በሩሲያ ላይ የተፈጸመው ጥቃት

ከ 7 ሰአት በፊት

ሩሲያ በጥቁር ባህር በሚገኘው የጦር መርከቧ ላይ በዩክሬን በተፈጸመባት ጥቃት ጉዳት መድረሱን አረጋገጠች።

ከጦር መርከቦቿ አንዱ ላይ ጉዳት መድረሱንም ሩሲያ አስታውቃለች።

ጥቃቱ የተፈጸመው ሩሲያ በጠቀለለቻት ክሪሚያ ውስጥ በምትገኘው የፊዮዶሲያ ወደብ ሰኞ ምሽት መሆኑም ተገልጿል።

እንደ ሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ከሆነ በጥቃቱ ግዙፉ የመርከብ ማሳረፊያ ኖቮቼርካስክ በዩክሬን ሚሳኤሎች ተመትቷል።

ቀደም ሲል የዩክሬን አየር ኃይል ኃላፊ የጦር አውሮፕላኖቻቸው መርከቧን እንዳወደሟት ተናግረው ነበር።

በጥቃቱ አንድ ሰው እንደተገደለም የክሪሚያ አስተዳዳሪ ሰርጌይ አክሲዮኖቭ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ስድስት ህንጻዎች ላይ ጉዳት መድረሱን እና የተወሰኑ ነዋሪዎችም ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች መወሰዳቸውንም አክለዋል።

በጥቃቱ ምክንያት የተቀሰቀሰውን የእሳት ቃጠሎ በቁጥጥር ስር ለማዋል አካባቢው ተዘግቶ የነበረ ቢሆንም የወደቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ወደ መደበኛ አገልግሎቱ ተመልሷል ተብሏል።

በወደቡ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ፍንዳታ የሚያሳይ የሚመስል ቪዲዮም በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ተጋርቷል።

ክሪሚያ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በዩክሬን አካልነት ብትታወቅም በአውሮፓውያኑ 2014 ሩሲያ ተቆጣጥራ ወደ ራሷ ግዛት ጠቅልላታለች።