
ከ 9 ሰአት በፊት
ሁለት ማሕፀን ያላት አሜሪካዊቷ እናት 20 ሰዓታት በወሰደ እና ከሚሊዮን አንድ ጊዜ የሚከሰት በተባለ ክስተት በሁለት ቀናት ሁለት ልጆች ወለደች።
በአላባማ ግዛት ነዋሪ የሆነችው ኬልሲ ሃቸር ማክሰኞ ዕለት አንዲት ሴት ልጅ ስትገላገል ረቡዕ ደግሞ ሌላ ሴት ልጅ ደግማለች።
ኬልሲ የተገላገለችው በርሚንግሃም በሚገኘው የአላባማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ነው።
የሁለት “ተዓምራዊ ልጆቿን” በሰላም መገላገል በማሕራዊ ሚድያዋ ያሰፈረችው ኬልሲ የሕክምና ሙያተኞቹን “አስደናቂ” ስትል ገልጣቸዋለች።
ሕፃናቱ በሁለት የሴት እንቁላል፤ በተለያዩ የወንደ ዘር ፍሬ የተረገዙ ብዙ ግዜ የተለያየ መልክ ያላቸው መንትያዎች [fraternal twins] ናቸው ተብሏል።
ሁለቱ ጨቅላቸው ምንም እንኳ መንትያ ቢሆኑም በ20 ሰዓታት በመወላዳቸው የተለያዩ የልደት ቀን ይኖራቸዋል።
አሜሪካዊቷ እናት በማሕበራዊ ሚድያ ገጿ እንዳሰፈረችው ቤተሰቡ አሁን በሰላም ወደ ቤት ተመልሶ የገና በዓልን ለማክበር እየተሰናዳ ይገኛል።
የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል አዋላጅ ለቢቢሲ እንደገለጡት እናት እና ልጆች በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን እንዲህ ዓይነት ነገር “በአንድ የሕክምና ባለሙያ ሕይወት ታይቶ የማይታወቅ ነው።”
ኬልሲ የ17 ዓመት ታዳጊ ሳለች ነው ሁለት ማሕፀን እንዳላት የተነገራት። ይህ እንደ ዩኒቨርሲቲው ገለጣ 0.3 በመቶ ሴቶች ላይ ብቻ የሚታይ ነው።
ሆስፒታሉ እንደሚለው ሁለት ማሕፀን ያላቸው ሴቶች በሁለቱም ማሕጸን የመጸነሳቸው ዕድል “ከአንድ ሚሊዮን አንድ ጊዜ ብቻ የሚከሰት ነው።”
- በእርግዝና ወቅት ነፍሰጡሮችን ለሚያሰቃየው ህመም ፈውስ የሚሆን ፍንጭ ተገኘ24 ታህሳስ 2023
- ‘ሆሊውድ ለኔ ሀብትና ትምህርት ቤቴ ነው’ – ፍርቱና ገብረስላሴ23 ታህሳስ 2023
- በርካቶች ካናዳን ለመኖሪያነት ለምን ይመርጧታል?23 ታህሳስ 2023
መሰል ክስተቶች በዓለማችን የሚታዩት በጣም በጥቂቱ ነው።
በ2019 አንድ የባንግላዴሽ ዶክተር አንዲት ሴት አንድ ልጅ ያለጊዜው ከወለደች ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ በሌላኛው ማሕጸኗ አርግዛ የነበረውን ልጅ መገላገሏን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ኬልሲ ከዚህ ቀደም ሶስት ጊዜ ጤናማ እርግዘና ያሳለፈች ሲሆን በዚህኛው ዙርም በአንድ ማሕፀኗ ብቻ እንዳረገዘች ነበር የምታውቀው።
ነገር ግን የአልትራሳውንድ ምርመራ ስታደርግ በሌላኛው ማሕፀኗም ተጨማሪ ልጅ እንዳላት መመልከት ቻለች።
“ደነገጥኩ. . . የምናየውን ማመን አልቻልንም ነበር” ስትል በወቅቱ የተሰማትን ታወሳለች።
ይህ ከሆነ በኋላ ነው በኢንስታግራም ገጿ የእርግዝና ሂደቷን ለተከታዮቿ ማጋራት የጀመረችው።
ልጆቹን ካዋለዱት ዶክተሮች መካከል አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ዴቪስ “ሁለቱም ሕፃናት በሁለቱ ማሕፀኖች ለማደግ የሚያስችል በቂ ቦታ ነበራቸው” ይላሉ።
ይህ የሆነው ከሌላው የተለመደ የመንታ ልጆች የማሕፀን ውስጥ ዕድገት በተለየ ሁለቱም ሕፃናት የየራሳቸው ማሕፀን ስላላቸው እንደሆነ ያብራራሉ።
ኬልሲ ወደ ሆስፒታል ስታቀና ለሁለቱም ልጆች የተለያየ ክትትል ሲደርግላት የቆየ ሲሆን ስትወልድም ለሁለቱ ሕፃናት የተለያዩ ዶክተሮች ናቸው የተመደቡት።
የሆስፒታሉ ባልደረባ የሆኑት ሽዌታ ፓቴል ባልደረቦቻቸው ከተለመደው የእርግዝና ክትትል ባገኙት እውቀት ነው በተሳካ ሁኔታ ያዋለዱት ይላሉ።
የመጀመሪያዋ ልጅ ሮክሲ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ምሽት 1፡45 ማክሰኞ በምጥ ስትወለድ፤ ሬቤል ተብላ የተሰየመችው ሁለተኛዋ ልጅ ደግሞ በቀዶ ሕክምና ተወልዳለች።
ዶክተር ዴቪስ ሁለቱ ሕፃናት የማይመሳሰሉ መንታዎች [fraternal twins] የተባሉት ሁለቱም ከተለያየ እንቁላል የተወለዱ ስለሆኑ ነው ይላሉ።