
ከ 9 ሰአት በፊት
የገና በዓልን በማስመልከት በተዘጋጀ የእራት መርሃ ግብር ላይ የታደሙ ከ700 በላይ የኤየርባስ አትላንቲክ ሠራተኞች መታመማቸው ተገለጸ።
የፈረንሳይ ጤና ኃላፊዎች አውሮፕላን አምራች ኩባንያው ያዘጋጀውን እራት የታደሙ ሰዎች ተቅማጥ እና ማስመለስ አጋጥሟቸዋል ብለዋል።
ለገና በዓል ተብሎ የተዘጋጀው እና በርካቶችን ለሕመም ያደረገው ምግብ ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
የፈረንሳይ ጤና ባለስልጣናት እራቱን ከታደሙት መካከል የታመሙት ሰዎች ቁጥር 700 ነው ይበሉ እንጂ ኤየርባስ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ታመው ሆስፒታል የተወሰዱት ወደ 100 የሚጠጉ ሰዎች ብቻ ናው ብሏል።
ግዙፉ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ በርካቶችን ለሕመም የዳረገው ምን እንደሆነ ለማወቅ እና ይህ ዳግም እንዳይከሰት ከጤና ባለስልጣናት ጋር በቅርበት እየሰራሁ ነው ብሏል።
- አሜሪካ በሕንድ ውቅያኖስ አንድ ዕቃ ጫኝ መርከብ ከኢራን በተነሳ ድሮን መመታቱን አስታወቀች24 ታህሳስ 2023
- በእርግዝና ወቅት ነፍሰጡሮችን ለሚያሰቃየው ህመም ፈውስ የሚሆን ፍንጭ ተገኘ24 ታህሳስ 2023
የፈረንሳይ ጤና ጥበቃ ኃላፊዎች የምግብ መመረዝ ምንጩን ለማወቅ ምርመራ መጀመሩን ለአገሪቱ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
ኤየርባስ አትላንቲክ የግዙፉ የዓለማችን አውሮፕላን አምራች ኩባንያ፤ ኤየርባስ አካል ሲሆን በአምስት አገራት ከ15ሺህ በላይ ሰዎችን ቀጥሮ ያሰራል።
ከአውሮፕላን እና ሄሊኮፕተር በተጨማሪ የወታደራዊ፣ የደኅንነት እና የሕዋ ምርቶች አምራች የሆነው ኤየርባስ ግሩፕ ደግሞ በአጠቃላይ 134 ሺህ ሠራተኞች አሉት።
በፈረንሳይ በቅርቡ በምግብ መመረዝ ምክንያት በርካቶች ሕመም ሲገጥማቸው ይህ ለመጀመሪያ ግዜ አይደለም።
ከወራት በፊት ቦርዶ በተባለች ከተማ ባለ አንድ ምግብ ቤት የተመገቡ በርካታ ሰዎች ሕመም ገጥሟቸው አንድ የግሪክ ዜጋ ሕይወቱ አልፎ ነበር።