እስራኤል በሶሪያ የፈጸመችው  ጥቃት

26 ታህሳስ 2023, 08:23 EAT

እስራኤል በሶሪያ በፈጸመችው ጥቃት አንድ የኢራን ከፍተኛ የጦር አዛዥ መገደሉን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

ሰይድ ራዚ ሙሳቪ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድ “ልምድ ያለው ወታደራዊ አማካሪ” እንደነበር ከፊል ኦፊሴላዊ የሆነው ታስኒም የዜና ወኪል ተናግሯል።

ከደማስቆ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በሰይዳ ዘይናብ አካባቢ በደረሰ የአየር ጥቃት መገደሉን የዜና ወኪሉ አክሏል።

እስራኤል ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው ኢላማዎች ናቸው ብላ በምትጠራቸው በሶሪያ ለዓመታት ወታደራዊ ጥቃቶችን አድርሳለች።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል ጥቃቶች ባለፉት ወራት በተደጋጋሚ ጨምረዋል።

ከሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ጅማሮ አንስቶ በሶሪያ የሚገኘው የኢራን ጦር የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድን ከሚወጉ አማጽያን በተቃራኒ ቆሞ ለአል አሳድ ድጋፉን ችሯል።

ሙሳቪ እ.ኤ.አ. በ2020 በአሜሪካ ለተገደለው የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድ አዛዥ ቃሴም ሱሌይማኒ ረዳት እንደነበር በዘገባው ተጠቅሷል።

በታስኒም ዘገባ መሠረት በሶሪያ ከሚገኙት በጣም ከፍተኛ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድ ኦፕሬተሮች አንዱ ነበር። በቴህራን እና በደማስቆ መካከል ያለውን ግንኙነት ማስተባበሩም ይነገራል።

የኢራን አብዮታዊ ጥበቃዎች እስራኤል “ለዚህ ወንጀል ትከፍላለች” ብለዋል።

የድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶችን በተመለከተ እምብዛም የማይናገረው የእስራኤል ጦር በኩል እስካሁን የተሰጠ አስተያየት የለም።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ኢራን እስራኤል በሶሪያ ውስጥ ሁለት የአብዮታዊ ጠባቂ አባላትን ገድላለች ስትል ከስሳለች።