
December 24, 2023

የሎጂስቲክስ ዘርፉን ለአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ዝግጁ ማድረግ ላይ በመከረው መድረክ ላይ
- የነፃ ንግድ ቀጣና የሙከራ ትግበራ በቅርቡ እንደሚከናወን ተጠቁሟል
ኢትዮጵያ በቅርቡ ተግባራዊ በምታደርገው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ሙከራ ላይ፣ የሎጂስቲክስ ዘርፉን በሚገባ ለማሳተፍ ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባ በሎጂስቲክስ ዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባለድርሻዎች ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ ዘርፉ ማኅበር አስተባባሪነት በተዘጋጀውና የሎጂስቲክስ ዘርፉን ለአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ዝግጁ ማድረግ ላይ በመከረው መድረክ ላይ ተገኝተው የነበሩ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት፣ በሕግ ማዕቀፉና በመሠረተ ልማትን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ዝግጁ መሆን እንደሚገባ ተናገሩ፡፡
ባለፈው ዓርብ ታኅሳስ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢንተርሌግዥሪ ሆቴል በተካሄደው የውይይት መድረክ ለይ የሎጂስቲክስ ማኅበሩ አመራሮች፣ የንግድ ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የግል ሎጂስቲክስ ድርጅት አመራሮችና የሎጂስቲክስ ባለሙያዎች ተገኝተው ነበር፡፡
በመድረኩ የመዝጊያ ንግግር አድርገው የነበሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሎጂስቲክስና አቅርቦት ሰንሰለት ማኔጅመንት ተግባር ፕሮፌሰር፣ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ማቲዎስ ኢንሰርሙ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የሎጂስቲክስ ዘርፉ ከሌላው በተሻለ ስለ ነፃ ንግድ ቀጣናው ጥሩ ግንዛቤ ሊኖረው እንደሚችል ነው፡፡
ሆኖም እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ከሕግ ማዕቀፉና ከመሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ የዝግጅት ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል ነው፡፡ እንደ መንገድና ድልድይ የመሰሉ የመሠረተ ልማቶች፣ እንዲሁም በድንበር ላይ የአሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች መቀያየር (በአገሮች መካከል ያለው የግራና ቀኝ ማሽከርከር ሕጎች) በተመለከተ እንቅፋቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ነው፡፡
ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተወክለው የመጡት አቶ ሳሙኤል ግዛው የተባሉ ባለሙያ እንደገለጹት፣ በአተገባበር ወቅት በትራንስፖርት ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ የተወሰኑ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ነው፡፡ ይህም የትራንስፖርት ሥራን ለመሥራት አገሮች በሚሰጡት ፈቃድ ላይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በምትሰጣቸው የትራንስፖርት ኦፕሬተር ፈቃዶች በኬንያ መሥራት የሚቻልበት ሁኔታ፣ እንዲሁም በሌሎች የጎረቤት አገሮች በሚሰጡ ፈቃዶች በኢትዮጵያ መሥራት የሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንቅፋቶች ሊሆኑ እንደሚትሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹በአንድ ነጠላ ሰነድ ኦፕሬተሮች ከአገር አገር እየዘዋወሩ መሥራት መቻል አለባቸው፤›› ብለዋል አቶ ሳሙኤል፡፡
የሎጂስቲክስ ማኅበሩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ኤልሳቤት ጌታሁን ለተሳታፊዎች እንደገለጹት፣ የነፃ ንግድ ቀጣናውን ዕድል ለመጠቀም ‹‹ምን ያህል ተዘጋጅተናል?›› የሚለውን መጠየቅ እንደሚገባና በዘርፉ በስፋት የሚጠቀሙበት ለማድረግ ቀጣናዊ የሎጂስቲክስ ትስስሩን በግርድፉ መፈተሽ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዋና የንግድ ተደራዳሪና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር የሆኑት አቶ ገብረስቀል ጫላ በዚህ ሳምንት መጀመርያ ለአንድ የአገር ውስጥ ሚዲያ እንዳሳወቁት፣ ኢትዮጵያ በኅዳር ወር ያስገባችውን የታሪፍ መጽሐፍ (Tariff Book) ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
ኢትዮጵያ በጥቂት ወራት ጊዜያትም የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣናን የሙከራ ትግበራ በተመረጡ ሸቀጦችና አገሮች ጋር ልታደርግ እንደምትችል አቶ ገብረመስቀል ፍንጭ ሰጥተው ነበር፡፡