
26 ታህሳስ 2023, 08:15 EAT
እስራኤል በጋዛ ላይ እያደረሰችው ያለው የአየር ጥቃት የማያባራ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለስልጣን አስታወቁ።
ባለስልጣኗ በጥቃቱ የተጎዱትን ለማከም እየታገለ ያለ ሆስፒታልን ከጎበኙ በኋላ ነው የአየር ድብደባው ምንም አይነት እረፍት እንደሌለው የተናገሩት።
የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ባልደረባዋ ጌማ ኮኔል አል አቅሳ ሆስፒታል ያዪት ነገር “ፍጹም እልቂት” መሆኑንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ ከአቅሙ በላይ ተጨናንቆ እንደሚገኝ ያስታወቁት ባለስልጣኗ ከዚህም ጋር ተያይዞ በርካታ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ማከም ተስኖታል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦራቸው በሐማስ ላይ የሚያደርገውን ጥቃት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄንን ያሉት ሰኞ ማለዳ ጋዛን ከጎበኙ በኋላ ሲሆን እስራኤል እያደረገችው ያለው ወታደራዊ ዘመቻ ገና ነው ብለዋል።
አጋራቸው አሜሪካ በበኩሏ እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመች ያለችውን የጥቃት መጠን መቀነስ አለባት ብላለች። አሜሪካ ይህንን ያስተላለፈችው በውጭ ጉዳይ ኃላፊዋ በአንቶኒ ብሊንከን በኩል ከቀናት በፊት ነው።
በሌላ ዜና የአሜሪካ ኃይል ኢራቅ ውስጥ ‘በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች’ ላይ የአየር ጥቃት ማድረሱን ፔንታጎን ገልጿል።
ኢርቢል በተሰኘው የአየር ጦር ሰፈር ላይ ከዚህ ቀደም በደረሰ ጥቃት ሶስት የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ለደረሰው ከባድ ጉዳት ምላሽ ነው ተብሏል።
- ደስታ የራቃት የቤተልሔም ከተማ25 ታህሳስ 2023
- ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት የጋዛ ነዋሪዎች ከሞት ጋር ተፋጠዋል22 ታህሳስ 2023
- ልብሳቸው ተገፎ ጋዛ ውስጥ በእስራኤል ወታደሮች የተያዙ ፍልስጤማውያን ወንዶችን የሚያሳይ ቪድዮ ይፋ ሆነ8 ታህሳስ 2023
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ አስቲን አገራቸው የፈጸመችው ጥቃት በሄዝቦላህ እና አጋሮቹ በሚገለገሉባቸው ሶስት ተቋማት ላይ ያነጣጠረ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
በኢራቅ እና በሶሪያ በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ ሚሊሻዎች ተደጋጋሚ ጥቃቶች ማድረሳቸውን የገለጹት ሎይድ ኦስቲን አገራቸው ህዝቧን እና ተቋማቷን ከመጠበቅ ወደ ኋላ እንደማትል አሳስበዋል።
እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን የተቀናጀ ጥቃት ተከትሎ በቀጣናው ሄዝቦላህ እና ሌሎች የታጠቁ ሚሊሻዎች እንቅስቃሴ እየተጠናከረ ይገኛል።
የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ዳይሬክተር ቶም ዋይት በአሁኑ ወቅት 150 ሺህ የሚገመቱ የማዕከላዊ ጋዛ ነዋሪዎች ከእስራኤል ጦር አካባቢውን ለቃችሁ ውጡ የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።
ጋዛን የጎበኙት ጌማ ኮኔል በበኩላቸው “በዲር አል ባላህ ከተማ በሚገኘው አል አቅሳ ሆስፒታል ያየሁት ፍጹም እልቂት ነው” ብለዋል።
በከፋ ሁኔታ የቆሰሉ ሰዎች በሆስፒታሉ ቢኖሩም ከአቅሙ በላይ በመጨናነቁም ሳይታከሙ ወረፋ ለመጠበቅ መገደዳቸውን ነው የተናገሩት።
የተወሰኑትም ቁስለኞች እሁድ እለት በማዕከላዊ ጋዛ በሚገኘው አል ማጋዚ የስደተኞች መጠለያ እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት የቆሰሉ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
በዚህ የእስራኤል ጥቃት ቢያንስ 70 ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር የሚገኘው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ በማግሃዚ የተፈናቃዮች መጠለያ ስለደረሰው ክስተት ሪፖርት እንደደረሰው ገልጿል። መከላከያው “በጋዛ ላይ በንጹሃን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በመቀነስ ላይ ያለመ እርምጃዎችን እየወሰደም” ስለመሆኑ ገልጿል።