የራሻ አሚን ቤተሰብ
የምስሉ መግለጫ,የራሻ አሚን ቤተሰብ

26 ታህሳስ 2023

የራሻ አሚን የአምስት ዓመት ልጅ ሌሊት ላይ በፍርሃት ሽንቱን አልጋ ላይ ሳለ ይለቃል።

ያለፈው ጥቅምት በካርቱም ሳሉ የጎረቤታቸው ቤት በሚሳዔል ከተመታ ጀምሮ ታዳጊው በፍርሃት ተይዟል።

“ማታ እያለቀሰ ይነሳል። አስፈሪ ሕልም ስለሚያይ ፈርቶ ነው የሚነቃው” ትላለች እናቱ።

ራሻ ሁለት ልጆች አሏት።

ጥይት ግድግዳዋን በስቶ ሲገባ ሌላኛው ልጇን ሊመታው ተቃርቦ ለጥቂት ነው የተረፈው።

ልጇ ገና 20 ወሩ ነው። ተኝቶ ሳለ ነው የተተኮሰው።

ዒላማ የተደረገው በቤታቸው አቅራቢያ ያለ ወታደራዊ መቀመጫ ነበር።

ራሻ ግን ለልጆቿ ድምጹ የሚሰማቸው “አክሽን ፊልም እየተቀረጸ በመሆኑ” ነው አለቻቸው።

የአምስት ዓመት ልጇ ብዙም አላመናትም።

31 ዓመቷ ነው። መምህርት ናት። ከቤተሰቧ ጋር ከጦርነቱ ያመለጡት ለጥቂት ነው።

የእርስ በእርስ ጦርነቱ 10,000 ሰዎችን ለሞት ዳርጓል።

ሰባት ሚሊዮን ገዳማ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

ራሻ ቤቷ በጦርነቱ ተጎድቷል።

በስልኳ ቤቷ ያለበትን ሁኔታ ለቢቢሲ አሳይታለች።

ግድግዳው፣ መስኮቱና በሮቹ ተሰባብረዋል። በሩ ተገንጥሏል።

“አሁንም ፍርሃት ውስጥ ነን። መሬት ላይ ፍራሽ አውርደን ነው የምንተኛው። ከመስኮቱ መራቅ አለብን” ትላለች።

ቤቱ ሊፈርስ ይችላል ብለው ስለሚፈሩ ቁምሳጥን እና ፍሪጅ ጋር አይጠጉም።

በሱዳን ጦር እና ቀድሞ አጋሩ በነበረው ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል መካከል ጦርነት ከተነሳ ስምንት ወራት አልፏል።

የሁለቱ ተዋጊ ቡድኖች ጀነራሎች አለመስማማትን ተከትሎ ነው ግጭቱ የተነሳው።

ጦሩ አገሪቱን መዲና ጨምሮ ምዕራባዊ ዳርፉርና ሌሎችም አካባቢዎችን ለመቆጣጠር ሳይችል ቆይቶ አሁን ማዕከላዊ ሱዳን ላይ ጠንካራ ይዞታ አግኝቷል።

ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ በቅርቡ የገዚራ ዋና ከተማ የሆነችው ዋድ ማዳኒን መቆጣጠር ችሏል።

ይህ ቦታ ከግጭቱ የሸሹ ሰዎች የተጠለሉበትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የተባለው ቦታ ነበር።

ከካርቱም የሸሹ ሰዎች ለሁለተኛ ጊዜ ከዋድ ማዳኒም መሸሽ ሊኖርባቸው ነው።

የመንግሥታቱ ድርጅት እንደሚለው ከገዚራ ቢያንስ 250,000 ሰዎች ሸሽተዋል።

የሱዳን 40% ስንዴ የሚመረው እዚህ ስለሆነ የአገሪቱ ዋነኛ ቁርስ አቅራቢ ስፍራ ተደርጎ ይወሰዳል።

ቀውሱ የምግብ እጥረት እንዳያስከትልም ተሰግቷል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ “የረሃብ ስጋት” መጋረጡን አስረድተዋል።

ራሻና ቤተሰቧ ጦርነቱን ሸሽተው ለመውጣት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም።

ባሏና ልጆቿ የእንግሊዝ ዜግነት አላቸው። ከሱዳን መውጣት እንደሚችሉ አስባ ነበር።

“ብዙ ገንዘብ ከፍለው” ወደ ውጭ አገር የሚወሰዱ ሰዎች ያሉበት ቦታ ቢጓዙም አልሆነም።

መንገድ ላይ በጦርነቱ የተገደሉ ሰዎች አስክሬን ወድቆ ተመልክተዋል።

ፋብሪካዎች ሲቃጠሉ፣ ሰዎች የተተወ ሱቅ ሲዘርፉና ሌላም አስከፊ የጦርነቱን ገጽታ አይተዋል።

ለንደን የተወለደው ባለቤቷና ልጆቿ መውጣት ቢችሉም እሷ ግን መውጣት እንደማትችል ተነገራት።

“ከማጠባው ልጄ ልትነጥሉኝ አትችሉም። ስንደርስ ለቪዛ እንከፍላለን አልናቸው” ስትል እያለቀሰች የተፈጠረውን ታስታውሳለች።

ባለቤቷ መሐመድ ሰይድ እንደሚለው ወደ ቤት ከመመለስ ውጭ አማራጭ አልነበራቸውም።

ከዚያ በኋላ የእንግሊዝ መንግሥት ቤተሰቡ ከሱዳን እንዲወጣ እንዲረዳው ሲጠይቅ ቆይቷል።

የዩኬ የአፍሪካ ሚኒስትር አንድሪው ሚቼል እንደሚሉት በአንዳንድ ሁኔታዎች ሕጉን ለማላላት ሞክረዋል።

“ይህን ያደረግነው ቤተሰቦችን ለመርዳት ነው” ብለዋል።

ራሻ እና ባለቤቷ በተደጋጋሚ ለውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኢሜል ጽፈዋል።

“እንደተተውን ነው የሚሰማን” ይላል መሐመድ።

አሁን ቤተሰቡ ካርቱም ነው ያለው። በታጣቆች ተከበዋል። መብራት በየቀኑ ይጠፋል። መሠረታዊ አገልግሎት ተቋርጧል።

ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት በሱዳን ጎረቤት አገራት፣ በኢጋድ እና ሳዑዲ አረቢያ የተደረጉ ሙከራዎች አልተሳኩም።

ተዋጊዎቹ ጀነራሎች አብደል ፋታሕ አል-ቡርሐን እና ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ እስካሁን በአካል ተገናኝተው ውይይት አላደረጉም።

ተፈናቃዮች

ወደ ድርድር ጠረጴዛው ሁለቱንም ለማውጣት የተደረጉ ሙከራዎች በተለይ ባለፉት ሳምንታት የበለጠ አስቸጋሪ ሆነዋል።

ኢጋድ በውይይት ተስፋ እንዳለ መናገራቸውን አል-ቡርሐን ነቅፈው “እስከ ድል ወይም መስዋዕትነት ድረስ” እንደሚዋጉ ገልጸዋል።

የአሜሪካና እንግሊዝ መንግሥታት ሁለቱም ወገኖች የጦር ወንጀል መፈጸማቸውን ከሰዋል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በምዕራብ ዳርፉር የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል። ሲልም ተከሷል።

ባለፉት ጥቂት ወራት በሱዳን በተለይም ማሳሊት ያሉ የአረብ ማኅበረሰብ አባላት ዒላማ ተደርገዋል። ሴቶች ተደፍረዋል። መንደራቸውም ተቃጥሏል።

የዩኬ የአፍሪካ ሚኒስትር አንድሪው ሚቼል ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን የሰብአዊ መብት ጥሰት ያደረሱና ዓለም አቀፍ ሕግ የጣሱ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጋሉ።

በሱዳን ያለው የምግብ አቅርቦት አስጊ ሁኔታ ውስጥ የነበረ ሲሆን ጦርነቱ ሲጀመር ደግሞ እጅግ ተባብሷል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃለ አቀባይ ሌኒ ኪንስሊ “ባለፉት አራት ወራት የምግብ እርዳታ ማድረስ የቻልነው ካርቱም ውስጥ ብቻ ነው” ብለዋል።

ዜጎችን መመገብ ለአገሪቱ ፈታኝ ነው የሚሆነው።

“ሁኔታው እየከፋ ስለመጣ ማንም ሰው ደኅንነት አይሰማውም። ግንቦት ላይ ረሃብ ሊከሰት ይችላል” ሲሉ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

ራሻ እና ቤተሰቧ በዘመዶቻቸው እርዳታ ነው ኑሮን እየገፉ ያሉት።

ወንድሟ ያገኘውን ገዝቶ እንዲመጣ ትልከዋለች።

ዕድለኛ የሆነ ቀን የዱቄት ወተትና ዳይፐር ገዝቶ ይመለሳል።

“ሥጋ እና ዶሮ የማይታሰብ ነገር ነው” ትላለች ራሻ።

ባቄላ እና አትክልት ዋነኛ ምግባቸው ነው።

“ልጆቼ ሰውነታቸው ቀንሷል። ልብሳቸው ከላያቸው ላይ እየወለቀ ነው” ትላለች።