በግላቸው የሚወዳደሩት ፖለቲከኛዋ ያካቴሪና ዱንትሶቫ

ከ 8 ሰአት በፊት

የቀድሞ የቴሌቪዠን ጋዜጠኛ የነበሩት እና በሚቀጥለው የሩሲያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ፑቲንን ለመገዳደር የተነሱት ዕጩ ከምርጫው መታገዳቸው ተሰምቷል።

በግላቸው የሚወዳደሩት ፖለቲከኛዋ ያካቴሪና ዱንትሶቫ ከዩክሬን ጋር ያለው ጦርነት እንዲቋጭ የሚቀሰቅሱ ናቸው።

ነገር ግን የምርጫ ኮሚሽኑ በሙሉ ድምፅ በሰጠው ወሳኔ ዕጩዋ የሞሉት ፎርም ላይ “100 ስህተቶች” ተመልክቻለሁ ብሎ አግዷቸዋል።

ያካቴሪና ግን ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመሄድ ውሳኔው በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።

የሩሲያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2024 የሚካሄድ ሲሆን የሩሲያው መሪ ፑቲን ከሁለት ዓመት በፊት ዩክሬን ላይ ጦርነት ካወጁ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ ነው።

የፑቲን ነቃፊ የሆኑት ዕጩ ገና ከመጀመሪያው ከምርጫ መታገዳቸው በቅስቀሳው ምንም ዓይነት የተቃውሞ ድምፅ እንዲሰማ እንደማይፈለግ ማሳያ ነው ይላሉ ተንታኞች።

የሩሲያ ምርጫ ቦርድ ኃላፊ ኤላ ፓምፊሎቫ እንደገለጡት ያካቴሪና ወደ ቀጣዩ ሂደት ማለፍ አይችሉም።

በሩሲያ ምርጫ ሕግ መሠረት አንድ ዕጩ ከኮሚሽኑ ይሁንታ ካገኘ በኋላ ቀጣዩ ሂደት በሺዎች ከሚቆጠሩ ደጋፊዎች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ነው።

“አንቺ ወጣት ሴት ነሽ። ገና ብዙ ነገር ይጠብቅሻል። አሁን የሚሰጥሽ ነቀፌታን ለአዎንታዊ ተፅዕኖ መጠቀም ትችያለሽ። የምታካብቺው ልምድ ሁሉ ጠቃሚ ነው” ሲሉ ከውሳኔው በኋላ ለ40 ዓመቷ ያካቴሪና ነግረዋታል።

የቀድሞዋ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ በሩሲያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለመሳተፍ መወሰናቸው የገለጡት ባለፈው ኅዳር ነው።

በወቅቱ ለሮይተርስ ዜና ወኪል በሰጡት ቃል “ማንኛውም ጤናማ ሰው ይህ ሲያደርግ ፍርሀት ይውጠዋል። ነገር ግን ፍርሀት ማሸነፍ የለበትም” ብለው ነበር።

የሩሲያ ሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ተደርጎለት የአንድ ፕሬዝደንት የሥልጣን ዘመን ከአራት ወደ ስድስት ዓመት ከፍ ብሏል።

በዚህ መሠረት የፑቲን የሥልጣን ዕድሜ በሁለት ዓመት የተራዘመ ሲሆን ያለፈው የሥልጣን ዘመናቸው ተሽሮ በሚቀጥለው ምርጫም እንዲሳተፉ በር ከፍቶላቸዋል።

የተቃውሞ ድምፆች በሞስኮው ከተሰሙ ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን በሚቀጥለውም ምርጫ ፑቲን እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል።

ክሬምሊን ግን ፕሬዝደንቱ ከሩሲያዊያን የሚሰጣቸው ድጋፍ ከልብ የመነጨ ነው ይላል።

ያካቴሪና ከዩክሬን ጋር ያለውን ጦርነት ማስቆም እና የፖለቲካ እስረኞችን ማስፈታት የሚለውን ሐሳብ በሰፊው በማቀንቀን ይታወቃሉ።

“ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ እናቀርባለን። ምክንያቱም ይህ ውሳኔ ሕጉን የተከተለ አይደለም” ሲሉ ዕጩዋ በቴሌግራም ገፃቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የምርጫ ኮሚሽኑ እስካሁን 29 ሰዎች በምርጫው ለመሳተፍ ማመልከቻ ማስገባቱን ቢገልጥም ከዛሬው ውሳኔ በኋላ ግን ፑቲን ብቻ ናቸው ሕጋዊ ዕጩ ሆነው መመዝገብ የሚችሉት።

ባለፈው ኅዳር አንድ የጦርነቱ ደጋፊ የሆነ ነገር ግን የፑቲን ስትራቴጂ በመንቀፍ የሚታወቅ ጦማሪ ፕሬዘደንቱን በመገዳደር “ፍትሐዊ ባልሆነው” ምርጫ እንደሚሳተፍ አሳውቆ ነበር።

የ52 ዓመቱ ኢጎር ጊርኪን በርካታ መልዕክቶን ማሕበራዊ ሚድያ ላይ ካሰፈረ በኋላ በቁጥጠር ሥር ውሎ በፅንፈኝነት ተከሷል።

ፑቲን በቅርቡ የዶሮ እና የእንቁላል ዋጋን ቀንሰዋል። ይህ ያደረጉት የኑሮ ውድነት ያደቀቃቸው ሩሲያዊያን ተቃውሞ ካሰሙ በኋላ ነው።