምረው መልሰዋል። ለፍትሕ ከተነሳው የአማራ ንቅናቄ የሚጠበቀውን ክብር አድርገዋል።

ሚዲያውን ሁሉም በቆረጣ ገብቶበት ሲያበላሽ እንደታየው አይደለም። አብዛኛው ለአማራ ፖለቲካ በጣም አሉታዊ ነው!

1)የፋኖ አመራሮች ያላደረጉት በጣም በአሉታዊ መልኩ አገዛዙ የአማራውን ትግል በሚያጥላላበት ሁኔታ በሚዲያ ተሰርቷል። ይህ መሬት ላይ ያለውን የማይገልፅ፣ አገዛዙ ንቅናቄውን በሀሰት ጭቃ የሚቀባው ላይ የተጨመረ አሉታዊ የሚዲያ አሰራር ነው። ከግንዛቤ እጥረትም፣ ከስሜታዊነትም ወዘተ የመጣ የሚዲያ አሰራር ነው።

2) ለቀጣይ አማራ ፖለቲካም ይህ አይነት የሚዲያ አካሄድ አይጠቅምም። ከጦርነቱ በኋላም ፖለቲካ አለ። ትህነግ እሴቱን በሙሉ ንዶ አሁን ትግራይ ውስጥ የሀይማኖት አባት ቢል፣ ሽማግሌ የሚሰማ ጠፍቶ ሰው እየፋጀ ነው። ኦሮሚያ እሴቱን አጥፍተው አህያ እየበሉ፣ ሰው እየጨፈጨፉ ነው። አረመኔነቱ ማንንም አልምር ብሏል። አማራው አቅም የሆነው ግዙፍ ስነልቦናው፣ እምነቱ ነው። ይህ መሬት ላይ እያለ ሚዲያ ላይ እያንሻፈፉ መዘገብ በቀጣይ ትውልድ ላይ ጭምር የተቃጣ ጥቃት ነው። አሁን የምንሰራው ለጦርነቱ ብቻ ሳይሆን ከጦርነት በኋላ ለምንጠብቀው ማህበሰብም በጎ መሆን አለበት!

3) ከመርህ አንፃርም አይሄድም። አገዛዙ ለኃይማኖት፣ ለእሴት ያለውን ነውር እየተቸን፣ ያልተፈጠረን ነገር እንደተፈጠረ አድርገን መዘገብ፣ ማጋነን፣ ያልተፈጠረ አሉታዊ ጎኑን አጉልቶ ማቅረብ ለፍትሕ የሚታገለው አማራው የገዥዎቹን አሉታዊ መልክ እንዲይዝ ጫና ማድረግ ነው።

4) በውጭ አገር ሆኖ ዲፕሎማሲ መስራት ያልቻለ፣ መጉላት ያለበትን ማጉላት ያልቻለ፣ የፋኖ አመራሮች በዲፕሎማሲ ያሸነፉትን መንገድም እያበላሸ እየሰራ ዝም መባል የለበትም። የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲም ድህነት ነው!

5) መሬት ላይ ያለው ንቅናቄ አይደለም የሚያውቃቸውን ሽማግሌዎች በሀሰት የከሰሱትን የውጭ ኃይሎች ጭምር አሳምኗል። አሜሪካን አሳምኗል፣ አውሮፓ ህብረትን አሳምኗል። ሚዲያ ላይ ሆነህ የተውካቸውን ትህነግ/ህወሓትና ኦነግን ቃር ቃር እያላቸው እንዲያምኑ ያደረገ፣ ያስገደዳቸው ነው። ሽማግሌዎቹ የመረጡት አካሄድ ትክክል ባይሆንም አስረድቶ መልሷል። እውነት አለው። እውነቱም ማስረዳትም ችሏል። መሬት ላይ ያለውን ከተማ ያዘ፣ ለቀቀ ብቻ በሚል የሚደገፍ የሚመስለው በርካታ ሚዲያ ግን ከሽማግሌዎቹ አንፃር የተሰራውንም አወላግዶ፣ በተለምዶ ደካማነቱ ሰርቶታል።

6) ፀረ አማራ የሆኑትን የትህነግና ኦነግ እንዲሁም ብልፅግና አካሄድ አማራው ሊሰራበት አይችልም። ሁሉም ወድቀውበታል። አማራው ያልወደቀው ትግሉን በእሴቱ ጭምር ስለሚያስኬድ ነው። አይደለም ሽማግሌ በ7ኛ ዙር የዘመተበትን ጦር በሚገባ መልሶ፣ አማራው አንገቱን እንደማይደፋ አሳይቷል። ይህ በሆነበት በተለየ መንገድ ሊቀርብ የሚችለውን ለጠላት በሚጠቅም፣ ጠላት መንገድ ማቅረብ ትግሉን መውጋት ነው።

7) ተሳሳቱም አልተሳሳቱም፣ የሚያውቃቸውን የአካባቢውን ሰዎች ቀርቶ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን እያሳመነ ያለ ንቅናቄ ነው። ብልፅግና ስለላካሸው ብቻ ሽማግሌዎች የአማራውን አላማ አስረስተው ያስገብሩታል ብሎ ማሰብ በራሱ መሬት ላይ ያለው ኃይልም አላማውንም ማቃለል ነው። ከዚህ ይልቅ መሬት ላይ በመሆነው መንገድ የአማራው ጉዳይ በሰፈር ሽምግልና እንደማይፈታ፣ ይህ ንቀት ለምን መቆም እንዳለበት ሙያን፣ አጋጣሚን ተጠቅሞ በሚገባ ማስረዳትና መሬት ላይ ያለውን ማገዝ የተሻለ ነው።

የአማራ ትግል በዚህ ጦርነት አያበቃም። ከዚህ ጦርነት በኋላም ረዥም ትግል አለ። የአጭር ጊዜው፣ ፀረ አማራዎቹ የሄዱበት ስልት እያነሱ መጠቀም መመለሽያ ያሳጣል። ብሔርተኝነቱ ከእሴት ውጭ ባዶ ነው። የሽምግልና ስርዓቱ ቢበላሽም በስርዓት ተገቢ መልስ ተሰጥቶበታል። በየቀኑ የሚሰሙትን ድንቅ ስራዎች በየግል ማጨማለቁ ለዩቱዩብ እንጅ ለትግሉ አይበጅም።

እያንዳንዱ ክስተት አማራው እንደታቀደለት መከራ፣ እየከፈለ እንዳለው ዋጋ በጥንቃቄ፣ በክብር፣ ምን ያመጣል ተብሎ ውይይት ተደርጎበት በእውቀት መሰራት አለበት። እጅግ ውድ ዋጋ እየተከፈለበት ነው! ጥንቃቄ ይጠይቃል! የቲክቶክ፣ የፌስቡክ፣ የዩቱዩብ አካውንት ስላለ ብቻ ሁሉም አይለጠፍም። ጦርነት ነው!