ቤኒንያሚን ኔታኒያሁ

ከ 5 ሰአት በፊት

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒንያሚን ኔታኒያሁ አገራቸው ከሐማስ ጋር የገባችው ጦርነት ትልቅ ዋጋ እያስከፈላት ነው አሉ።

የአገሪቱ ጦር ባለፉት ሁለት ቀናት በርካታ የእስራኤል ወታደሮች መገደላቸውን ያስታወቀ ሲሆን እስራኤል የእግረኛ ኃይሏን ወደ ጋዛ ካስገባች ወዲህ ከ154 ያላነሱ ወታደሮቿ ተገድለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ግን “ምንም ምርጫ ስለሌለ” መዋጋታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳላ በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ ጤና ሚንስቴር የእስራኤል ጦር ትናንት እሁድ በመጠላያ ጣቢያ ላይ ባደረሰው የቦምብ ድብደባ ቢያንስ 70 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።

ሚኒስቴሩ ከመስከረም 26ቱ ጥቃት ወዲህ በጋዛ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ20 ሺህ በላይ መሆኑን ይገልጻል። ከእነዚህ ሟቾች መካከል አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች ናቸው። ሕይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ ከ54 ሺህ ያላሱ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ከትናንት በስቲያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእስራኤል ወታደሮች መገደልን ተከትሎ ኔታኒያሁ በሰጡት መግለጫ “ይህ በጣም ከባድ ቀን ነው” ካሉ በኋላ ሠራዊታቸው ሐማስን የማጥፋት እና ታጋቾችን ነጻ የማውጣት ዕቅዱን እስኪያሳካ ድረስ “በሙሉ ኃይሉ” መዋጋቱን ይቀጥላል ብለዋል።

“ግልጽ መሆን ያለበት አንድ ነገር አለ። ይህ ረዥም ጦርነት ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ኔታኒያሁ።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረበት ዕለት አንስቶ እስካሁን ድረስ ከ8 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተዋጊዎችን መግደሉን አስታውቋል።

የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ታጣቂ ቡድኑ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በድንገት ድንበር ተሻግሮ ከ1200 በላይ ሰዎች ገድሎ እና 240 ታጋቾችን ከወሰደ በኋላ መጀመሩ ይታወሳል።

እስራኤል በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ግን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰላማዊ ሰዎች ከመገደላቸው በተጨማሪ በጋዛ ከፍተኛ የሆነ የመሠረተ ልማት ውድመት አስከትላለች።

ይሁን እንጂ እስራኤል በወታደራዊ እርምጃዎቿ ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለሁ የምትል ሲሆን ሐማስ ሕዝብ በሚሰበሰብበት እራሱን ይደብቃል ትላለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን የእስራኤል አጋሮች አገሪቱ ለሰላማዊ ሰዎች የምታደርገውን ጥበቃት እንድታጠናክር እያሳሰቡ ይገኛሉ።

ባለፉት ጥቂት ቀናት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል።
የምስሉ መግለጫ,ባለፉት ጥቂት ቀናት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከጠቅላይ ሚንስትር ኔታኒያሁ ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር ሰላማዊ ሰዎችን መጠበቅ “እጅግ ወሳኝ” መሆኑን ስለመናገራቸው ዋይት ሃውስ አስታውቋል።

ሁለቱ መሪዎች በስልክ ንግግራቸው የተኩስ አቁም ማድረጉ ለሐማስ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ ስለተግባቡ ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ ሲባል የተኩስ አቁም ማድረግ እንደ አማራጭ አልተነሳም ተብሏል።

ባሳለፍው ሳምንት መጨረሻ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲሁ ከፍተኛ መጠን ያለው የሰብዓዊ እርዳታ ጋዛ እንዲደርስ የውሳኔ ሃሳብ ቢያሳልፍም ምክር ቤቱ የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረስ በሚለው ላይ ግን ሳይስማማ ቀርቷል።

ባለፉት ቀናት በግብጽ ሁለቱን ተዋጊ ኃይሎች ለጦርነቱ ፋታ እንዲሰጡ ለማግባባት ሲደረግ የነበረው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።