
26 ታህሳስ 2023
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) በምዕራብ አርሲ የምትገኘውን፣ ሌጲስን የ2023 የዓለም የቱሪዝም መንደር ብሎ ከመረጣቸው መንደሮች መካከል አንዷ ናት።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ምርጥ የቱሪዝም መንደር በሚል ስም ሳቢ የሆኑ የዓለም መንደሮች ማወዳደር የጀመረው እኤአ በ2021 ነው።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በኦሮምያ እና አማራ ክልሎች የሚገኙትን ወንጪን እና ጮቄን በዓለም ቱሪዝም መንደርነት አስመዝግባለች።
የዓለም የቱሪዝም ድርጅት በዚህ ዓመት ሦስተኛ ዙሩን ውድድር ያካሄደ ሲሆን፣ ከመላው ዓለም ከቀረቡ 260 መንደሮች መካከል 54 መንደሮች ምርጥ የዓለም የቱሪዝም መንደር ስያሜን አግኝተዋል።
እነዚህ መንደሮች ተመርጠው እውቅና የተሰጣቸው በጥቅምት ወር ሳማካርድ ኡዝቤኪስታን በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ነበር።
በዚህም መሰረት ሌጲስ የተቀመጡትን ዘጠኝ የመምረጫ መስፈርቶች አሟልታ የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር ተብላለች።
በ2023 ከአፍሪካ የዓለም የቱሪዝም መንደር ተብለው የተመረጡት ሁለት ብቻ ናቸው።
እነዚህም በኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያ ክልል የምትገኘው ሌጲስ አንዷ ስትሆን ሁለተኛዋ ደግሞ ግብጽ የምትገኘው ዳሃሹር መንደር ነች ነች።
ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ሌጲስን ጨምሮ ሦስት የኢኮ ቱሪዝም መንደሮችን በዓለም አቀፍ ደረጃ አስመዝግባለች።
እነርሱም በ2021 በኦሮምያ ምዕራብ ሸዋ የምትገኘው ወንጪ፣ በ2022 ደግሞ በአማራ ክልል ጎጃም የምትገኘው ጮቄ መንደር እና በ2023 ደግሞ ሌጲስ ናቸው።
- የመስቀል በዓልን ጨምሮ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ያስመዘገበቻቸው 15 ቅርሶች28 መስከረም 2023
- በከተሜዎች ዘንድ ‘ፋሽን’ እየሆነ የመጣው ተራራ መውጣት6 ግንቦት 2023
- ሸዋል ኢድ – ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የመዘገበው የሐረሪዎች የአደባባይ በዓል10 ታህሳስ 2023
የሌጲስ መንደር በየት ትገኛለች?
ከመሀል አዲስ አበባ ወደ ደቡብ 160 ኪሎ ሜትር ሲኬድ፣ ምዕራብ አርሲ ዞን አርሲ ነገሌ እና ቆሬ ወረዳዎች መካከል ትገኛለች።
እኤአ ከ2010 ጀምሮ የአካባቢውን ተፈጥሮ እና ባህል በግንባር ቀደምትነት በመንከባከብ እና በማልማት እየሰሩ የሚገኙት አቶ ዳቀቦ ዳሌ የአንሴዳ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዳይሬክተርም ናቸው።
ድርጅታቸው አንሴዳ (ANCEDE) የአካባቢ ጥበቃ እንክብካቤ እና ልማት የሚሰራ መሆኑንም ይናገራሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራርያ ከሆነ የዓለም ቱሪዝም መንደሯ ሌጲስ ከሁለት የምዕራብ አርሲ ዞን ወረዳዎች የተውጣጡ አራት ቀበሌዎች የተዋቀረች ነች።
ሌጲስ የዓለም የቱሪዝም መንደር፤ ለዋና ከተማዋ አዲስ አበባ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ መሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ የቱሪስት መዳረሻ ከተሞች የሆኑት ሐዋሳ እና ሻሸመኔም በአቅራብያዋ ናቸው።
በተጨማሪም አብጃታ ሻላ ፓርክ ተፈጥሮን ለመመልከት የሚሄዱ ጎብኝዎች ሌጲስን በቅርብት ያገኟታል።
የላንጋኖ ሐይቅ ደግሞ የሌጲስ የቱሪዝም መንደር ኩታ ገጠም ነው።
ሌጲስ የቱሪዝም መንደር በኢትዮጵያ የቱሪስት መንደር ተብለው ስማቸው ካርታ ላይ ከሰፈሩ ሦስት አካባቢዎች መካከል አንዷ ሆናለች።

ጎብኝዎች ሌጲስ ቢሄዱ ምን ምን ይመለከታሉ?
ሌጲስ አራት የገጠር ቀበሌዎችን በስሩ አቅፎ የያዘ የጋምቦ ጥብቅ ስፍራ አካል ነው።
ከሌጲስ ጀርባ የሚገኙት የዱሮ እና ካካ ተራራዎች የተራራ ጉዞ ለማድረግ ለሚፈልጉ ጎብኚዎች ምቹ ናቸው።
የዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ የእደ ጥበብ ስራዎች ሌጲስ ተሸላሚ ካደረጓት መስፈርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ሌጲስ መዳረሻቸው የሚሆን ጎብኚዎች ተራራ መውጣት የሚወዱ፣ የእግር ጉዞ ማድረግ የሚያስደስታቸው ከሆነ ሁነኛ ስፍራ ነች።
በዚህ ስፍራ በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው የሌጲስ ደን እና የተፈጥሮ መስህብ ይጎበኛል።
በሌጲስ የተለያዩ አዕዋፋት፣ እንደ ነብር፣ ከርከሮ፣ ኒያላ፣ ጦጣዎች እና ጎሬዛዎች የመሳሰሉ የዱር እንስሳትን መመልከት ይቻላል።
የአካባቢው የተለያዩ መልክዓ ምድሮች እና የተራራ ሰንሰለቶች፣ ድንቅ ሸለቆዎችን ይዟል።
አቶ ዳቀቦ ዳሌ የገጠር መንደር ሽታ፣ ኩልል ያሉ ወንዞች ድምጽ፣ የወፎች ዝማሬ፣ የዝንጀሮዎች ከዛፍ ዛፍ ዝላይ ፣ የሚበሉ የዱር ፍሬዎች እንደዚሁም የተለያዩ የዱር አራዊቶችን መመልከት የናፈቃቸው የዓለም የቱሪዝም መንደር ወደ ሆነችው ሌጲስ በመምጣት ናፍቆታቸውን መወጣት ይችላሉ ይላሉ።
በተፈጥሮ ጥላ ስር ለማረፍ፣ ያልተበረዘ እና ማስመሰል ያልጎበኘው እስከ ኢትዮጵያዊ ወዘናው ያለ የእንግዳ አቀባበል፣ ቀልብ የሚያክም ተፈጥሮ ለሚሉ ጎብኚዎች ሌጲስን የሚስተካከል እንደሌለ አቶ ዳቀቦ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ።
በአጠቃላይ ወደ ሌጲስ መንደር ከሄዱ ቢያንስ የሚከተሉትን ተመልክተው የታወከ መንፈሳቸውን ያረጋጉበታል ይላሉ አቶ ዳቀቦ።

በ”ወንተሼ ሜዳ” የፈረስ ጉግስ፤ በዚህ የሌጲስ መንደር ኅብረተሰቡ ለዘመናት ጠብቆ ያቆየው የፈረስ ግልብያ ወደ ቱሪዘም መስህብነት ተለውጧል።
ለጥ ያለ ሰፊ አረንጓዴ መስክ እና በጫካ ተከብቦ በተለያዩ ጌጣጌጦች የተዋቡ ፈረሶች በአካባቢው ነዋሪዎች ለጎብኚዎች እንደሚመቹ ሆነው ተዘጋጅተዋል።
ይህ የፈረስ ግልብያ መስክ ወንተሼ ይባላል። የፈረስ ጉግሱ ቋሚ በሆነ ዓመታዊ ፕሮግራሞች የሚካሄድ ሲሆን፣ ከቅርብ እና ከሩቅ የሚመጡ አንግዶች የሚሳተፉበት ሆኖ ይዘጋጃል።
ይህ ዝግጅትም በህብረ ዝማሬ እና በተለያዩ ባህላዊ ዝግጅቶች ታጅቦ የሚደረግ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ እንግዶች በሚጎበኙበት ማንኛውም ወቅት ፈረስ ግልብያ የሚፈልጉ ከሆነ በፍላጎታቸው ላይ ተመስርቶ አገልግሎት የሚያቀርቡ የፈረስ ባለቤቶች ተደራጅተው እና ተገቢውን ስልጠና ወስደው አገልግሎት ያቀርባሉ ይላሉ አቶ ዳቀቦ።
“ይህ መንደር በምርጥ የዓለም የቱሪዝም መንደርነት ሲካተትም ሌጲስ የፈረስ ግልብያ መንደር የሚለው ከሌጲስ ፏፏቴ ጋር አንድ ላይ አቅርበን ነው።” ሲሉም ያክላሉ።
የሌጲስ ወንዝ የሚፈጥረው ፏፏቴ ሌላው የአካባቢው ትልቁ የኢኮ ቱሪዝሙ መስህብ መገለጫ ነው።
ይህች መንደር በዓለም የቱሪስት መንደር ደረጃ እንድትታወቅ ካደረጋት ነገር ዋነኛው፣ የሌጲስ ፏፏቴ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።
ይህ ፏፏቴ ጥበቃ በተደረገለት ጫካ ውስጥ፣ ከላይ ከዳገት ወደ ታች ሲወረወር ከአካባቢው ተፈጥሮ ጋር ሰምሮ ልዩ ውበት ይፈነጥቃል።
በሌጲስ ፏፏቴ ዙርያ የሚገኘው የተፈጥሮ ጫካ ለአካባቢው ተጨማሪ ውበት ሰጥቶታል።
በተጨማሪም የተፈጥሮ አቀማመጡ ውብ የሆነው ይህ ጫካ፣ ብዙ ዓይነት ዝርያ ያላቸው አእዋፋት፣ የተለያዩ ዱር አራዊቶች በጉያው አቅፎ ይዟል።
በዚህ በ2023 የዓለም የቱሪዝም መንደር አካባቢ ብዙ የተለያየ ጽሑፍ የሰፈረባቸው የትክል ድንጋዮች መኖራቸውን አቶ ዳቀቦ ይናገራሉ።
ባለ ብዙ ቅርንጫፍ ዋርካ ወደ ሌጲስ የቱሪዝም መንደር የሚመጡ ጎብኝዎች ሌላው የሚገጥማቸው በተፈጥሮ ለየት ያለ የቱሪስት መስህብ ነው።
“ስሩ አንድ የሆነ ትልቅ ዛፍ፣ ቅርንጫፉ ግን ብዙ የሆነ ቅልጡሬ [የፍየል ዋርካ] የሚባል ዋርካ አለ። ይህ ዋርካ መንገድ ዳር ይገኛል።”
የፌደራሉ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ጋር በመሆን ባለሙያዎችን ልኮ መሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች የሚያሟላ መሆኑን ከገመገመ በኋላ ከቀረቡት ሰባት የኢትዮጵያ መንደሮች ሌጲስ በቀዳሚነት ምርጥ መንደር ተብላ ተመርጣለች።
የዓለም ማኅበረሰብ ያወጣውን እነዚህን መስፈርቶች አሟልታ የተገኘችው የሌጲስ መንደር፣ እንድታሸንፍ ካደረጓት ነገሮች መካከል አንዱ የአካባቢው ባህልን ጠብቃ በማቆየቷ ነው።
አቶ ዳቀቦም “ሌጲስ ባህሉን ጠብቆ እና የተፈጥሮ ሀብቱን ተንከባክቦ እዚህ ያደረሰ ነው።”
እኤአ በ2010 USAID ፈንድ አድርጎት Ethiopian sustainable tourism alliance (ESTA) በተባለ ፕሮጀክት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የእንክብካቤ ስራ የተጀመረለት ሌጲስ መንደር ዛሬ ለቱሪስት መስህብ የሚሆን በርካታ ውብ ባህሎች እንዳሉት አቶ ዳቀቦ ይናገራሉ።

ምን መሟላት አለበት?
የሌጲስ ነዋሪዎች በከፊል አርሶ አደር ናቸው የሚሉት አቶ ደቀቦ፣ ኅብረተሰቡ የበለጠ ጥቅም አግኝቶ በቀጣይነት ይህችን የቱሪስት መስህብ የሆነች መንደር እንዲንከባከብ ለማድረግ፣ ለመንደሯ መሟላት ያለባቸው መሰረተ ልማቶች እንዳሉ ይገልጻሉ።
ወደ ሌጲስ በሁለት አቅጣጫዎች የሚወስዱ የኮሮኮንች መንገዶች አሉ። አንዱ በቆሬ ወረዳ በኩል ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በአርሲ ነገረሌ ወረዳ በኩል ነው።
እነዚህ ሁለቱም መንገዶች የተሟሉ እና ደረጃቸውን የጠበቁ ስላልሆኑ ጥገና እና ማሻሻያ ይፈልጋሉ።
በሌጲስ መንደር አቅራብያ የሚገኙ ትላልቅ ከተሞች እና የቱሪስት መዳረሻዎች መኖራቸውን የሚያስታውሱት አቶ ዳቀቦ፣ መንደሯ ከእነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች እንድትጠቀም መሟላት እና መስተካከል ያለባቸው መሰረተ ልማቶች መኖራቸውን አልሸሸጉም።
ወደ የዓለም ምርጥ የቱሪስት መንደር እየመጡ ተራራ የሚወጡ፣ የፈረስ ጉግስ ላይ የሚሳተፉ እንዲሁም በተፈጥሮ ጉያ ስር ገብተው፣ ከከተማ ሁካታ የሚሸሸጉ ጎብኝዎች እንዳሏት የሚናገሩት አቶ ዳቀቦ ከዚህ በተጨማሪ ማረፍያዎች፣ ሎጆች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እነደሚያስፈልጉ ይናገራሉ።
ይህች መንደር የዓለም እውቅና ስላገኘች የሚጎበኙ እንግዶች ሊበዙ ይችላሉ የሚሉት አቶ ዳቀቦ፣ “በእኛ በኩልም ቢሆን የመንግሥት አካላት፣ ኅብረተሰቡ እና ባለሀብቶች መሰራት ያለበትን እንዲያሟሉ እንጠይቃለን” ሲሉ ይማጸናሉ።