
26 ታህሳስ 2023
በርካታ ሕንዳዊያንን ያሳፈረውና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን እያዘዋወረ ነው ተብሎ የተጠረጠረው አውሮፕላን በስተመጨረሻ ሕንድ አርፏል።
አውሮፕላኑ ፈረንሳይ የሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ለቀናት እንዲቆይ ተደርጓል።
ኤርባስ ኤ340 የተሰኘው የግል አውሮፕላን ከዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ወደ ኒካራግዋ እያቀና ነበር።
አውሮፕላኑ ነዳጅ ለመቅዳት ባረፈበት ወቅት ነው ፖሊስ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን እያዘዋወረ ሊሆን ይችላል ሲል እንዳይንቀሳቀስ ያገተው።
276 ሰዎች ወደ ሕንድ ሲመለሱ ሁለት ሕፃናትን ጨምሮ 25 ሰዎች ፈረንሳይ ውስጥ ጥገኝነት ጠይቀው ቀርተዋል።
ሁለት በሕገ-ወጥ ሰው ማዘዋወር የተጠረጠሩ ግለሰቦችም ለምርመራ ፈረንሳይ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርገው ነበር።
ነገር ግን ሁለቱ ሰዎች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነፃ እንዲወጡ ሆኗል።
- ኢትዮጵያ ተቀምጦ ከአማዞን ዕቃ መግዛት ይቻላል? ዶላር የተጫነበት ኤቲኤም ካርድስ ከየት ይገኛል?25 ታህሳስ 2023
- በሺዎች የሚቆጠሩ ከደቡብ አሜሪካ የተውጣጡ ስደተኞች አንድ ላይ ወደ አሜሪካ ድንበር አቀኑ25 ታህሳስ 2023
- “ትግራይ ቀጣይዋ ሆሊውድ እንድትሆን ነው የምፈልገው”- ፍርቱና ገብረ ሥላሴ25 ታህሳስ 2023
ሌጀንድ ኤርላይንስ የተሰኘው ድርጅት ንብረት የሆነው አውሮፕላን በሙምባይ ሰዓት አቆጣጠር ከእኩለ ለሊት በኋላ ነው ያረፈው።
ባለፈው ሐሙስ ነው ከፓሪስ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው ሻሎን-ቫትሪ አየር ማረፊያ እንዳይንቀሳቀስ የታገደው።
ፖሊስ አውሮፕላኑ ውስጥ ካሉ ተሳፋሪዎች መካከል የተወሰኑት “የሕገ-ወጥ ዝውውር ሰለባ ናቸው” የሚል ጥቆማ ከደረሰው በኋላ ነው አውሮፕላኑ እንዳይንቀሳቀስ ያገደው።
አውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት አብዛኛዎቹ ዩኤኢ የሚሠሩ ሕንዳዊያን መሆናቸው ይታመናል።
አንድ ሶስተኛ ተሳፋሪዎች ደግሞ ከምዕራባዊቷ የሕንድ ግዛት ጉጃራት የመጡ መሆናቸው ተዘግቧል።
የፈረንሳይ ባለሥልጣናት እንደሚያምኑት ተሳፋሪዎቹ ወደ ኒካራግዋ እያቀኑ ያሉት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አሊያም ካናዳ ለመግባት አቅደው ስለነበር ነው።
አውሮፕላኑ ወደ ሕንድ የተመለሰው ምንም ዓይነት ወንጀል ሳይፈፅም ስለቀረ ነው ወይ የሚለውን ጥያቄ ባለሥልጣናት እስካሁን አልመለሱም።
አውሮፕላኑ በዕቅዱ መሠረት ወደ ኒካራግዋ መሄድ ሲገባው ወደ ሙምባይ ለምን እንደተመለሰም ግልፅ አይደለም።
ሌጀንድ አየር መንገድ የሮማንያ የግል አውሮፕላን ድርጅት ሲሆን አራት አውሮፕላኖች እንዳሉት ፍላይትራዳር የተሰኘው የበረራ ቁጥጥር ድረ-ገፅ ይጠቁማል።