መርከብ

24 ታህሳስ 2023, 08:54 EAT

ትናንት ቅዳሜ በሕንድ ውቅያኖስ ኬሚካል የጫነ መርከብ ከኢራን በተነሳ ሰው አልባ አውሮፕላን መመታቱን የአሜሪካ ጦር አስታወቀ።

ፔንታገን እንዳለው ኬም ፕሉቶ የተባለው ዕቃ ጫኝ መርከብ ከዒላማቸው ጋር በሚላተሙ የድሮን አይነቶች ጥቃት የተፈጸመበት ከሕንድ የባሕር ዳርቻ 370 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ የውሃ አካል ላይ ነው።

ጥቃቱን ተከትሎ በመርከቡ ላይ እሳት ተነስቶ የነበረ ሲሆን በሰው ላይ ግን የደረሰ ጉዳት የለም ተብሏል።

ለዚህ ጥቃት ቴህራን በቀጥታ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ ባትልም፤ የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዥ፤ አሜሪካ እና አጋሮቿ በጋዛ ወንጀሎችን መፈጸማቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ ቴህራን ሌሎች የባሕር ላይ መተላለፊያዎችን ለመዝጋት ትገደዳለች ብለዋል።

ብርጋዴየር ጀነራል ሞሐመድ ሬዛ ናቅዲ ይህ ማስጠንቀቂያቸው የሜደትራኒያን ባሕር እንዲሁም በስፔን እና ሞሮኮ መካከል ያለውን የጂብላተራል መተላላፊያ እንደሚጨምር ተናግረዋል።

የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዥ ይህን ጠንካራ አስተያይት ይስጡ እንጂ ቴህራን የውሃ አካላቱን እንዴት ልትዘጋ እንደምትችል ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ከእስራኤል እና ከሐማስ ጦርነት መቀስቀስ ወዲህ በቀይ ባሕር በኩል በሚያልፉ ግዙፍ የጭነት መርከቦች ላይ የሚሳኤል እና የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል።

ለእነዚህ ጥቃቶች ኃላፊነት ሲወስዱ የቆዩት የየመን ሁቲ አማጺያን ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ለገባው ሐማስ ያላቸውን ድጋፍ በይፋ ከገለጹ በኋላ በቀይ ባሕር በኩል አድርገው ወደ እስራኤል የሚያቀኑ መርከቦችን ዒላማ እንደሚያደርጉ በይፋ አሳውቀዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜና አሜሪካ በደቡባዊ ቀይ ባሕር የዕቃ ጫኝ መርከቦች መተላለፊያ መስመር ላይ በሁቲ አማጺያን አማካይነት የተተኮሱ ሁለት ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን መትታ መጣሏን አስታውቃለች።

ከዚህ በተጨማሪም ይህ ዓለም አቀፍ የውሃ አካል ላይ ቅኝት እያደረገ የነበረ የአሜሪካ የባሕር ኃይል መርከብ የቱሂ አማጺያን ከሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች የተነሱ አራት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትቶ መጣሉን አስታውቋል።

የሁቲ አማጺያን ባለፉት ሳምንታት ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ነዳጅ እና የተለያዩ ምርቶችን ጭነው የሚንቀሳቀሱ ግዙፍ መርከቦችን ማጥቃታቸው በነዳጅ እና በሌሎች ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት አለ።

ከእነዚህ ጥቃት እራሳቸውን ለመከላከል የዓለማችን ዋነኛ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅቶች ቀይ ባሕርን ከመጠቀም ይልቅ ረዥም ጊዜ እና ብዙ ነዳጅ አባክነው በደቡብ አፍሪካ በኩል አድርገው ወደ መዳረሻቸው እያቀኑ ነው።

መርከቦች ቀይ ባሕርን ትተው በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል በመጓዛቸው ለተጨማሪ 10 ቀናት 6ሺህ 400 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠበቅባቸዋል።
የምስሉ መግለጫ,መርከቦች ቀይ ባሕርን ትተው በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል በመጓዛቸው ለተጨማሪ 10 ቀናት 6ሺህ 400 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠበቅባቸዋል።

ምዕራባውያን መንግሥታት የሁቲ አማጺያን ይህን መሰል ጥቃት መሰንዘር የቻሉት ከኢራን ወታደራዊ ድጋፍ በማግኘታቸው ነው ይላሉ።

አሜሪካ በቀይ ባሕር ላይ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች ኢራን ዘመቻዎችን በማቀድ እና ጦር መሳሪያ በማቅረብ ተሳትፎ ታደርጋለች ስትል ትከሳለች።

የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ አድሪን ዋትሰን ጥቃቶቹ ኢራን የሁቲ አማጺያን ቀጠናውን እንዲያምሱ የምታደርገው ጥረት አካል ነው ብለዋል።

ፔንታጎን ትናንት ኬም ፕሉቶ የተባለችው መርከብ በኢራን ድሮን መመታቷን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ መርከቡ ከሳዑዲ ተነስቶ ወደ ሕንድ እያቀና ነበር ብሏል።

ይህ ኬሚካል የጫነ መርከብ የላይቤሪያን ሰንደቅ ዓላማን የሚያውለበልብ፣ ባለቤትነቱ የጃፓን እንዲሁም የሥራ ስምሪቱ ቁጥጥር የሚደረግበት በኔዘርላንድስ መሆኑን ፔንታጎን ጨምሮ አስታውቋል።