
ከ 5 ሰአት በፊት
በሺዎች የሚቆጠሩ ከማዕከላዊ እና ደቡብ አሜሪካ አገራት የተውጣጡ ስደተኞች በእግራቸው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ድንበር እያቀኑ ነው።
ሕፃናትና አዋቂዎች ሳይቀሩ 8 ሺህ ገደማ የሚሆኑ በአብዛኛው ከቬንዝዌላ፣ ኩባ እና ሜክሲኮ የመጡ ስደተኞች ናቸው ወደ አሜሪካ ድንበር እያቀኑ ያሉት።
ግለሰቦቹ “የደኅነት ስደት” የሚባል በግዙፍ ቀይ ቀለም የተፃፈ ፅሑፍ ይዘው ነው ወደ ድንበር እያቀኑ ያሉት።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ለጉብኝት ወደ ሜክሲኮ መዲና ለመምጣት ማቀዳቸው በተሰማ ማግስት ነው ይህን የሆነው።
ብሊንከን ስደተን ለመቆጣጠር ከሜክሲኮ መንግሥት ጋር ስምምነት ይገባሉ ተብሎ ተገምቷል።
በአውሮፓውያኑ 2022 እና 2023 ወደ አሜሪካ ለመግባት አቅደው ሜክሲኮ ድንበር ላይ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን በላይ ነው።
በመስከረም 2023 ብቻ የአሜሪካ ድንበር ጥበቃ 200 ሺህ ያህል ግለሰቦች የሜክሲኮ ድንበርን አቋርጠው ሊገቡ ሲሉ እንደያዛቸው የዩኤስ ሃገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት መረጃ ያሳያል።
- ከወለጋ ተፈናቅለው በአማራ ክልል ተጠልለው ያሉ ወደመጣንበት እንድንመለስ ተገደናል አሉ23 ታህሳስ 2023
- ‘ረሃብ በረታብን’ – ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በልመና ያጨናነቋት የጂቡቲ ከተማ18 ታህሳስ 2023
- እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ የሐማስና ኢስላሚክ ጂሃድ አባላትን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ገለጠች24 ታህሳስ 2023
የፈረንጆቹ ገና ዋዜማ የስደተኞች ጉዞ የተነሳው ከጉዋቲማላ ከምትዋሰነው የደቡብ ሜክሲኮዋ ታፓቹላ ከተማ ነው።
ጉዞውን የተቀላቀለ አንድ ሆንዱራሳዊ ስደተኛ ሕይወቱን ለማጥፋት ያሰበ አንድ የወንጀለኞች ቡድንን ሸሽቶ ስደት እንደመረጠ ይናገራል።
ለሮይተርስ ዜና ወኪል ድምፁን የሰጠው ሆዜ ሳንቶስ “በጣም ስለፈራሁ ወደ ሜክሲኮ አቅንቼ ወደ አሜሪካ ለመግባት ተስፋ ይዤ መጥቻለሁ” ይላል።

ባለፈው አርብ የሜክሲኮው ፕሬዝደንት አንድሬ ማኑዌል ሎፔዝ ኦብራዶር፤ የስደተኞችን ጉዳይ አንድ ለማለት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆናቸው ተናግረዋል።
የሜክሲኮው መሪ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ረቡዕ ተገናኝተው ለማውራት ዕቅድ ይዘዋል።
ዋይት ሐውስ ባወጣው መግለጫ ብሊንከን በምዕራብ በኩል ያለውን “ያልተለመደ የስደተኞች ጉዞ” በተለመከተ ውይይት እንደሚያደርጉ ገልጧል።
መግለጫው ጨምሮ ሁለቱ ሃገራት “የድንበር የደኅንነት ጉዳይን ለመመከት” ውይይት እንደሚያደርጉ አሳውቋል።
ወደ አሜሪካና እና ሜክሲኮ ድንበር የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር በተለይ ከ2021 በኋላ ቁጥሩ እጅግ እየጨመረ መጥቷል።
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በርካታ የስደተኞች ስብስብ ወደ ሜክሲኮና አሜሪካ ድንበር ሲያቀና ከሜክሲኮ ፖሊስ ጋር መጋጨቱ ይታወሳል።