ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ፍልስጤማዊያን

ከ 9 ሰአት በፊት

እስራኤል 200 የሐማስ እና የኢስላሚክ ጂሃድ አባላትን ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ሥር አውላ ለምርመራ ወደ ግዛቷ እንደወሰደቻቸው ገለጠች።

የእስራኤል መግለጫ እንደሚለው የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች ከሰላማዊ ዜጎች ጋር ተሸሽገው የተገኙ ሲሆን በሰላም እጃቸውን ሰጥተዋል።

እስራኤል እንደምትለው ሐማስን ለማጥፋት በጋዛ ኦፕሬሽን ከጀመረች ጀምሮ 700 ያክል ፍልስጤማዊያን ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር አውላለች።

እስራኤል በዚህ ዘመቻ ከ20ሺህ የማያንሱ ሰዎችን በጋዛ ስለመግደሏ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል።

ሐማስ በእስራኤል እየተገደሉ ያሉት አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት ናቸው ይላል።

ቢቢሲ ይህን በግሉ ማረጋገጥ አልቻለም። እስራኤል ከዚህ ቀደም በምታካሂደው ዘመቻ ምክንያት ሰላማዊ ዜጎች እንዳይጎጉ ጥንቃቄ እንደምታደርግ ገልጣ ነገር ግን ሐማስ ሕዝብ በበዛበት ሥፍራ እየተደበቀ ነው ስትል ወቅሳ ነበር።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንደሚገልጠው ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ 20 ሺህ ፍልስጤማዊያን ሲገደሉ 53 ሺህ የሚሆኑ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ቅዳሜ ዕለት አዲስ መግለጫ ያወጣው የጤና ሚኒስቴር 201 ተጨማሪ ሰዎች ተገድለዋል ያለ ሲሆን ከዚያ ቀደም ባለው ቀን ብቻ 368 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ የእርዳታ ሥራው አባል የሆነው የ56 ዓመቱ ኢሳም አል-ሙግራቢ ከባለቤቱ እና ልጆቹ እንዲሁም ከ70 ዘመድ አዝማዶቹ ጋር በአየር ጥቃት እንደተገደለ አሳውቋል።

እስራኤል ደግሞ አምስት ተጨማሪ ወታደሮቿ መገደላቸውን አሳውቃለች። ይህ የእስራኤል እግረኛ ኃይል ዘመቻ ከተጀመ ጀምሮ በጠቅላላው የተገደሉ የእሰራኤል ወታደሮች ቁጥር 144 ያደርሰዋል።

የእስራኤል ጦር አሁንም በጋዛ የሚያካሂደውን የአየር ጥቃት የቀጠለ ሲሆን ሰላማዊ ዜጎች ለቀው እንዲወጡ እያስጠነቀቀ ነው።

ቅዳሜ ዕለት ሐሳሕ አስትራሽ የተሰኘው ወደ ጋዛ የጦር መሣሪያ በማስገባት የተጠረጠረውን ግለሰብ በአየር ጥቃት መግለዷን እስራኤል ብትገልጥም ከሐማስ የተሰጠ ማረጋገጫ የለም።

በሌላ ዜና የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና የእሰራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በጋዛ ስላለው ጦርነት በስልክ አውርወተዋል።

ባይደን “ሰላማዊ ዜጎችን ስለመጠበቅ፣ ሰብዓዊ እርዳታ ስለሚሰጡ ሰዎች እና ሰላማዊ ሰዎችን ከጦርነት ቀጣና ስለማስወጣት” አውርተዋል ሲል ዋይት ሐውስ መግለጫ አውጥቷል።

ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በበኩላቸው “እስራኤል ያሰበችውን እስክታሳካ ድረስ ጦርነቱን እንደምትቀጥል ግልፅ አድርገዋል” ማለታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።

የእስራኤል ጦር ኃይል በሰሜናዊ ጋዛ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ኦፕሬሽን እያካሄደ መሆኑን የገለጠ ሲሆን ወደ ደቡባዊ ጋዛ እያቀና እንደሆነም ተናግሯል።

የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው እሰራኤል ሰላማዊ ዜጎች ለቀው እንዲወጡ ባዘዘችው ሥፍራ 150 ሺህ ያክል ሰላማዊ ዜጎች ይኖራሉ።

የፍልስጤም ዜና ወኪል የሆነው ዋፋ ቅዳሜ ባወጣው ዘገባው ቡሬጂ የተሰኘው የስደተኞች መጠለያ የቦምብ ጥቃት ደርሶበታል።

ቢቢሲ ከእስራኤልም ሆነ ከፍልስጤም የሚወጡ ዘገባዎችን በግሉ ማረጋገጥ ባይችልም በያዝነው የአውሮፓውያኑ ወር መጀመሪያ በጋዛ ሰርጥ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ፍልስጤማዊያንን ቪድዮ ማረጋገጥ ችሏል።