
25 ታህሳስ 2023, 15:44 EAT
የጎርጎሮሳውያንን የዘመን አቆጣጠር ለሚከተሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዛሬ የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ነው ነው።
ክብረ በዓሏ በተለያዩ አገራት በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ቢሆንም እየሱስ ተወልዶባታል በምትባለው የፍልስጤሟ ከተማ ቤተልሔም ደስታ ርቋታል።
ከጋዛ ጦርነት ጋር ተያይዞ የቤተልሔም ከተማ የሐዘን ድባብ ወርሷታል።
በዘንድሮውም የገና አከባበር እንዲሰረዝ ተደርጓል። ከዚህ ቀደም በገና ወቅት በቤተልሔም የሚገኘው ማንገር አደባባይን ያጥለቀልቁ የነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች እና የእምነት ተጓዦች ዘንድሮ የሉም።
“ከተማዋ ወና ሆናለች። ደስታ፣ ልጆች፣ ሳንታ የሉም። በዚህ ዓመት ምንም አይነት በዓል የለም” ስትል እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ በምትገኘው ቤተልሔም ነዋሪ የሆነችው ማዴሊን ትናገራለች።
በገና ወቅት በዋናው አደባባይ መካከል የሚቆመው የገና ዛፍ በዘንድሮው የለም። የገና ዘፈኖችም ሆነ መገበያያ ስፍራዎች የሉም። ቤተልሔም ባዶ ሆናለች፣ ሐዘን ወርሷታል።
እየሱስ በበረት የተወለደበትን የሚያሳየውም ትዕይንት ህጻኑ እየሱስ በፍርስራሽ ክምሮች እና በሽቦ ታጥሮ በሚያሳይ ትዕይንት ተተክቷል። ይህም የጋዛ ህጻናት እያለፉበት ያለውን ለማሳየት ነው።
የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ደምቆ የሚከበርባት የኔቲቪቲ (ልደት) ቤተ ክርስቲያን በዘንድሮው ወና ሆናለች። የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋይ የሆኑት አባ ኤይሳ ታልድጂያ ከተማዋ የቀድሞ ጥላዋን እንደምትምመስል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በዚህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለ12 ዓመታት ያህል በካህንነት አገልግያለሁ። የተወለድኩትም በቤተልሔም ነው። ከተማዋን እንደዚህ ሆና አይቼያት አላውቅም፤ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት እንኳን” ይላሉ።
“በጋዛ ውስጥ ወንድሞች እና እህቶች አሉን። ለዚያም ነው በዓሉን ለማክበር ፈታኝ የሚያደርገው። ነገር ግን በጸሎት አንድ ላይ ነን” ይላሉ።

- ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት የጋዛ ነዋሪዎች ከሞት ጋር ተፋጠዋል22 ታህሳስ 2023
- በተለያዩ ቀለማት የሚሠራው የአንገት ልብስ [ከፊያህ] እንዴት የፍልስጤማውያን መለያ ሆነ?20 ታህሳስ 2023
ጃውዳት ሚክሃኤል የሚኖረው በቤተልሔም ቢሆንም አጠቃላይ ቤተሰቡ ግን የሚኖሩት በጦርነት እየተናጠች በምትገኘው ጋዛ ውስጥ ነው።
ወላጆቹ ወንድሙ እና ሌሎች በርካታ የቤተሰቡ አባላት እና ዘመዶቹ ከጋዛ በስተምስራቅ በምትገኘው ሼጃያ ሆሊ ፋሚሊ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።
የእስራኤልን ጥቃት ፈርተው በዚህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ በርካቶች ከሞት ጋር ተፋጠው ይገኛሉ። የእስራኤል ጦር ቤተ ክርስቲያኗን ኢላማ ማድረጋቸው የተነገረ ሲሆን በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ጥቃት ከፍተው እናት እና ልጅም መግደላቸው ተዘግቧል።
ቢቢሲ ከጃውዳት ጋር እየተነጋገረ እያለም አባቱ ሃንና ሚክሃኤል ደወሉ።
የስልክ መስመሩ ይቆራረጣል፣ ኢንተርኔቱም ደካማ ነው። ጃውዳት ግን እንዲያም ሆኖ አባቱን በጨረፍታም እንኳን ለማየት እየጣረ ነው።
አባትየው ለልጃው ቤተሰቡ ሁሉ ደህና መሆናቸው ተናገሩ። ከሁለት ሳምንት በኋላም ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን መውጣት እንደቻሉ የተናገሩት አባት ምግብ እየፈለግን ነው አሉ። በቤተክርስቲያኑ ዙሪያ የተረፈው የፍርስራሽ ክምር ብቻ ሲሆን ሁሉም ሱቆችም እንደተቃጠሉ ገለጹ። “ሙሉ በሙሉ ወድሟል” ይላሉ አባት።
ኮሙኒኬሽን ተቋርጧል፤ ውሃም የለም አሉ። ያላቸው ምግብ በጣም እየተመናመነ እንደሆነም ለቢቢሲ አስረዱ። “በህይወት ለመቆየት ብቻ ትንሽ ምግብ አለን። ሆድን መሙላት ግን አይታሰብም” ሲሉም ለቢቢሲ ተናገሩ።
የባለፈውን ዓመት የገና በዓል ድምቀትንም አስበው እንዴት የተለየ ነበር ሲናገሩ በለቅሶ ነው።
“በእንደዚህች ባሉ ቀናት ቤተ ክርስቲያናችንን እናስጌጥ ነበር። መዝሙሮችም ይዘመራሉ። ምዕመናኑም ለማገልገል ይመጣሉ። በአሁኑ ወቅት ግን ከዚህ መከራ እንዲያወጣን እየጸለይን ነው” አሉ።
ቤተሰቡ በቅርቡ ከፍተኛ ኃዘን ደርሶበታል።

ከሳምንት በፊት በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ተጠልለው የነበሩት ናሂዳ ካሊል አንቶን የተሰኙት የጃውዳት አያት ወደ መታጠቢያ ቤት ሲሄዱ ሁለት ጊዜ በጥይት ሆዳቸው ላይ ተመትተው ተገደሉ። አክስቱ ሳማር ካማል እናቷን ለመርዳት ስትጣደፍም ጭንቅላቷን በጥይት ተመትታ ተገድላለች።
ጃውዳት የቤተሰቦቹን ሞት እና የቀብር ስነ ስርዓትም ፎቶዎችም ለቢቢሲ አሳይቷል።
ከጦርነቱ መጀመሪያ ጀምሮ ቤተሰቦቹ በዚህች ቤተክርስቲያን ነበር ተጠልለው የነበሩት። ቤተ ክርስቲያኗ ከጥቃት አላተረፋቸውም የሚወዷቸውን ሁለት የቤተሰብ አባላት ግድያ አይተዋል። እዚያም ቀብረዋቸዋል።
ቤተሰቡ ለተገደሉት የቤተሰቦቻቸው አባላት የእስራኤል አላሚ ተኳሾችን ተጠያቂ አድርገዋል። የእስራኤል የመከላከያ ሰራዊት ምርምራውን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
አባትየው ከእንባቸው ጋር እየታገሉ ሁለቱ የቤተሰቡ አባላት ሲገደሉ እንደተመለከቱ ይናገራሉ። “መቋቋም የማንችለው ድንጋጤ ነው የደረሰብን” ይላሉ።
እያለቀሱ ብዙ መናገር ያልቻሉት አባት ለቢቢሲ ይቅርታ በመጠየቅም “ ይቅርታ። በጣም ከባድ ነው። ብዙ መከራ እየደረሰብን ነው” አሉ።
ቢቢሲ ከአባት ጋር እያወራ እያለ የፍንዳታ ድምጽ የተሰማ ሲሆን ጃውዳትም ሳይወድ አባቱን በግድ ተሰናበተ።
ትናንትና ጥዋት በቤተልሔም የቤተ ክርስቲያን ደወል ሲደወል የእየሱስ ልደት ትዕይንት በፍርስራሽ በተከበበት ስፍራ የአካባቢው ነዋሪዎች ተሰባስበው ነበር። የአረብኛ መዝሙሮች በድምጽ ማጉያዎች የተሰሙ ሲሆን ሰላም እንዲሰፍን እና ህጻናቱንም እንዲጠብቃቸው ጸሎትም ነበር።
በርካታ ነዋሪዎች መሃል ላይ ትልቅ የፍልስጤም ሰንደቅ ዓላማንም ይዘው እያውለበለቡ ነበር።
የእየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ፒዛባላም በቤተልሔም ተገኝተው ነበር። ባህላዊውን ጥቁር እና ነጭ የፍልስጤም ስካርፍም ለብሰው ነበር።
ወደ ኔቲቪቲ ቤተክርስቲያን ከመግባታቸውም በፊት ይህ “የዘንድሮው በጣም የሚያሳዝን የገና በዓል ነው” ሲሉም ተናገሩ።
“በአሁኑ ወቅት በጦርነት ውስጥ ነው ያለነው፣ በአስከፊ ጦርነት ውስጥ። ወገኖቻችንን የጋዛ ህዝብን እያሰብነው ነው። ሁለት ሚሊዮን ህዝብ እየተሰቃየ ነው” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላለልፈዋል።
አክለውም “የተኩስ አቁም በቂ አይደለም” ሲሉም ተናገሩ።
“ እነዚህ ግጭቶች በዘላቂነት ሊቆሙ ይገባል። ጥቃት የሚወልደው ግፍን እና ጥቃትን ብቻ ነው” አሉ

ከማንገር አደባባይ ጥቂት እርምጃዎች ርቀት ያሉትም የቅርሳቅርስ መሸጫ ሱቆች ባልተለመደ መልኩ ሰው ርቋቸዋል። ዝነኞቹ የፍልስጤም ስካርፎች፣ የትራስ መሸፈኛ ልብሶች እና ቅርሶች ከሱቁ ውጭ ተንጠልጥለው ይታያሉ።
ወቅቱ ገበያው የሚደራበት ቢሆንም ዘንድሮ ግን ምንም የለም።
“በጋዛ በርካታ ሰዎች በተገደሉበት ሁኔታ በዓልን ልናከብር አንችልም” በማለትም ከማንገር አደባባይ ወጣ ብሎ በሚገኘው ገበያ የሱቅ ባለቤት የሆኑት አቦድ ሱቡህ ተናግረዋል።
ከተማዋንም ሆነ ንግዳቸው በዚህ መልኩ ቀዝቅዞ ማየት እንደሚያሳዝን የሚናገሩት እኚሁ ግለሰብ ቢሆንም የገናን በዓል ዘንድሮ ማክበር ስህተት ነው ይላሉ። “ በአሁኑ ወቅት ደስተኛ መሆን አንችልም። ሩቅ አይደለንም ያለነው። አሁንም በፍልስጤም ውስጥ ነን” ብለዋል።