
Daniel Shibeshi
¤ የእኔና ቤተሰቦቼ ህይወት አደጋ ላይ ነዉ

… ትላንት ቅዳሜ (13/04/2016 ዓ.ም) ከቀኑ 9:30 ገደማ ይሆናል። በቁጥር ከ40 በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ሲቪል የለበሱ የደህንነት አካላት በተለያዩ ተሽከርካሪዎች መኖሪያ ቤቴንና ሰፈሩን በመክበብ፤ ቀጥለውም በቀጥታ የግቢዬን አጥር በር ሰብረው ገቡ።
እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔም ሆንኩኝ ባለቤቴ በቤት አልነበረንም። እኔ ከአዲስ አበባ ውጭ ወደ 400 ኪሜ ያህል ርቄ ለግል ሥራ ወጣ ብያለሁ። ባለቤቴም ዕቃ ልትገዛ መርካቶ ሄዳ ነበር ። እቤት የነበሩት በእንግድነት ለህክምና የመጣችዉ የባለቤቴ ታላቅ እህት እና ሁለት ልጆቼ ናቸው።
በሰዓቱ በጣም ከፍ ያለ ድምፅና ጫጫታ የሰሙ እቤት የነበሩ ተደናግጠው ምንድነው? ምን ተፈጠረ? እያሉ ከሳሎን ወደ ግቢ ተንጋግተው ሲወጡ በቅጽበት ግቢው በፖሊሶች ተወሮ እና ተጥለቅልቆ አገኙት። ከላይ እቤት የነበሩት ብዬ የጠቀስኳቸዉ ያልጠበቁት ነገር በመሆኑ ከባድ ድንጋጤ ላይ ወደቁ፤ ወዲያው ከእነዛ ግቢውን ያጥለቀለቁት የፀጥታ አካላቶች በልጆቼና በእንግድነት በመጣችው የሚስቴ እህት ላይ ሽጉጥና ክላሽ በጆሮ ግንዳቸውና በአፍንጫቸው ደገኑ። በድንፋታ አስፈራሯቸው። የባለቤቴን እህት እየደበደቧት መሬት ላይ እንድትቀመጥ አደረጓት። ከዛ በተከታታይ ፋታ ሳይሰጡ ዳንኤል የት ነው ያለው?? እያሉ ማፋጠጥ ጀመሩ።
ቶሎ ንገሩን በማለት ልጆቼና የባለቤቴን እህት አስጨነቋቸው። ህፃናትን አስለቀሱ፣ ሽብር ፈጠሩባቸው። ይህን ነው የማይባል የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ከተቷቸው። ቀጥለውም ቶሎ ብለሽ «እቤት ለቅሶ ስላለ ቶሎ ና ብለሽ ንገሪው፤ ሌላ ቃል ትንፍሽ እንዳትይ በማለት አስገድደው ወደ እኔ ሰልክ አስደወሉ፤ እንደ ጋጣሚ የእኔ ስልክ አልሰራ ሲሏቸዉ ወደ ባለበቴ አስደውለው ቀጥታ ወደ ቤት እንዲትመጣ ተነገራት። እሺ አለቻቸው።»
ይሁን እንጂ ባለቤቴ እስኪትመጣ ድረስ አላስችል ብሏቸው የቤቴ መኝታ ክፍሉን በር ሰብረው ገቡ። በረበሩ፣ የመኝታ ክፍሌ እቃዎች አመሠቃቀሉ ምንም ሳያስቀሩ ሁሉንም ነገር ምንቅርቅር አድርገው ፈተሹ። እኔን ለመያዝ የተሰማራውን ኃይል የመራው ፖሊስ ኃላፊ «በወንጀል የሚያስጠይቅ ቁስና ሰነድ አለማግኘታቸውን ለአለቃው ሲያብራራ “ምንም ነገር አልተገኘና ምን እናደርግ?” ብሎ እዛው በር ላይ ቆሞ በስልክ ሪፓርት ሲያደርግ ያዳመጡ ሰዎች ነግረውኛል። በኋላ ከአለቃው በተሰጠው ተጨማሪ ትዕዛዝ መሰለኝ «ሁለት ላፕቶፖችን ጨምሮ ከቅንጅት እስከ ኢዜማ ያሉ በርካታ ዶክሜንቶችን፣ ሀርድዲስኮችን፣ ማስታወሻ ደብተሮችን፣ ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችንና የህትመት ውጤቶችን ከቤቴ ጭነው ወሰዱ።»
እንደሚታወቀው በአብዛኛው ለተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍ እንዳልደረሳቸውና በሶፍት-ኮፒ እንደሚያጠኑ ይታወቃል። ይህንን ሆኖ ሳለ ከልጆቼ መኝታ ክፍል ያገኙትንና ልጆች የሚያጠኑበትን ኮምፕዩተሮችን ጭምር ሰብስበው ወሰዱ። የልጆቼ ኮምፕዩተር እንዲተውላቸው ጎረበቶቼም ጭምር ቢማጸኑም ለመተው ፈቃደኛ አልሆኑም።
ልብ በሉ! «ይህን ሁሉ ሲያደርጉ እኔን ለመያዝ ሆነ ቤቴን ለመበርበር የሚያስችል የፍርድ ቤት የብርበራና የመያዣ ትዕዛዝ የላቸውም።»
አሁን ደግሞ ድርጊቱ ከተፈጸመበት ሰዓት ጀምሮ በተለያየ መንገድ ባሰባሰብኩ መረጃ እንዳረጋገጥኩት ከሆነ #ህይወቴ በአደጋ ውስጥ ነው። የቤተሰቦቼም ሕይወት በከባድ ሥጋት ውስጥ ወድቋል። ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ ተጨንቋል። ምን መሆን እንዳለብኝና ለማን ወደየት አቤት ማለት እንዳለብኝ፣ እንዴትስ ነፍሴን ማዳን እንዳለብኝ ግራ ገብቶኛል።
ውድ የሀገሬ ልጆች አሁን በዚህ ሰዓት ያለ ምንም ምክንያት የእኔና የቤተሰቦቼ እንዲሁም የልጆቼ ህይወት አደጋ ዉስጥ ወድቋል። ከእግዚአብሄር በታች ለጊዜው አንድ አማራጭ ብቻ ነዉ ያየሁት ። ይህንንም ለሚመለከተው ሁሉ ብሎም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለሁበት ሁኔታ ማሳወቅ ነው። ስለዚህ የሚመለከታችሁ ደጋግ ኢትዮጵያዉያን እንዲሁም ሚድያዎች ይህንን ፅሁፍ ፅፌ እንደጨረስኩና ይህንን ተከትሎ የእኔና የቤተሰቦቼ ህይወት ምን ላይ ሊሆን እንደሚችል አላውቅም።
በመጨረሻም፦ ከእንዲህ አይነት ሕግንም፣ ዴሞክራሲንም፣ ሰብዓዊና ባጠቃላይ የዜጎችን መሠረታዊ መብቶችንም ወዘተ እየጣሱ መቀጠል ሀገራችንን፣ ሕዝባችንንም … ብዙ እጅግ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፤ አስከፍሏልም፣ እያስከፈለም ይገኛል። ከዚህ እብደት ለመውጣት የአንበሳ ድርሻው የመንግሥት ነው። በተረፈ መንግሥት የምር ሀገራችንን የማኖር ውጥን ካለው እኛን ማሳደድን ያዝ አድርጎ ውስጡን ይፈትሽ!!!!
ዳንኤል ሺበሺ
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ
___________
All reactions:
11