ዜና የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የግል ተቋማትን አስተዳደራዊ በደሎችንና ቅሬታዎችን መቀበል ጀመረ

ሔለን ተስፋዬ

ቀን: December 24, 2023

ከግል ተቋማት የሚደርሱትን የአስተዳደራዊ በደሎችና ቅሬታዎችን መቀበል መጀመሩን፣ የኢትዮጵያ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡

የተቋሙ ዋና ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ተቋሙ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ ከግል ተቋማት የሚደርሱትን የአስተዳደራዊ በደል አቤቱታዎችን መቀበል ጀምሯል፡፡

ከግል እርሻዎች፣ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮችና ከሌሎች ድርጅቶች ቅሬታዎችና አቤቱታዎችን መቀበል ሥራው መሆኑን ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ ተደንግጓል ብለዋል፡፡ አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ከታተመ በኋላ በሚቀርቡ ቅሬታዎች መሠረት ወደ ምርመራ እንደሚገቡም ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ ሁሉንም የግል ተቋማት ተደራሽ ማድረግ እንደማይችል የገለጹት እንዳለ (ዶ/ር)፣ አብዛኛውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚዘውረው የግሉ ዘርፍ ስለሆነ ሰፊ ምኅዳር እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በተለይም ከግል ተቋማት እያቀረቡ ካሉ አስተዳደራዊ በደሎች መካከል፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከሥራ ማሰናበት፣ ሥራ ላይ ሆነው የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው በቂ ሕክምናና ካሳ አለመክፈልና ሌሎችም ቅሬታዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ተሻሽሎ የወጣው አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ሲወጣ የማስተዋወቅና የማስተማር ሥራዎችን ለማከናወን የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዝግጀት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሚቀርቡ አስተዳደራዊ በደሎችን መሠረት አድርጎ ምርመራ ለመጀመርና ቅሬታ ለቀረበባቸው ተቋማት ደብዳቤ ለመጻፍ፣ ተሻሽሎ የወጣው አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ መውጣት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አዋጁ መውጣቱ በመንግሥት ድርጅቶች ላይ ተወስኖ የነበረ ሥራውን እንዲሰፋ ማድረጉን ገልጸው፣ ከዚህ በተጨማሪ የተቋሙ ሠራተኞች ያለ መከሰስ መብት ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ሠራተኞች በሥራ ሥምሪት ላይ እያሉ ከዚህ ቀደም በወረዳ ፖሊስና በአስፈጻሚ አካላት ይታሰሩ እንደነበረ አስታውሰው፣ በአዋጁ የተሰጣቸውን ያለ መከሰስ መብት ያለ ዕንግልትና ያለ ፍርኃት ለመሥራት ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ያለ መከሰስ መብት በራሱ ዋስትና እንደማይሆን የገለጹት እንዳለ (ዶ/ር)፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ የሚታሰሩ መኖራቸውን አክለዋል፡፡

ይህም ያለ መከሰስ መብት በራሱ ዋስትና እንደማይሆን እንደሚያሳይ፣  ነገር ግን ተቋሙ ዓለም አቀፍ ደረጃ መመዘኛን ለማሟላት ይረዳዋል ብለዋል፡፡